Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all 15006 articles
Browse latest View live

ቅዱስ ሲኖዶስ: በሊቢያ ክርስቲያን በመኾናቸው የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ‹‹የዘመኑ ሰማዕት›› እንዲባሉ ወሰነ፤ ‹‹የ፳፩ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማዕታት›› በመባል በአንድነት ይታሰባሉ!!!

0
0
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት ጀምሮ ለአራት ቀናት ያካሔደውን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ኹለተኛ ዓመታዊ ቀኖናዊ ጉባኤ ሲያጠናቀቅ ባወጣው ባለዐሥራ አንድ ነጥቦች መግለጫው÷ በሊቢያ ራሱን እስላማዊ መንግሥት(ዳኢሽ) እያለ የሚጠራው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ስለ ክርስቲያንነታቸው በግፍ እና በአሠቃቂ አኳኋን የገደላቸውን ኢትዮጵያውያን እና ግብጻውያን ኦርቶዶክሳውያን የሰማዕትነት ሥያሜ በመስጠት በሰማዕትነት ክብር ማክበሩን አስመልክቶ፣ ተከታዮቹን ኹለት ዐበይት ውሳኔዎች ማሳለፉን ዛሬ፣ ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. አስታውቋል፡-
  1. ምንም ጥፋት እና በደል ሳይኖርባቸው ክርስቲያኖች በመኾናቸው ብቻ በሊቢያ ሀገር አይ ኤስ በተባለ የአሸባሪ ቡድን በግፍ እና በሚዘገንን ኹኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በሟቾቹ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ተወያይቶ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ያለውን ኹኔታ በጥልቀት ከተረዳ በኋላ ሟቾቹ የዘመኑ ሰማዕት እንዲባሉተስማምቶ ወስኗል፡፡

the synod canonize ethiopian and coptic martyrs

 

ethiopian-and-coptic-christians

የኢትዮጵያ እና የግብጽ አኃት አብያተ ክርስቲያን ቅዱሳን ሲኖዶሶች በሰማዕትነት ክብር ያከበሯቸው 30 ኢትዮጵያውያን እና 21 ግብጻውያን ኦርቶዶክሳውያን የ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታ

 

2. እንዲኹም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ሚያዝያ ፲፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በሊቢያ የተሠዉት 30 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ልጆቻችን እና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 15 ቀን 2015 በሊቢያ የተሠዉት 21 የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ክርስቲያኖችበኹለቱም አብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶስ የሰማዕትነት ክብር የተሰጣቸው ስለኾነ፣ የኹለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት ተብለው በአንድነት እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡
3. በልዩ ልዩ ምክንያት ከኢትዮጵያ ሀገራቸው ወጥተው በባዕድ ሀገር የሚገኙትንና ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል እና ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያናችን መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ጋራ በመቀናጀት አስፈላጊውን ኹሉ እንድታደርግ፣ ይህን በተመለከተ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ፣ የቤተ ክርስቲያናችን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንም ርዳታ ሰጪዎችንም በማስተባበር ሓላፊነቱን ወስዶ በንቃት እና በትጋት እንዲሠራ ጉባኤው ወስኗል፡፡

The post ቅዱስ ሲኖዶስ: በሊቢያ ክርስቲያን በመኾናቸው የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ‹‹የዘመኑ ሰማዕት›› እንዲባሉ ወሰነ፤ ‹‹የ፳፩ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማዕታት›› በመባል በአንድነት ይታሰባሉ!!! appeared first on Zehabesha Amharic.


አሁንም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በደህንነቶች እየታደኑ እየታሰሩ እየተደበደቡ ነው

0
0

 

መንግስት ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም አይ ኤስ አይ ኤስን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ የተነሳበትን ተቃውሞ ሰበብ በማድረግ ፖሊስ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን እያደነ መያዙን ቀጥሏል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ፖሊስ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን በየመስሪያ ቤትና መኖሪያ ቤታቸው እያደነ ሲይዝ የቆየ ሲሆን ዛሬ ሚያዝያ 30/2007 ዓ.ም የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው ቢሴ ብርሃኑ መኖሪያ ቤቱ አካባቢ ተይዞ ታስሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ይገኛል፡፡
67በምስራቅ ጎጃም አስተባባሪና የደብረማርቆስ ዕጩ የሆነው ሳሙኤል አወቀ፣ በደቡብ ጎንደር ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ አደመና ደብረማርቆስ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነችው የሀሰብ ጌታቸው ላይ የተፈፀመባቸው ድብደባ ይህን ይመስላል፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia

The post አሁንም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በደህንነቶች እየታደኑ እየታሰሩ እየተደበደቡ ነው appeared first on Zehabesha Amharic.

የለውጥ ሃይሎችን አፍሶ በማሰር እና በማሳደድ ስር ነቀሉን የለውጥ አብዮት ማስቆም አይቻልም

0
0

metemaበሃገራችን ውስጥ ለይስሙላ በወያኔ የተጠራውን ምርጫ በመንተራስ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያጣው የወያኔ ስርአት የለውጥ ሃይሎችን እያፈሰ በማሰር እና በማሳደድ ላይ መሆኑ ባለፉት ሳምንታት እየተመለከትን ነው::የወያኔ አምባገነን ጁንታ በጠራው የጸረ አይሲስ ሰልፍ አሳቦ የተቃዋሚ ሃይሎች አባላትን በተለይ የሰማያዊ ፓርቲ የለውጥ ሃይሎችን እንዲሁም የተለያዩ የለውጥ ፈላጊ ሃይሎችን ከየመንገዱ እየለቀመ እያፈሰ በማሰር ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ የማጎሪያ ካምፖች እያከማቸ ይገኛል:እንዲሁም መንግስታዊ ሽብርተኝነትን በመሸሽ የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በገሃድ እየታየ ነው::

በአዲስ አበባ እና በክፍለ ሃገር ከተሞች ምርጫውን ተከትሎ ግርግር ያነሳሉ ሕዝባዊ አመጽ ይመራሉ ያስተባብራሉ የተባሉ ወጣቶች ታፍሰው የታሰሩ በአውቶብስ እና በጭነት መኪና ተጭነው ከየእስር ቤቱ ከከተሞች ክልል ውጪ ባሉ የማጎሪያ ካምፖች በመውስድ ላይ መሆኑን ሲታወቅ ገና ያልተጫኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በየእስር ቤቱ እንደሚገኙ ጉዳዩን እየተከታተሉ የሚገኙ የገለጹ ሲሆን የለውጥ ሃይል የሆኑ ወጣቶችን አፍሶ አስሮ እና አሳዶ ስር ነቀል የሆነውን የለውጥ አብዮት ማስቆም እንደማይቻል ወያኔዎች በፍጹም አልተረዱትም::እንዲሁም ከምርጫው ጋር በተያያዘ አፈሳውን እና መታሰሩን በመፍራት የተለያዩ ክፍለሃገር ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ሃገሮች እየተሰደዱ መሆኑ ከየአከባቢው የሚወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ::

ምርጫውን ተከትሎ የስል ነቀል አብዮት አመጽ ያሰጋው ወያነ ህዝቡ አንድነቱን በማሳየት በአደባባይ ተቃውሞውን መግለጹ ከፍተኛ ስጋት ላይ እንደጣለው ራሱ እየመሰከረ ባለበት ባሁኑ ወቅት የምርጫ ካርዶችን አምጡ በማለት በማስገደድ ላይ ይገኛል::ወያኔ ማንም እንደማይመርጠው በማወቁ ያለው እድል የመሳሪያ ሃይል ተጠቅሞ በአንድነት የተነሳበትን ሕዝብ ማዳከም ሌላው አላማ ቢሆንም አንድ ለአምስት ብሎ ከዚህ ቀደም ያደራጀው እንዳልሰራለት እና አሁንም በሌላ መንገድ ያንኑ አንድ ለአምስት የሚለውን አደረጃጀቱን ለምርጫው ለመጠቀም እየሰራ መገኘቱ የለውጥ ሃይሎች የትግል ውጤት ምን ያህል እንዳፍረከረከው በተግባይ እየታየ ነው::ይህንንም የለውጥ ሃይሎች እንቅስቃሴ በመስጋት በከፍተኛ ደረጃ ወጣቶችን በማፈስ በማሰር እና በማሳደድ ለማሸማቀቅ ቢሞክርም ቀሪው የህብረተሰብ ክፍል ከንፈሩን በመንከስ ወያኔን ሊበቀለው በዝግጅት ላይ መሆኑን በተግባር አንድነቱን አጠናክሮ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል::ወጣቱን ሃይል በማሰር እና በማሳደድ ስር ነቀሉን የለውጥ አብዮት ማስቆም አይቻልም::

‪#‎Miniliksalsawi‬

The post የለውጥ ሃይሎችን አፍሶ በማሰር እና በማሳደድ ስር ነቀሉን የለውጥ አብዮት ማስቆም አይቻልም appeared first on Zehabesha Amharic.

የግብጹን መሪ ሰብአዊነት ያዩ ባለ ሥልጣኖቻችን ለሕዝባቸው ምን ምላሽ አላቸው?!

0
0

በፍቅር


ethiopia2ብጥብጥና ኹከት በነገሠባት፣ እንደ አይ ኤስ ላሉ ጽንፈኞች፣ አክራሪ፣ ጨካኝና ነፍሰ ገዳይ ቡድን መናኻሪያ ከኾነችው ከአገረ ሊቢያ ባለፈው ሰሞን ኹላችንንም እጅጉን ያሳቀቀን፣ እንባን ያራጨን፣ እማማ ኢትዮጵያን የኀዘን ከል ያለበሰ ከፉ መርዶን፣ የሚሰቀጥጥ ዜናን ሰምተናል፡፡ እንባችን ገና ከዓይናችን ሳይደርቅና ሳይታበስም ደግሞ ከዛች የሞት ምድር በምንሰማው ወገኖቻችን የእባካችሁ የድረሱልን ጥሪ ግራ ተጋብተን፣ በምናምጥበት፣ እግዚኦ አምላክ ሆይ ድረስልን! እያልን ባለንበት ከፈርዖኖቹ ምድር፣ ከዓባይ ስጦታ ምድር፣ ከወደ ግብጽ ደስ የሚያሰኝ የምሥራችን ሰማን፡፡

ከመሐመድ ጋዳፊ ሞት በኋላ ይኼ ነው የሚባል መሪ በሌላት በአገረ-ሊቢያ በስደት፣ በሞት ፍርሃትና በሥጋት ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን የግብጽ መንግሥት ነጻ አውጥቷቸው በዛች በፈርኦኖች ምድር ወገኖቻችን ደስታቸውን ሲገልጹ ዐየን፡፡ ለእነዚህ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የኾኑት ጄ/ል አብዱልፈታህ አል ሲሲ በዓለም አቀፉ በካይሮ አየር ማረፊያ ከባለ ሥልጣኖቻቸው ጋር በአካል ተገኝተውም አቀባበል ሲያደርጉላቸው ጭምርም፡፡

ethiopiaኢትዮጵያውያኑም ስደተኞች ፊታቸው ላይ አንዳንች ልዩ ስሜትና ፈገግታ እየተነበባቸው የግብጽን ባንዲራ እያውለበለቡ ከሞት ሥጋትና ፍርሃት ላታደጓቸው የግብጽ መንግሥትና ለጄ/ል አብዱል ፈታህ አል ሲሲ አድናቆታቸውን፣ ምስጋናቸውን ሲገልጹ የሚያሣዩ ምስሎችንና ቪዲዮዎችንም በርካታ ኢትዮጵያውያን በአድናቆትና እጅግ በመገረም በማኅበራዊ ድረ ገጾች እየተቀባበሉት ይገኛሉ፡፡

በርካታዎችም፡- ‹‹ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣልን?! እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ በታሪካዊ ጠላትነት ከፈረጅናት ከግብጽ ይሄ ዓይነቱ መልካምነት፣ ደግነት እንዴት ኾነ በሚል በመንታ ስሜት ውስጥ ኾነው የግብጽን መንግሥት በእጅጉ እያመሰገኑ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ከምስጋናቸው ባሻገር ይህ የጄ/ል አል-ሲሲ ዕርምጃ አንዳች ፖለቲካዊ አጀንዳና ዲፕሎማሲያዊ መልእክት እንዳለው እየተናገሩ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደታች ጥቂት ነገሮች አነሣለሁ፡፡ ለነገሩ ይኼ ሁለተኛ ነገር ይመስለኛል፡፡ ትልቁና ዋናው ወገኖቻችን በሕይወት ለአገራቸው ምድር የሚበቁበት መንገድ መመቻቸት መቻሉ ነው፡፡

ዛሬ በሊቢያ በረኻ የወገን፣ የመንግሥት ያለኽ! በሚል ሲጮኹና ሲንከራተቱ የነበሩ እነዚህ ወገኖቻችን ከጭንቀትና ከሥጋት ተገላግለው የሰላም አየር ወደሚተነፍሱበት ወደ ግብጽ ምድር በሰላም መድረሳቸው ሰው የመኾን ክብርን፣ ፍቅርና ሰብአዊ ርኅራኄ ምን እንደኾነ በቅጡ ለምንረዳ ሰው ለኾንን ሰዎች ኹሉ ከፖለቲካውም፣ ከዲፕሎማሲያዊውም አጀንዳ በላይ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፣ የሚገባኝም!!

በእርግጥም እነዚህ ወገኖቻችን ከዛ የሞት መናፍስት ካረበቡበት፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ የሞት አበጋዞችና የክፋት ልጆች ያለ አንዳንች ከልካይ የጥፋት ሰይፋቸውን መዘው ከሚርመሰመሱበት፣ ሞትና ጭካኔ ከነገሠባት ከምድረ ሊቢያ ነጻ ወጥተው በሰላም ወደ ግብጽ ምድር መድረሳቸው እፎይ፣ ተመስገን ፈጣሪ ሆይ የሚያሰኝ ታላቅ ነገር፣ ድንቅ የኾነ የምስራችም ነው፡፡ ሌሎችም በጣርና በጭንቅ ያሉ ወገኖቻችንም የእነርሱ ዕድል እንዲገጥማቸው ነው የምንጸልየው፣ የምንመኝላቸው፡፡

እንደ እውነቱ ከኾነ ኢትዮጵያውያኑ በካይሮ አየር መንገድ የግብጽን ባንዲራ እያውለበለቡ ከመከራ፣ ከጭንቀት፣ ከሞት ለታደጋቸው የግብጽ መንግሥት ደስታቸውን ሲገልጹ ማየት በሥልጣን ላይ ላለው የኢሕአዴግ መንግሥት ትልቅ ኪሣራና ውርደት ነው፡፡ በነጋ ጠባ ልማት፣ ዕድገት እያለ የሚለፍፈው መንግሥት ሕዝቡን ከስደት ለመታደግ አቅቶትና ያለ ምንም እፍረት የወገኖቻችንን እልቂት ለራሱ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሲጠቀምበት ታዝበነዋል፡፡ ይህን ውርደት ከማየት የበለጠ እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ ምን የሚያሳፍር፣ ምን የሚጠዘጥዝ ሕመምና ሥቃይ ይኖራል ወገን፡፡

እንደው የጄ/ል አል ሲሲ ምንም የተደበቀ ይባል የተሰወረ ፖለቲካዊ/ዲፖሎማሲያዊ አጀንዳ ይኑራቸው ግና ኢትዮጵያውያኑ ወገኖቻችንን በካይሮ አየር መንገድ ማረፊያ ገኝተው አቀባበል ሲያደርጉላቸው፣ የወገኖቻችንን በግፍ መታረድ ሰምተው ቢያንስ እንኳን ለሕዝቡ መጽናኛ የሚሆን መልእክት ለማስተላለፍ እንኳን ገና እያጣራን ነው በሚል በወገኖቻችን ሞት ላይ ሰብአዊ ርኅራኄ በጎደለው ሁኔታ ርካሽ ፖለቲካቸውን ሲሸቅጡብን፣ ሲነግዱብን አንዳንች እፍረት ብሎ ነገር ያልተሰማቸው ባለ ሥልጣኖቻችን እንደው ይሄን የጄ/ል አል ሲሲን ደግ ተግባር ሲያዩ ምን ተሰምቶአቸው ይኾን?!

ከትልቅ አክብሮትና ትሕትና ጋር፣ ለመሆኑ ክርስቲያን ነን በሚል በአደባባይ ያወጁልን የአገራችን ርዕሰ ብሔርና ጠቅላይ ሚ/ር እነዚህን ወገኖቻችንን የግብጹ ፕ/ት ዓላማቸው ምንም ይሁን ምንም ካይሮ አየር ማረፊያ ድረስ ተገኝተው አቀባባል ሲደርጉላቸው ሲያዩ ምን ተሰምቶአቸው ይሆን?! መቼም ለወገናቸው ልባቸው ውስጥ የቀረች ትንሽ እንጥፍጣፊ የኾነች ፍቅር፣ ክብርና ሰብአዊነት ካላቸው ይህን ውርደትና እፍረት የሚሸከሙበት ጫንቃ፣ ወኔ ይኖራቸውስ ይኾንን?!

ከሊቢያ በረኻ እስከ ደቡብ አፍሪካ፣ ከየመን እስከ ሳውዲና መካከለኛው ምሥራቅ የወገኖቻችን ደም የውሻ ደም ያኽል እንኳን ክብር ተንፍጎት፣ ሕዝባችን ላይ የሞት ሞትና ውርደት ሲታወጅባቸው ኀዘናችን፣ ቁጭታችንን ብሶታችንን ለመካፈል አንድ ቀን እንኳን በቅጡ ድምጻቸው ያልተሰማው ባለ ሥልጣኖቻችን፣ መሪዎቻችን ይህን የአል ሲሲን ሰብአዊነት ሲመለከቱ ምን ተሰምቶአቸው ይኾን?! እናስተዳድረዋለን ለሚሉት ሕዝባቸው ፍቅርና ሰብአዊነት ብሎ ነገር የተራቆቱ እነዚህ ባለ ሥልጣኖቻችን ከበቀልና ከክፋት ወጥተው ቆም ብለው ልባቸውን፣ ራሳቸውን በቅጡ ይፈትሹ፡፡

ጭካኔና በቀል በረበበትና በሚነበብበት ፊታቸው፣ ወዳጃችን ዲ/ን ዳንኤል ክብረት እንደጸፈው ማዘናቸውንም ኾነ መደሰታቸውን በማይገልጽ ድርቅ ያለ ስሜት፣ ከሥልጣን/ከወንበር ጋር ፍቅር በወደቀ ብኩን ልባቸው፣ በስንት ጉትጎታና እግዚኦታ በቴሌቪዥን ቀርበው የሚናገሩት ቃላቸው ሣይቀር እንደ በቆሎ ቂጣ አፋቸው ላይ እየተፈረፈረ ሲወድቅ እየታዘብን፣ ውስጣችን በኀዘን ነዶና ተኮራምቶ ከበገነ፣ ከተቃጠለ በኋላ የማታ ማታ የግዳቸውን የሚያስተላልፉልን እንጨት እንጨት የሚል ማጽናኛቸው እንኳን ከልባችን ከጆሮአችን ለመድረስ አቅም የሌለው መኾኑን ማን በነገራቸው፡፡

ለመሆኑ መንግሥታችን ፍቅርና ሰብአዊነት ምን እንደሆነ ይገባዋል፣ ያውቃልን?! እስቲ ከሰማችሁን ይህችን ዘመን አይሽሬ የኾነች ‹‹ታላቁ ነፍስ›› በሚል በሕዝባቸው የሚሞካሹት፣ የህንድ የነጻነት አባት የኾኑት ማሕተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት ተናገሩትን አባባላቸውን ልጥቀስላችሁ፡- ‹‹Power based on Love is a thousand times more effective and permanent than power derived from fear.››

ፍርሃት አምጦ የወለደውን ጭካኔያችሁን እስቲ በፍቅር፣ በሰብአዊነትና በርኅራኄ ዘይት አለስልሱት፡፡ እንዲህ የምታስጨንቁትን ሕዝብ የሚያይ፣ የሚመለከት ፈጣሪ፣ ታዳጊ አምላክ እንዳለም አትዘንጉ፡፡ ያን አፍሪካን ሳይቀር የሚጠብቅ ግዙፍ የኾነ ሰራዊትና መሳሪያ ገንብቻለኹ፣ ማን ወንድ፣ የትኛውስ ጀግና ነው ከፊቴ የሚቆመው ብሎ የተገደረውን ደርግን/ጎልያድን በእናንተ በታናናሾቹ/በዳዊቶቹ ያዋረደው ሕያው አምላክ ዛሬም በዙፋኑ ላይ እንዳለ አትዘንጉት፡፡

እናም መሪዎቻችን ፍቅር ከምንም በላይ ኹሉን ለመግዛት፣ ኹሉን ለማሸነፍ የሚያስችል ታላቅ ኃይልና ብርቱ ጉልበት እንዳለው ቢረዱ እንዴት መልካም በኾነ ነበር፡፡ መሳሪያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሠራዊታቸውን ተማምነው ሕዝቡን እያስጨነቀ፣ በምስኪን ሕዝቡ ላይ የብረቱን ቀንበር እያጠበቀ ላለው መንግሥታችን ይህ መልእክት ይድርሰው ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡

እባካችሁ አምባ ገነኖች የሕዝብን ቁጣና ብሶት በኃይል፣ በመሳሪያ መግታት እንደማይቻልም ከታሪክ ተማሩ፡፡ እኛ ግን እንዲህ እንላለን፣ እንዲህም እንመኛለን፣ መቼም ምኞት አይከለከልምና፡-

ለሕዝብ የአደራ ቃል ታማኝ የኾኑ፣ በሕዝብ ፍቅር የነደዱ፣ በሕዝባቸው ጽኑ ቃል ኪዳን የታሰሩ፣ ራሳቸውን ለመሥዋዕትነት ያዘጋጁ እንደ አይሁዳዊው ሕዝብ ነጻ አውጪ እንደ ሙሴ፡-‹‹ይህን ሕዝብን በምድረ በዳ ከምታጠፋው እኔ ከሕይወት መዝገብ ደምስሰኝ፡፡›› የሚሉ፣ በሕዝባቸው ስለ ሕዝባቸው ፍቅር በነፍሳቸው የቆረጡ፣ ጽኑ፣ ባለ ራእይ የኾኑ፣ ከሥልጣን፣ ከወንበር በፊት ሕዝብ ልብ ውስጥ ትልቅ ስፍራን፣ ክብርን ያገኙ፣ ጀግና መሪዎችን እንመኛለን፤ በእውነት ይህን ማግኘትም ትልቅ መታደል ነው፡፡

እንደ መውጫ ከፍጥረት ታሪክ ማግሥት ጀምሮ የግብጽ ምድር በረከት፣ ሲሳይና ሕይወት በኾነው በዓባይ ውኃ ሺ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያና ግብጽ፣ እስከ ዛሬ ዓይንና ናጫ ከኾኑበት የዓባይ ውኃ ፖለቲካ እስጥ አገባ ለጊዜውም ቢሆን ግብጾቹ አቋማቸውን አለሳልሰው እንዲያ እንዳላልናቁንና እንዳላዋረዱን፣ እንዲህ ወገኖቻችንን ከመታደግ ባለፈ በአደባባይ በርዕሰ ብሔራቸው አማካኝነት ወገኖቻችንን በክብር ለመቀበል የቻሉበት አካኼድ በኢትዮጵያና በግብጽ በኩል ለተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ድርድር አንድ እመርታ፣ አንድ ታላቅ ድል እንደኾነ ነው የሚሰማኝ፡፡

ትንግረተኛ በኾነው በዓባይ ወንዛችን ምክንያት ጠላትነትን ከተርፍንባቸው ከግብጾቹ እንዲህ ዓይነቱ ሰብአዊነትና ርኅራኄ ማየታችን የግብጹን ፕሬዝዳንት እናመስግናቸው ዘንድ ያስገድደናል፡፡ በመንግሥታችን፣ በባለ ስልጣነሞቻችን እያፈርንና እየተሳቀቅንም ቢሆን በሂደት ግብጾቹ አቋማቸውን በማለሳለስ እንዲህ ዓይነቱን ወገኖቻችንን ከሞት የታደጉበትን የወዳጅነት ውለታቸውን፣ ሰብአዊ ርኅራኄያቸውን መቼውንም ቢሆን አገራችንና ሕዝባችን የሚረሳው፣ የሚዘነጋው አይሆንም፡፡

ግብጻውያኑ ከበዛው ተንኮላቸውና መሰሪነታቸው ጋርም ቢሆን ፈረንጆቹ፡- ‹‹A friend in need is a friend in deed!›› እንዲሉ በዚህ የእማማ ኢትዮጵያ ዋይታና የሰቆቃ የቀውጢ ጊዜ ቢያነስ ከጎናችን ቆመው ታማኝነታቸውንና ወዳጅነታቸውን አሳይተውናልና ልናከብራቸቀው፣ ልናወድሳቸው ግድ ይለናል፡፡

በሌላ በኩል ግን ከላይ ለመግለጽ እንደ ሞከርኩት ይህ የግብጽ መንግሥት ዕርምጃ ሕዝቡን ከስደት፣ ከባዕድ ጋር ከሚደርስበት ግፍ፣ መከራ፣ ሥቃይና ሞት ለመታደግ ወኔውም ኾነ አቅሙ ላነሰው፣ ለሚያስተዳድረው ለሕዝቡ ፍቅርና ክብር ለመስጠት ላዳገተው መንግሥታችን ግን ቢያስተውለው ታላቅ ውርደት፣ ኪሳራም ነው!!

የቀሩትም በስደት ላይ ያሉ ወገኖቻችን ወደ አገራቸው በሰላም ይገቡ ዘንድ ጸሎታችን ነው!! ‹‹እግዚአብሔር ትዕግሥትን፣ በጎ ትምህርትንም ይሰጣቸው ዘንድ የድካማቸውንም ፍጹም ዋጋ ይሰጣቸው ዘንድ ስለ ተሰደዱ ሰዎች እንማልዳለን፡፡›› እንድትል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ-ቅዳሴዋ!!

ሻሎም!!

 

The post የግብጹን መሪ ሰብአዊነት ያዩ ባለ ሥልጣኖቻችን ለሕዝባቸው ምን ምላሽ አላቸው?! appeared first on Zehabesha Amharic.

የብሄራዊ ደህንነት መረጃ ሃላፊዎች ጥብቅ ፍተሻ እንዲካሄድ አዘዙ

0
0

Policeሰሞኑን በአዲስ አበባ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አባላት ነን ያሉ ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች፣ ከደህንነት መስሪያ ቤት ነው የመጣነው በማለት በየክፍለከተማዎችና ወረዳዎች እየዞሩ፣ ለመንግስት መስሪያ ቤቶችም ሆነ ለግል ተቋማት ሃላፊዎች፣ ” ማንም ሰው ፣ የመንግስት ባለስልጣናም ሆነ መለዮ ለባሽ ወታደር፣ ፖሊስ ወይም ተስተናጋጅ ባለጉዳይ” ሽጉጥን ጨምሮ የትኛውንም አይነት የጦር መሳሪያ ይዘው እንዳይገቡ፣ የመስሪያ ቤት ጠባቂዎች ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር እንዲያደርጉ” ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
እንዲህ አይነት ትእዛዝ ተላልፎ እንደማያውቅ የሚናገሩት ምንጮች፣ ትእዛዙ መጪውን ምርጫ ተከትሎ ረብሻ ሊፈጠር ይችላል ከሚል ስጋት ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮች አስተያየታቸውን ቢሰጡም፣ ትእዛዙ በኢህአዴግ ባለስልጣኖች ላይ ሳይቀር መተላለፉ ውሳኔው ከመጪው ምርጫ ጋር ብቻ ያልተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል።
የደህንነት ሰራተኞች ለመስሪያ ቤት ሃላፊዎች ብቻ ሳይሆን ትእዛዙን ለጥበቃ ሃላፊዎችም እየሰበሰቡ በመናገር ላይ ናቸው።

Source:: Ethsat

The post የብሄራዊ ደህንነት መረጃ ሃላፊዎች ጥብቅ ፍተሻ እንዲካሄድ አዘዙ appeared first on Zehabesha Amharic.

ዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 74 (በPDF ያንብቡ)

“ዜጎችን በማዋረድ የሚደሰት አገዛዝና ለመዋረድ የፈቀደ ሕዝብ እስካለ ድረስ የቁልቁለቱ ጉዞ መጨረሻ የለውም”–አርበኞች ግንቦት 7

0
0

የአርበኞች ግንቦት 7 በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ጽሁፍ

የህወሓት አገዛዝ ፋሽስታዊ ባህርያት እያደር መረን እያጣ፤ ነውረኛ እየሆነ መጥቷል። በአሳለፍነው ሣምንት ብቻ እንኳን አስነዋሪ ይዘት ያላቸው ሁለት ፋሽስታዊ ክስተቶችን አስተውለናል።
ginbot 7
አንዱ በምርመራ ስም በታሳሪዎች ላይ የሚደረገው አሳፋሪ ሰቆቃ ነው። በገላቸው በሚያፌዙና በሚሳለቁ ተቃራኒ ፆታ መርማሪዎች ፊት ለሰዓታት ተመርማሪዎች ራቁታቸውን እንዲሆኑ የሚደረግበት እና እየተፌዘባቸው የሚደበደቡበት ሥርዓት መኖሩ የጉዳቱ ሰለባዎች ይፋ ሲያወጡ እፍረቱ ለመርማሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ይህንን ጉድ ተሸክመን ለኖርነው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነው። በተለይም ደግሞ እንዲህ ዓይነት ክብረነክ ሰቆቃ በሴቶች ላይ እየተፈፀመ መሆኑን ስንሰማ አገራዊ ውርደቱ ያሸማቅቀናል። እንዲህ ዓይነቶችን በሰው ስቃይና እፍረት የሚዝናኑ ጉዶችን ተሸክመን የምኖር መሆናችን ሁላችንን ያዋርደናል። ይህንን አስነዋሪ “የምርመራ ዘዴ” ያጋለጡት የዞን 9 ብሎገሮች፣ ጋዜጠኞችና ፓለቲከኞች ክብርና ሞገስ የሚገባቸው ጀግኖች ሲሆኑ የተዋረዱት እነሱ ሳይሆኑ እኛ ኢትዮጵያዊያን መሆናችን ሊሰማንና “ውርደት በቃ” ልንል ይገባናል።

ሁለተኛው አሳፋሪ ድርጊት ደግሞ ወገኖቻችንን በግፍ ባረደው አይሲስ በተሰኘው አሸባሪ ድርጅት ላይ የህወሓት አገዛዝ የተለሳለሰ አቋም ወስዷል ብለው ራሱ ህወሓት በጠራው ሰልፍ ላይ ተቃውሞዓቸውን ባሰሙ ወጣቶች ላይ አገዛዙ የወሰደው የኃይል እርምጃና ከዚያም ወዲህ እየተደረገ ያለው ነገር ነው። አገዛዙ ለፕሮፖጋንዳው ይጠቅመኛል ብሎ በጠራው ሰልፍ ወጥተው ተቃውሞዓቸውን የገለፁ ወጣቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበዋል፤ በጅምላ ወደ እስር ቤቶች ተግዘዋል። የአገዛዙ ካድሬዎች ወገኖቻችንን የፈጀውን አይሲስን በመቃወም ፋንታ የራሱ የህወሓትን ውል አልባ ህግ አክብረው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትን ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን እና አረና ፓርቲን እየወነጀሉ መሆኑ አጅግ አሳፋሪ ነገር ነው። የአይሲስን አረመኔአዊ ድርጊት ከኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ጋር ለማገናኘት በህወሓት የደህንነት ቢሮ አማካይነት እንቅስቃሴ መጀመሩ እየተሰማ ነው። ለወጣቱ በብዛት መሰደድ በምክንያትነት የሚያቀርቡት ደላሎችን መሆኑ አላዋቂነት ሳይሆን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቅራኔው በኢትዮጵያዊያን መካከል እርስ በርስ እንዲሆን ያለመ መሠሪነት ነው። ከዚህም አልፎ የትግራይ ወጣቶችን ነጥሎ በመሰብሰብ “ትምክህተኞች ሊበሉህ ነውና ታጥቀህ ሳይቀድሙህ ቅደም” እያሉ መቀስቀስ በመንግሥት ደረጃ የእርስ በርስ እልቂትን ከማደራጀት ተለይቶ አይታይም። የሥርዓቱ ይሉኝታ ቢስነት የደረሰበት ዝቅጠት ገላጭ ከሆኑ ነገሮች አንዱ “እስከምርጫ መጨረሻ ድረስ ልጆቻችሁን አስረን እናቆይላችሁ” እያሉ ወላጆችን እስከመጠየቅ መድፈራቸው ነው።
arbegnoch ginbot 7
ከላይ በአጭሩ የተዘረዘሩት ኩነቶች የሚያረጋግጡት ህወሓት የተማከለ አመራር አጥተው መንገድ የጠፋቸው፤ ሆኖም ግን እጃቸው ውስጥ የገባው ስልጣንና ሀብት ላለማጣት ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ አውሬዎች ስብስብ መሆኑ ነው። እንዲህ ዓይነቱን የአውሬዎች ስብስብ የሚገዛው የህግም ሆነ የሥነ-ምግባር ገደብ የለም። ህወሓት እስር በርሳችንን አባልቶ አገራችንንና ሕዝቧን ወደ ማንወጣው አዘቅት ከመክተቱ በፊት ራሱ ህወሓትን ማስወገድ እና በምትኩት ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን መገንባት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው። ይህ ካላደረግን አሁን በወህኒ ቤቶች የሚደረገው ዜጎችን ልብስን አስወልቆ የማዋረድ አስነዋሪ ተግባር ነገ በአደባባዮች የማይደረግ ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለንም። ይህ ትውልድ ኃላፊነቱ ካልተወጣ ህግን አክብረው ከአገዛዙ የተለየ ሀሳብ እናራምዳለን የሚሉ ወገኖቻችን በሙሉ አደጋ ውስጥ ናቸው። በህወሓት መሠሪ ተግባራት ሳቢያ በክርስትናና እስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው መግባባት እንዲሻክር እየተደረገ ነው። ዜጎችን በማዋረድ የሚደሰት አገዛዝና ለመዋረድ የፈቀደ ሕዝብ እስካለ ድረስ የቁልቁለቱ ጉዞ መጨረሻ የለውም። ይህንን ማስቆም ያለብን እኛ ሁላንችንም ነን። በአደባባይ መደራጀት ሲከለከል በምስጢር መደራጀትን መልመድ የኛ ኃላፊነት ነው። የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓልን ስናከብር ከቀደምቶቻችን ልንወርስ ከሚገቡን እሴቶች አንዱ ለክብራችን ዋጋ መክፈል ያለብን መሆኑን ጭምር ነው። የኢትዮጵያዊያን ክብር በወያኔ ሲዋረድ እያየን ዝምታን ከመረጥን ከዚህም የባሰ እንዲመጣ መፍቀዳችንን እንወቀው።

አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የዜጎችና የአገር ውርደት ይብቃ! በተባበረ ክንድ ህወሓት ይወገድ፤ በምትኩም ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመመሥረት መሠረት እንጣል፤ ይህንን ታላቅ ኃላፊነት ለመወጣት በኅብረት እንነሳ ይላል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!

The post “ዜጎችን በማዋረድ የሚደሰት አገዛዝና ለመዋረድ የፈቀደ ሕዝብ እስካለ ድረስ የቁልቁለቱ ጉዞ መጨረሻ የለውም” – አርበኞች ግንቦት 7 appeared first on Zehabesha Amharic.

በመጨረሻም በግብጽ ነጻ ወጡ…እኛ ግን መንግስት አለን እንዴ?

0
0

ክንፉ አሰፋ

የፌስቡክ አርበኛው ቴድሮስ አድሃኖም ቦሌ ሄደው ከሊብያ ነጻ የወጡ ዜጎችን ሲቀበሉ አየን። እፊታቸው ላይ የማፈር ሳይሆን የጀግንነት ስሜት ይነበባል። አቀባበላቸውም 90 ደቂቃ በእንቴቤ የሚለውን ታሪክ ይመስላል። ኡጋንዳ ላይ የታገቱ ዜጎችዋን ለማስለቀቅ እስራኤል ያደረገችው ገድል። ቴድሮስ አድሃኖምም በኩራት እና በድል አድራጊነት ስሜት ነው ስደተኞቹን የተቀበሉት። መቼም ሼም የሚባል ነገር ከነሱ ዘንድ ጠፍቷል። በስራቸው ማፈር ሲገባቸው አይናቸውን በጨው እያጠቡ የሌላውን ድል እንደራስ ያጣጥሙታል። ህሊና ያለው ሰው ያሳደዳቸውን እና በባእድ ነጻ የወጡ ዜጎቹን ሲመለከት ብርክ ነው የሚይዘው። አልገባቸው ይሆናል እንጂ ክብራቸውን የሚቀንስ ማንነታቸውን የሚፈትን ድርጊት ነው። አስቀድመን በግብጽ መገናኛ ብዙሃን ዜናውን ባንሰማ ኖሮ ደግሞ ሌላ ታሪክ ይነግሩን እንደነበር ጥርጥር የለውም።
ethiopia
ሁኔታቸው አባት እና እናቱን በግፍ ገድሎ ፍርድ ቤት የቀረበውን አይነደረቅ ያስታውሰናል። ወንጀል መፈጸሙን ያመነው ይህ ጎረምሳ የፍርድ ማቅለያ እንዲናገር በመሃል ዳናው በተጠየቀ ግዜ እንዲህ አለ። “ያው አባት እና እናት ስለሌለኝ፤ ለወላጅ አልባ ልጆች እንደሚደረገው ልዩ እንክብካቤ ያስፈልገኛል።”

በአለም-ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንደሰማነው እነዚህን ዜጎች ነጻ ያወጣችው ግብጽ ናት። ከአይሲስ ጥርስ ወጥተው ግብጽ ምድርን ሲረግጡ አቀባበል የተደረገላቸው በምንስቴር ደረጃ ሳይሆን በረዕሰብሄር ደረጃ ነው። ከአውሮፕላን ሲውርዱም የግብጽን ባንድራ እያውለበለቡ ነበር። አዲስ አበባ ላይ ግን ባንዲራ አልያዙም። ይህም ትልቅ ትርጉም አለው። ባንዲራ የአገር ክብርና ፍቅር ነው። የህዝብ አንድነት እና ትሰስር በባንዲራ ይገለጻል። አንገት ላለው፤ አንገቱን የሚያስደፋ እውነታ!

በግብጽ መከላከያ ሃይል ነጻ የወጡት እነዚህ 27 ኢትዮጵያውያን ካይሮ ሲደርሱ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ፕሬዝዳንታዊ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ቅድምያ ለሰብአዊ ፍጡር ክብርን ከመስጠት የሚመነጭ ተግባር ነው። ትልቅ የፖለቲካ ትርፍ ቢያገኙበትም ይገባቸዋል። ክቡር የሆነን ሰው ነብስ አትርፈዋልና ይህ ለኛ ትልቅ ትርጉም ነው የሚሰጠን። መልካም ስራ ለክፉ ቀን ስንቅ ነው።

አዲስ አበባ ሲገቡ ግን ሃይለማርያም ደሳለኝ ሊቀበሏቸው አልቻሉም። ምክንያቱም ግልጽ ነው። ለሳቸው ያለገደብ የተሰጠው ስልጣን ተቃዋሚዎችን እና ዲይስፖራውን መሳደብ ብቻ ነው። ምናልባትም ለኚህ አሻንጉሊት ዋነኛው ችግር አይሲስ ሳይሆን አሜሪካ ላይ የተነሳው አልሻባብ ነው። አሜሪካ ባሸተተች የኛዎቹ ያስነጥሳቸዋል። ለዚህ የአሜሪካ ቆሻሻ ጦርነት የኢትዮጵያን ወታደር ለመላክ አላንገራገሩም። የኛ ወገን እንደ ከብት ሲታረድ ግን የመረጡት ብሄራዊ የሃዘን ቀን ማወጅ፣ ከንፈር መምጠጥ፤ ሻማና ጧፍ ማቃጠል …። ምክንያቱ እነሱ እንደሚሉት የድንበር መዋሰን ጉዳይ አይደለም። ይህ ቢሆን አሜሪካ ሽብርተናን ለመውጋት አፍጋኒስታን ወይንም ሶርያ አያዋስናትም። መውረር ባስፈለጋት ግዜ ፓናማንም ግሪናዳንም ወርራለች። ሶማልያ ላይ ከሰፈረው ሰራዊት ስንቱ እንደሞተ በፓርላማ ሲጠየቁ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስተር ሲመልሱ፤ “ይህ ጉዳይ እናንተን አይመለከትም!” ነበር ያሉት። የፓርላማ አባላት ይህንን ወሳኝ ጉዳይ የማወቅ መብት ከሌላቸው ታዲያ ለማን ነበር ሪፖርቱ የሚቀርበው? ለአሜሪካ?

አለም ስለ አይሲስ ጭፍጨፋ ሲጨነቅ፣ እነሱ ግን ምርጫው ነው እንቅልፍ የነሳቸው። እናም በዜጋው ሰቆቃ ሳይሆን በሰላማያዊ ፓርቲ ላይ ተጠምደዋል። አይሲስን ከመዋጋት ሰማያዊ ፓርቲን ማጥፋት ይመርጣሉ። የመከላከያ ሰራዊቱ አንበሳነት በሃገር ውስጥ ብቻ መሆኑን አስመስክሯል። በዜጋው ላይ ኮማንዶ ሲለማመድ አሳዩን።

ለእነሱ ሽብርተንኛ አይሲስ ሳይሆን ጋዜጠኛ ነው። የጸረ-ሽብር አዋጅ አውጥተው ጋዜጠኛ እና ተቃዋሚዎችችን ያፍኑበታል። ሽብርተኛው ዜጋዋ ሳይሆን አይሲስ እንደሆነ ግብጽ ትምህርት የሰጠቻቸው ይመስላል። ከራስዋም አልፋ እኛኑ ስትታደግ አየን።

በዚህ ሰሞን የቴድሮስ አድሃኖም ፌስ ቡክ ገጽ ተጨናንቆ ነው የሰነበተው። የስደት ቀውሱ ያመጣውን ችግር ይዞ ትንሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መሆኑ ነው። የኝህ ሰው ስራ ጨርሶውኑ በፌስ ቡክ ላይ ሆኗል ያስብላል። ጨጓራው የተቃጠለ ዜጋም ይህንኑ ገጽ የንዴቱ ማብረጃ አድርጎታል።

በሳምንቱ መጀመርያ ላይ አይቴ ቴድሮስ እንዲህ ብለው ጽፈዋል። “የመጀመሪያ ዙር ከሊብያ ተመላሽ ወገኖች አዲስ አበባ ገብተዋል። መንግስት ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።”

ታዲያ ሚኒስትሩ እንዲህ ይበሉ እንጂ እነዚህ ወገኖች ሲገቡም ሆነ አቀባበል ሲደረግላቸውም አልታየም። እውነት ነው በኢትዮጵያዊነታቸው ሳይሆን በዘር እየተለኩ፣ ለገዢው ፓርቲ ቅርብ የሆኑ፣ ወዘተ በሱዳን በኩል እንዲገቡ መደረጉ ተሰምቷል።

ተስፋዬ ሁሴን የተባለ ወገን በዚያው ጽሁፍ ስር እንዲህ ሲል መለሰላቸው፣ “መቸስ ውሸትህ አያልቅ፣ በቀደም እለት የደቡብ አፍርካ ተመላሾች ብለህ ቀደድክ። ነገር ግን እዚህ ከደቡብ አፍርካ የገባ አንድም ስደተኛ ባልነበረበት፣ ተመላሾች ብለህ ስትዋሸን ዝም አልን። አሁን ደግሞ ከሊቢያ … መጥኔ ውሸትህን ለሚጋቱ አድርባዮች! ጊዜ እየጠበቅህ ብቻ የእንትን ተመላሾች በል። ነገ ደግሞ የሰማይ ቤት ተመላሾች እንደምትለን ተስፋ አደርጋለው። በውሸት፣ በፌዝ 24 ዓመት…”

ቴድሮስ አድሃኖም መጻፋቸውን ቀጠሉ፣ ስለ ሁለተኛው ዙር ተመላሾች። ዙቤር ኡስማን የተባለ መላሽ ደግሞ “አገር የሌለው ሰው የሄደበት ሁሉ አገሩ ነው! ኢትዮዽያውያን ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ግብፅ፤ የግብፅን ሰንደቅ ኣላማ እያውለበለቡ ሲወርዱ! ከሃበሻ ምድር ተሸርፋ “አገር” የሆነችው ግብፅ ዛሬ የእንጀራ እናታችን ሆነች!” ሲል ነበር ቁጭቱን የገለጸው።

እርግጥ ነው። ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ለዜጋው ግድ አይሰጠውም። አንድ ኢትዮጵያዊ ይልቅ አንድ የህንድ ወይንም የሳዑዲ ዜጋ በሃገራችን ትልቅ ክብር አለው። ከዜጋው ይልቅ ለባእዳን “ባለሃብቶች” ደህንነት የሚጨነቅ ስርዓት ነው። ሲጀመር ዜጋው ከሀገሩ እንዲሰደድ ያደረገው ብልሹ የሆነ ስርአቱ ነው። አርሶ አደሩችን ከቀያቸው እያፈናቀለ፣ ለም መሬታቸውን ለህንድ እና ሳዑዲ ባለሃብቶች በመናኛ ዋጋ በመቸበችብ የወጣቱን ተስፋ ገደለው። ወጣቱ አገር የለውም። ለመኖር ሲል፣ ፍትህ ፍለጋ፣ ስራ ፍለጋ፣ እንጀራ ፍለጋ ይሰደዳል።

የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮው አዲሱ አበበ ከሊቢያ ሁለት ስደተኞችን በስልክ አነጋግሮ ነበር። ሁለቱንም ወደሃገር ቤት መመለስ እንደሚፈልጉ ጠይቋቸው የሰጡት ምላሽ “መመለስ አንፈልግም!” የሚል ነው። እነዚህ ወገኖች በሞት ጥላ ውስጥ ሆነው እንዲህ ማለታቸው በሀገር ቤት ያለው ችግር ምን ያህል የከፋ መሆኑን ይጠቁመናል።

ሰሞኑን በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ አዲስ አይደለም። የአይሲሱ ግድያ አለም አቀፍ ትኩረትን ሳበ እንጂ በሳዑዲ አረቢያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በየመን፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በእስራኤል ወዘተ ፍጹም ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት በዜጎቻችን ላይ ተፈፅሟል። ሴቶች እህቶቻችን በጎረምሶች ተደፍረዋል። በአሰቃቂ ሁኔታም ገድለዋል። ለዜጎቹ የሚከራከር አካል ባለመኖሩም የተናቅን ህዝብ አደርጎናል።

እስራኤል ሃገር በፈላሽ ሙራዎች ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር መድልኦ አለም ሲያወግዘው የኛዎቹ ዝም ነው ያሉት። ባለፈው አመት ናይሮቢ ውስጥ ሰባ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እየተለቀሙ ሲታፈሱ እና ሲታሰሩ እዛ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ “ኬንያ ውስጥ ጉዳት የደረሰበት ሕጋዊ ዜጋ የለም” ሲል ነበር መልስ የሰጠው። ሊብያ በፈራረሰች ግዜ አፍሪካ ዜጎች በየኤምባሲያቸው ገብተው ሲጠለሉ ኢትዮጵያውያን መሄጃ አልነበራቸውም። በመጨረሻ ግን የናይጄሪያ ኤምባሲ ተቀብላ አስተናገደቻቸው።

አይሲስ ወደ የመን እየገባ መሆኑ በተሰማ ግዜ ሰይፉ ፋንታሁን አንድ ዘገባ አቅርቦ ነበር። በዘገባው ላይ የመን ያሉ ኢትዮጵያውያን መንግስት ከወሬ ያለፈ ምንም ነገር እንዳላደረገ ይናገራሉ። ይልቁንም ዓለምአቀፍ ሞዴልና ተዋናይ የሆነችው የሐረር ወርቅ ጋሻው ስደተኛውን ለመርዳት የአቅሟን እያደረገች እንደሆነ ጋዜጠኛ ግሩም ተ/ሐይማኖት ተናግሯል።

በየመን እየታየ ያለውም ጉዳይ እርግጥ “ኢትዮጵያ መንግስት አላት ወይ?”..የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ነው። ጋዜጠኛው የመን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ “እንረዳቸዋለን ወይስ እናርዳቸዋለን?” ነው ያለው ሲል ባሰፈረው ጽሁፉ በዶቺቬሌ ቃላቸውን የሰጡት የኤምባሲው ቃል አቀባይ አቶ አምደሚካኤል ንግግር ኣሳፈሩን ይላል። “ኢትዮጵያዊያኑን እንረዳቸዋለን። ከአይ. ኦ. .ኤም. ጋር በመተባበር ወደ ሀገር መመለስ የሚፈልጉትን እንመልሳለን” ብለዋል። … ” አዎ ይረዳሉ ግን ኤምባሲ ውስጥ ላሉ ሰራተኞች ነው። ..እኛን ግን እንረዳለን ማለት ፈልገው ሳይሆን እናርዳቸዋለን ማለታቸው ነው። ሲያርዱ እንጂ ሲረዱ መቼ ታይተው ነው።” ብሎ ነበር የጻፈው።

እውነታው ይህን ይመስላል። አንዳንድ የስርአቱ አጨብጫቢዎች ታዲያ ይህ እውነታ አይወጥላቸውም። ዜጋ እየተሰቃየ እነሱ ግን ስለ ህንጻ ይነግሩናል፤ ስለ ታምራዊው 11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ይሰብኩናል። … ሕንጻና መንገድንማ ቅኝ ገዥዎችም ሰርተዋል። ለዚያውም እነሱ ከሚነግሩን የበለጠ።

ሕዝብ ደግሞ እያለ ያለው ፣ “ከህንጻ በፊት ነጻ!” እንሁን ነው! ሀገር ማለት መሬት አይደለም። ሃገር ማለት ወንዙ፣ ተራራው፣ ሽንተረሩ፣ አደለም። ሃገር ማለት ሕዝቡ ነው። የህዝቡ ሰቆቃ ግድ የማይለው አካል መንግስት ሊሆን አይችልም።

The post በመጨረሻም በግብጽ ነጻ ወጡ… እኛ ግን መንግስት አለን እንዴ? appeared first on Zehabesha Amharic.


የምስጢራዊው ድምፃዊ ‹አዳዲስ› ምስጢሮች

0
0

ጥላሁን ገሠሠ የዛሬ ስድስት ዓመት በፋሲካ ዋዜማ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ህዝብና መንግስት እንደ አንድ ሆነው ቀብሩን እንዳደመቁትና በጋራ እንደሸኙት እናስታውሳለን፡፡ጥላሁን በህይወት በነበረባቸው ዘመናት በህይወቱ ውስጥ ያሉ ብዙ አነጋጋሪና ምስጢራዊ ጉዳዮችን ሳያብራራና ግልፅ ሳያደርግ ማለፉን ተከትሎ በዓመቱ የወጣው የህይውት ታሪኩን የያዘው መፅሐፍ ነገሮችን አፍረጥርጦ ይፋ ያደርጋል የሚል ግምት ነበር፡፡ ያም ሆኖ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ‹ደራሲያን› በቡድን ተፅፎ የታተመው መፅሐፍ በጥላሁን ዙሪያ ያሉና የሚነገሩ ምስጢሮችን ሳያፍታታም ሆነ ሳይነካ የወጣ መፅሐፍ መሆኑ በወቅቱ አነጋጋሪ ነበር፡፡ ጥላሁን ገሠሠ በሕይወት በነበረበት ወቅት ለመጨረሻ ጊዜ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ ተመስርቶ ተዘጋጀ የተባለው መፅሐፍ አንድ የህይወት ታሪክ መፅሐፍ መያዝ ያለበትን መሠረታዊ ደንቦችን ያልተከተለና ጥላሁን ገሠሠን የማይመጥን መፅሐፍ መሆኑን ቁም ነገር መፅሔት በወቅቱ አስተያየቷን አስፍራለች፡፡
tilahun
ጥላሁን ገሠሠ የሚሊዮኖችን ስሜት የመቆጣጠሩን ያህል፤ ከ50 ዓመታት በላይ የማንጎራጎሩን ያህል፤በሀገር ፍቅር ስሜት ህዝቡን ያነደደ ሰው የመሆኑን ያህል የግል ህይወቱና ማንነቱም ለብዙዎች ምስጢር ነው፡፡ በትውልዱ፤ በዕድገቱ፤ በቤተሰቦቹ ፤ በትዳር ህይወቱና በልጆቹ ዙሪያ የሚታወቁ ነገሮች የጠለቁ አይደሉም፡፡ይህንኑ መነሻ በማድረግ ይመስላል ሰሞኑን በጥላሁን ገሠሠ ዙሪያ አንድ መፅሐፍ ታትሞ ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡‹ጥላሁን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክና ምስጢር› በሚል ርዕስ በጋዜጠኛ ዘከሪያ መሐመድ የተፃፈው መፅሀፍ ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ በቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በተገለፀው መፅሐፍ ላይ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ ከአስተዳደጉ፤ከቤተሰቡ ማንነት፤ከሙዚቃው ስራው አንፃር ሳይንሳዊ የህይወት ታሪክ አፃፃፍን ተከትሎ እንደተዘጋጀ የሚናገረው ጋዜጠኛ ዘካሪያ ጥላሁን ገሠሠ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ከሁለት ወራት በኃላ ስራውን መጀመሩንና አምስት ዓመታት እንደፈጀበት ይናገራል፡፡ በአራት ምዕራፎች የተከፋፈለው መፅሐፉ 448 ገጽ ያለው ሲሆን ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በተፃፈው መፅሀፍ ላይ የተገለፁ የሀቅ መፋለሶችን እንደሚያስተካክልና ለዓመታት ምስጢር የነበሩ ጉዳዮችን ‹ሆድ ይፍጀውን › ጨምሮ ለአንባቢያን ይፋ ያደርጋል፡፡ ከቤተሰቡ በተገኘ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀው ይህ መፅሐፍ እስከዛሬ ድረስ በየትኛውም ሚዲያ ላይ ያልታዩ ጥላሁን ገሠሠ የአንድ ዓመት ህፃን ሳለ ጀምሮ ያሉ ፎቶግራፎችን አካቶ ይዟል፡፡
ያልተፈቱት ምስጢሮች
በጥላሁን ህይወት ብዙ ያልተፈቱ ምስጢሮች አሉ፡፡ በ1985 ዓ.ም ከተፈጸመበት የግድያ ሙከራ ጀምሮ የቤተሰባዊ ህይወቱና የውልደት ቦታው ምስጢር ሆነው ወይም በተዛቡ መረጃዎች ታጅበው አመታትን ዘልቀዋል፡፡
የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ጋዜጠኛ ዘከርያስ መሃመድ ከአቶ ፈይሣ ሃሰና ሃይሌ ማስታወሻ ላይ ያገኛቸውን መረጃዎች መነሻ በማድረግ እውነቱን ላሳያችሁ ይለናል፡፡ በመጽሐፉ እንደቀረበው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ የሚል ካባ የተደረበለት ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ የተወለደው አዲስ አበባ ሳይሆን ወሊሶ አካባቢ ሶየማ በተባለ ቦታ ነው፡፡ ከአቶ ፈይሣ ሃሰና ማስታወሻ የተገኘው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፡-
‹‹በወረራው ምክንያት ተበታትኖ የነበረው ቤተሰባችን ሶየማ በሚገኘው የቤተሰብ ርስት ላይ ዳግም ተገናኘ፤ በዚህ ጊዜ ጌጤነሽ (የጥላሁን እናት) መውለጃዋ ተቃርቦ በጣም ከብዳ ነበር፡፡
… መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም የመስቀል በዓል ዕለት መላው ቤተሰባችን በወላጅ አባቴ በአቶ ሃሰና ቤኛ እልፍኝ ተሰብስበን ነበር፡፡ ከዕኩለ ቀን በኋላ በትልቁ እልፍኝ ጌጤነሽ በምጥ ተያዘች፤ ፅንሱ በሆድዋ ውስጥ ፋፍቶ ስለነበር ምጧ ረጅም ሰዓት ወሰደ፤ በዚህም ምክንያት ጌጤነሽ ደካክሟት ምጧ በተራዘመ ቁጥር ድካምዋ በርትቶ አቅም እያጣች በመሄድዋ ለእሷም ሆነ ለልጅዋ ህይወት በጣም ሰጋን፤ ቤተሰቡ በሙሉ ፀሎትና ልመና ያደርግ ጀምር፤ በመጨረሻም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ሲሆን ጌጤነሽ ወንድ ልጅ ተገላገለች፤ የጌጤነሽ እናት ነገዬ አብደላ ዲንሳሞ ለተወለደው ልጅ ደገፋ ስትል ስም አወጣችለት፡፡›› (ገፅ 29-30)

ጥላሁን ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ከተለያዩ ሴቶች ጋር ጋብቻ የፈፀመ ሲሆን የመጀመሪያ ባለቤቱ መሆናቸው የሚነገረው ወ/ሮ አሥራት አለሙ ቢሆንም ጋዜጠኛ ዘከሪያ በአዲሱ መፅሐፉ ይህንን እውነት ያፈርሰዋል፡፡ የመጀመሪያ ባለቤቱ ፊት በር አካባቢ ትኖር የነበረች ፈለቀች ማሞ የተባለች ሴት ናት ይለናል፡፡ ከፈለቀች ጋር በሰርግ መጋባታቸውም ይነገራል፡፡ በወቅቱ ካሳ ተሰማ፣ እሳቱ ተሰማ እና ሸዋንዳኝ ወልደየስ የጥላሁን ሚዜዎች ነበሩ፡፡ (ገፅ 352)፡፡

ይሁን እና ከወ/ሮ ፈለቀች ጋር ረጅም አመታትን በትዳር አልቆዩም፡፡ በቅናት ምክንያት ፈለቀች ጥላው ጠፋች፡፡ ከዚያ በኋላ ሁለቱ ሰዎች ለረዥም ጊዚያት በአካል እንኳ ተገናኝተው አያውቁም ነበር፡፡ ዘከርያ የፈለቀች ጥላሁንን ባዶ ቤት ጥላው መጥፋት ከሌላ የልጅነት ታሪኩ ጋር አዛምዶ ይተነትነዋል፡፡

አቶ ፈይሳ ማናቸው?

አቶ ፈይሳ ሃሰና ሐይሌ የጥላሁን ገሠሠ አጎት ናቸው፡፡ ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ የግል ታሪካቸውን ጨምሮ የጥላሁን እና የቤተዘመዶቹን ታሪኮች በመፃፍና ፎቶግራፎቹን በማንሳት ታሪክን ለትውልድ ያስቀመጡ ታሪከኛ ሰው ናቸው፡፡ ጋዜጠኛው ዘከርያ መሐመድ አሁን በመፅሐፍ መልክ ላሳተመው አዲስ የጥላሁን ታሪክ መነሻ የሆኑት እርሳቸው ናቸው፡፡ ይህ የአቶ ፈይሳ ማስታወሻ በጥላሁን ዘንድም የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እና እሱ በሕይወት እያለ እንዲታተም አይፈልግም ነበር፡፡ ለአመታት ከጋዜጠኞች ደብቋቸው የነበሩት ታሪኮች ተገልጠው ከአዲሱ እውነት ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥን አይፈልግም ነበር፡፡ ይሁን እና ህይወቱ ካለፈ በኋላ እንደሚታተም እርግጠኛ ነበር፡፡ ለአቶ ፈይሳ ልጆችም ማንቂያ የሚመስል ሀሳብ ሹክ ብሏቸዋል፡፡ ‹‹እኔ ስሞት ይህን ታሪክ አትተኙበትም›› የሚል፡፡

የ22 ዓመታት እንቆቅልሽ

ጥላሁን ‹‹ሆድ ይፍጀው›› በሚል ያለፈው የ1985ቱ የግድያ ሙከራ በማን እና ለምን እንደተፈፀመ ጥርት ያለ መረጃ አሁንም ድረስ ባይገኝም ዘከርያ በመፅሐፉ ውስጥ ያስቀመጣቸው ትንታኔዎች ሁለት ድምዳሜዎች ላይ ሊያደርሱን ይታትራሉ፡፡ የመጀመሪያው ድምዳሜ ጥላሁን እራሱን ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል የሚል ነው፡፡ አደጋው ከደረሰበት በኋላ ለንደን ለህክምና በሄደበት ወቅት ከቅርብ ጓደኛውና የጀርመን ሬድዮ ጋዜጠኛ ከነበረው ጌታቸው ደስታ ጋር ሲያወሩ እንደቀልድም ቢሆን ራሱን ለመግደል መሞከሩን ነግሮታል፡፡ ‹‹ስማ ጥላሁን ያኔ የጀመረህ ሰውዬ ሳይጨርስ አይተውህም፤ ወንድምህ ነኝ፡፡ ነገ ብትሞት በሚቻለው በማንኛውም መንገድ ገዳይህን እፋረደዋለሁ…. ንገረኝ… ማነው የወጋህ?››
‹‹ ራሴ ነኝ››
‹‹ሂድ ባክህን… ይሄን ሂድና ለምታወራለት አውራ እኔ አለቀበልህም›› (ገፅ 290)

ጌታቸው የጥላሁንን መልስ ያመነ አይመስልም፡፡ ነገር ግን ከዚህ የጥላሁን መልስ ተነስተን ሊሆን የሚችልበትን እድል ስንገምት አንድ ጥያቄ ማንሳት ጥሩ ይሆናል፡፡ ጥላሁን በርግጥ የመግደል ሙከራ የተደረገበት በሰው ከሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩት እነዚያ ሁሉ አመታት ያ ሰው ጥላሁንን ለምን አልተተናኮለውም፡፡ መቼም አንድ ሰው በጊዜያዊ ንዴት ያን ያህል ጥቃት ይፈፅማል ተብሎ አይታሰብም፤ ከዚያ በተጨማሪ ግን በፖሊስ የምርመራ ውጤት ሊረጋገጥ አልቻለም፡፡ ወይም ተረጋግጦ ቢሆን እንኳን በድብቅ ቀርቷል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ጥላሁን እራሱን ለማጥፋት ሞክሯል ወደሚል ጫፍ ይወስዱናል፡፡ ዘከርያ በመጽሐፉ ከልጅነቱ ጀምሮ የነበሩትን የጥላሁን ህይወት በሰፊው በመተንተን እንቆቅልሾቹን ሊፈታልን ሞክሯል፡፡

በሌላኛው ጫፍ ደሞ ጥላሁን ላይ ጥቃት የፈፀመ ሰው እንዳለ እንድናስብ ይገፋናል፡፡ ሰውዬው አቶ አወቀ መንገሻ ይባላል፡፡ ከገፅ 292 – 293 ድረስ በሰፈረው ፅሁፍ የቀደሙ መፅሔቶች ላይ የወጡትን መረጃዎች መሠረት በማድረግ ስለ ጉዳዩ ተተንትኖ ቀርቧል፡፡

ጥላሁንና አቶ አወቀ የሚቀራረቡ ጓደኛሞች ቢሆኑም በመጨረሻ ግን ተኮራርፈው ነበር፤ በዚህ ምክንያት አቶ አወቀ ወይም በአቶ አወቀ የታዘዘ ሰው ጥላሁን ላይ ጥቃቱን ፈፅሞ ሊሆን ይችላል ወደሚል ሀሳብ ይገፋናል፡፡ ተከታዩን ፅሁፍ እንመልከት፡-
‹‹ በ1990ዎቹ አጋማሽ አካባቢ አንድ እለት መሻለኪያ በሚገኘው የጥላሁን ሼል ነዳጅ ማደያ ቢሮ የስልክ ጥሪ አቃጨለ፡፡ የጥላሁን ፀሐፊ ስልኩን አንስታ ‹‹ጤና ይስጥልኝ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ቢሮ›› አለች፡፡

… ‹‹አወቀ የሚባል ሰው ሞቷል፡፡ እንኳን ደስ አለህ በይው፡፡››
‹‹እንዴ! ሰው ሲሞት እንዴት ለሰው እንኳን ደስ ያለህ ይባላል?!››
‹‹ግዴለም ለእርሱ ስትነግሪው ይገባዋል፡፡ አንቺ የማታውቂው ነገር ስላለ ነው፡፡››
በማግስቱ ይሁን በሳልስቱ ጥላሁን ከአሜሪካ ስልክ ደወለ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ፀሐፊዋ ሌሎች መልዕክቶችን አስቀድማ ‹‹አወቀ የሚባል ሰው ሞቷል የሚል መልዕክትም ተቀብያለሁ›› አለችው፡፡ የቀረውን መልእክት ግን ማስተላለፍ አልፈለገችም፡፡ … ምንም እንኳ በዛች ሰዓት የጥላሁን ገፅታ ባይታያትም ፀሐፊዋ ከምትሰማው የጥላሁን ድምፅ ሁለመናው ወለል ብሎ ይታያት ነበር፡፡ ከዚያ ለራሱ የሚያወራ ያህል ‹‹ ህም እርሱ ሞተና… እኔ ነዋሪ ሆንኩኝ?!›› አለ፡፡ (ገፅ 297)

መጽሐፉ ለምን?

የመጽሐፉ አዘጋጅ ዘከርያ መሐመድ በመቅድሙ ላይ እንዳሰፈረው እስካሁን በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የሰማናቸውና ያነበብናቸው እንዲሁም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በ2002 ዓ.ም ለህትመት ባበቃው መፅሐፍ የሰፈሩት የጥላሁን ገሠሠ ታሪኮች በመሠረታዊ ሀቅ ደረጃ ጉድለት አለባቸው፡፡ ‹‹ ጥላሁን ወደ ሙዚቃ ዓለም ከገባበት ዘመን አንስቶ እስከ ህልፈቱ ማግስት፣ ሕይወትና ሥራዎቹን የሚመለከቱ አያሌ ዘገባዎች በመገናኛ ብዙሀን ቀርበዋል በ2002 የህልፈቱ 1ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት ደግሞ ጥላሁን ገሠሠ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉስ የሚል ርዕስ ያለው መፅሐፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ ነገር ግን በዚህ መፅሐፍ ውስጥ የምናነበው የጥላሁንን የሕይወት ታሪክ እና ርዕሱ ከተጠቀሰው መፅሐፍ መሆኑ ከዚህ ቀደም ሲል በመገናኛ ብዙሀን ሲተረክ የኖረው የጥላሁን ሕይወት ታሪክ በመሠረታዊ ሀቅ ደረጃ ለየቅል ናቸው፡፡ ጥላሁን ገሠሠ የህይወቱ ታሪክ እና ሚስጢር የተሰኘውን ይህን መፅሐፍ የወለደው ከዚህ ልዩነት ጀርባ ባለው በጥላሁን ህይወት እና በስብዕናው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳደረ በምንም አጋጣሚ ያልተነገረ ቤተሰባዊ ክስተት ነው፡፡
ባለፉት 50 ዓመታት ስናነብና ስንሰማ የኖርነው የጥላሁን የትውልድ፣ የልጅነትና የቤተሰቡ ታሪክ ጥላሁን እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ድረስ ሚስጥር አደድጎ የያዘው የልጅነት ዘመን ቤተሰባዊ ጠባሳ የወለደው የተቀየረ ታሪክ ነው፡፡ ይህ መፅሐፍ በጥላሁን የሕይወት ታሪክ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ ሀቆች እንዴትና ለምን እንደተቀየሩ፣ እንዲሁም በጥላሁን ስብዕና ላይ ያሳደረው አንድምታ ምን እንደሚመስል ይተርካል፣ ይተነትናል፡፡›› ይላል፡፡
ዘከርያ መጽሐፉን ለማዘጋጀት የተነሳበትን አላማ ሲገልጽም፡- ‹‹ የተዛቡ ታሪኮችን ማስተካከልና የተዛቡ እይታዎችንና ግንዛቤዎችን ማስተካከል፣ ሰውዬውን መረዳት፣ ከሱ ህይወት መማር እንድንችል ነው፡፡ ለኛም እኮ ይጠቅመናል የሱ ህይወት ምን አይነት ምስቅልቅል ውስጥ እንደነበር እናያለን፡፡ እኔ ጥላሁን ገሰሰ ዝም ብሎ ተረት እንዲሆን አልፈልግም፡፡ ማንም የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ ጥላሁን የተለያየ ሰው በሚያነሳው ብጥስጣሽ አሉባልታ መካከል እንዲቆም አልፈልግም፤ ይሄ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ምን አይነት ስብዕና ነበረው፤ ከህዝቡ ጋር ምን አይነት መቀራረብ ነበረው፤ የልጅነት ህይወቱ ምንድነው የሚሉትን ነገሮች መለስ ብለን ብናውቅ እንማርበታለን፤ እንጠቀምበታለን፤ እሱንም ደግሞ ከተዛቡ ግንዛቤዎች እናጠራዋለን፡፡››ይለናል፡፡

ጥላሁን በህይወት ዘመኑ የደበቀን የግል ምስጢሮች እንዳሉትም ዘከርያ ይናገራል፡- ‹‹ እኛም አላወቅንለትም እሱም ደብቆናል፡፡ ሁለቱም ነው የሚባለው እሱ ስለደበቀን ነው እኮ እኛም ያላወቅነው፡፡ ነገር ግን ስለደበቀንና ሌላ ታሪክ ስለነገረን ውሸታም ነው ልንለው አንችልም፡፡ በርግጥ ውሸት ነው፡፡ ግን ለህልውናው ሲል እራሱን ለማቆየት ሲል ስሜቱን ለማጠገግ ሲል በሰቀቀን ላለመሞት ሲል አንድ ሰው ይዋሻል፡፡ ይሄ የሁላችንም ጉዳይ ነው ይሄ መፅሐፍ እኮ የጥላሁንን ታሪክ ለመናገር የወጣም አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎችን ያክማል ብዬ አስባለሁ እኔ፡፡ ጥላሁን ያደረገውን ማድረግ ጉዳትም ጥቅምም ይኖረዋል፡፡ ወደኋላ ያሉ መጥፎ ትውስታዎችን እንሸሻቸዋለን፤ ማስታወስ አንፈልግም፤ ስለዚህ ከዚያ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ማውራት ካለብን ከዚያ ሸሽተን ሌላ ታሪክ ጨምረንበት እንናገራለን፡፡ ጥላሁን ዝነኛ ባይሆን ኖሮ እኮ ሁሉም ሰላም ይሆን ነበር፡፡ ዝነኛ የሆነውም ያንን ታሪክ በመሸሹ ነው፡፡ ጥቅምም ጉዳትም ነበረው፡፡ ጥላሁን ደስተኛ ሰው አልነበረም፤ ለራሱ ሆኖ አይደለም የኖረው፡፡ እነዚያ የሚጎዱት ነገሮች ደግሞ በቀላሉ የሚታረቁት አይደሉም፡፡ እና ለምን ለህዝብ ያንን ታሪኩን አልተናገረም ልል አልችልም፡፡ ግን ስነልቦናውን ጎድቶታል፡፡ የተረጋጋ የትዳር ሕይወት እንዳይኖው አድርጎታል፡፡ የሆነ አቅሙን ነስቶታል፡፡ የሚፈጠሩ አደጋዎችን የመጋፈጥ አቅሙን ሸርሽሮታል፤ በዚህ ምክንያት ቤተሰቡ ይፈርሳል፡፡ ምክንያት አለው ሰዎች እንዲረዱት እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ለምሳሌ ጥላሁን ብዙ ስለማግባቱ አንስተው በመጥፎ ሁኔታ የሚተረጉሙት አሉ፡፡ ለምንድነው ብለው ግን አይጠይቁም፡፡ ዝም ብለው ‹አለሌነት› አድርገው ይወስዱታል፡፡ አይደለም / ላይሆን ይችላል፡፡ መጀመሪያ ለምንድ ነው ብለን ጠይቀን ትክክለኛውን ነገር መረዳት አለብን››

Source: ቁም ነገር ቅጽ 13 ቁጥር 201 ሚያዝያ 2007

The post የምስጢራዊው ድምፃዊ ‹አዳዲስ› ምስጢሮች appeared first on Zehabesha Amharic.

የተጨናገፈው፤የዕልቂት ድግስ – (ሚያዚያ 30ን ከስፍራው) –በደረጀ ሀብተወልድ፤ኢሳት

0
0

dereje

በጎቹ ጨፌው ላይ – በፍቅር ያዜማሉ፣
ተኩሎች አድፍጠው – ይጠባበቃሉ፣
ጩኸት ሊበረክት-ሊፈስ ሲል ዕንባ፣
እረኛው በድንገት-መሀል ጣልቃ ገባ።
አገር በደም ባህር-ሊጠመቅ ተፈርዶ፣
ውሀ ጥምቀት ሆነ-ከላይ ዝናም ወርዶ።

ቅንጅት፤ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ የጠራውን የሚያዚያ 30/1997 ዓ.ም ሰልፍ ለመዘገብ ወደ መስቀል አደባባይ ያመራሁት እኩለ-ቀን ላይ ነው። ከረፋዱ 4 ፡00 ሰ ዐት ጀምሮ ታክሲዎች መደበኛ ሥራቸውን ትተው ሰዎችን በነፃ ወደ መስቀል አደባባይ ማመላለስ በመጀመራቸው፤ሰልፉ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል መገመቱ ቀላል ነበር።ቀድሜ ወደ ሥፍራው የተንቀሳቀስኩትም፤ ማለፊያ መንገድ ሳይዘጋጋ ወደ አደባባዩ ለመቅረብ እንድችል ነው።እንደወትሮው ሁሉ ዛሬም መቅረፀ-ድምፄንና ካሜራዬን አንግቤያለሁ። የወቅቱ ሀዳር ቀጥሎም የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጅንግ ኤዲተር የነበረው ዳዊት ከበደ፤ እንዲሁም የሀዳር ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበረው ፈለቀ ጥበቡ አብረውኝ አሉ።

የሰው ጎርፍ ከየአቅጣጫው እየተግተለተለ ወደ አንድ ሥፍራ ተከማችቶ እንደ ረጋ ውቅያኖስ ሆነ።ዳርቻው የማይደረስበት ውቅያኖስ።
መለስ፤ ከአንድ ቀን በፊት ያዩትን የኢህአዴግ ሰልፍ በማድነቅ “ማዕበል” ብለው መጥራታቸውን ያስታወሰው ሪፖርተር ጋዜጣ ፤ከቅንጅት ሰልፍ በሁዋላ ባወጣው ርዕሰ-አንቀጽ ” ለማዕበልም፤ ማዕበል አለው” በማለት ነበር ለመለስ ንግግር ምላሽ የሰጣቸው።
የማዕበሎች ሁሉ ማዕበል።
ምኒልክ ጋዜጣ ደግሞ፦”ሱናሚ”ሲል ነው የጠራው።
የሚገርም ቀን።

ሚያዚያ 30/ 97፦ በኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታዬ ህልም ሚመስል ትዕይንት።ሚሊዮኖች ነፃነታቸውን በአደባባይ በማወጅ ዲሞክራሲን በጋራ የዘመሩበት ታሪካዊ ቀን።
ሆኖም፤
የሰልፉ አስተባባሪዎች ለዕለቱ የተሰናዳውን ፕሮግራም ለማቅረብ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ፈፅሞ ያልተጠበቀ ነገር ሆነ-መብራት ጠፋ። በወቅቱ ተቀርፎ የነበረው የአዲስ አበባ የመብራት ችግር፤ ከረዥም ወራት በሁዋላ የቅንጅት ሰልፍ ፕሮግራም ሊጀመር ደቂቃዎች ሲቀሩት እንደ አዲስ ተቋረጠ።
እንደ ትናንት የኢህአዴግን ሰልፍ በተንቦገቦገ መብራት ያስተናገደው አደባባይ፤ዛሬ ሚሊዮኖች ለወጡበት ሰልፍ ብርሀኑን ነፈገ።
በተደጋጋሚ ወደ መብራት ሀይል ባለሥልጣን ስልክ በመደወል የተደረገው ጥረትም ሳይሳካ ቀረ።
ጥቂት ሰዎች- ዕልፎችን፦“የጀኔሬተሩ ቁልፍ በእኛ እጅ እሰከሆነ ድረስ ብርሀን እንድታዩ አንፈቅድላችሁም” አሏቸው።
በሆነው ነገር ህዝቡ ተቆጣ። ከዳር እስከ ዳር የተቃውሞ ጩኸት ማሰማት ጀመረ።
የህዝቡ ቁጣ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን የሰጉ የቅንጅት አመራሮችም ፤ የእጅ ማይክራፎን ይዘው በሰልፉ መሀል በመዟዟር ‘ከመብራት መቋረጥ ጀምሮ ሆነ ተብለው እየተፈፀሙ ያሉትን ማናቸውንም የሚያበሳጩ ድርጊቶች ህዝቡ በትዕግስት እንዲያልፋቸው’ በአደራ ጭምር ተማፀኑ።
“…እነሱ የፈለጉት በብስጭት ወደ ህገ-ወጥ ድርጊት እንድንገባ ነው።እያመቻቹን ያሉት የሀይል እርምጃ ለመውሰድ ነው።ንቁባቸው! እንኳን መብራት ማጥፋት ሌላም ነገር ቢፈጽሙ ከህጋዊና ሰላማዊ መስመራችን የማንነቃነቅ የዲሞክራሲ ሰልፈኞች መሆናችንን እንድናሳያቸው፤ ደግመን ደጋግመን አደራ እንላለን!!”
ህዝቡ የመሪዎቹን ጥሪ ተቀብሎ የሚሆነውን ነገር በትዕግስት መጠባበቅ ጀመረ።
በላዩ፤አናት የሚበሳው የፀሀይ ቃጠሎ አለ።

ግን…ግን…

ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የተሰባሰቡበት ዝግጅት ሊጀመር ፤ደቂቃዎች ሢቀሩ ሆነ ተብሎ መብራት እንዲጠፋ የተደረገው ለምን ይሆን? ?
አንዳፍታ ከእኛ ጋር በሰልፉ መሀል እየተሻሻችሁና እየተገፋፋችሁ ወደ መድረኩ እንድንሄድ ላስቸግራችሁ…
በግምት፤ መድረኩን በ20 ሜትር ርቀት እስከከበበው አጥር ድረስ ከመጣችሁ ይበቃችሁዋል።በቃ! ከዚህ በሁዋላ ማለፍ አትችሉም። ከመንግስት ጋዜጠኞች በስተቀር ማንም ወደ መድረኩ እንዲወጣ አልተፈቀደም።እዛው ቆማችሁ በመድረኩ ጀርባ ስላለው ነገር የምነግራችሁን አዳምጡ።

እኔና ጓደኞቼ ከመድረኩ ሆነን የታሪካዊውን ሰልፍ ፎቶ ለማስቀረት ስለፈለግን ወደ ሰባት ከሚደርሱት የኢቲቪ፣የኢትዮጵያ ራዲዮ እና የራዲዮ ፋና ጋዜጠኞች ጋር በመቀላቀል የተከለለውን አጥር አልፈን ወደ ፊት መራመድ ጀመርን።
ከፊት እየመራ ጋዝይጠኞቹን ወደተዘጋጀላቸው ቦታ የሚወስዳቸው ሰውዬ፤ የግል ፕሬስ ጋዜጠኞች ይቀላቀላሉ ብሎ ስላልገመተ ያለምንም ጥያቄ “ተከተሉኝ”እያለ ወደ ፊት ወሰደን። የሰልፍ መስመር እንደያዝን በኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የሰላምና የልማት ኢንስቲትዩት ጓሮ በኩል ገባን።
እንዴ!?
ምንድነው የሚታየው ጉድ!?
ዐይኔን ማመን አልቻልኩም።
ሁላችንም በድንጋጤ እርስ በእርስ ተያዬን።
ከመድረኩ ጀርባ ዙሪያውን በአጥር በተከለለና እንደ ምድር ቤት ዝቅ ባለ ቦታ ላይ በስድስት ከባድ መኪናዎች ላይ የሠፈሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች መትረየሶችንና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ወደ ህዝቡ ደግነው በተጠንቀቅ ይጠባበቃሉ።
አገር ሰላም ብለው መስኩ ላይ በደስታ የሚዘምሩት በጎች እነዚህን ያደፈጡ ነጣቂዎች አላዩዋቸውም።አዎ! እንደኛ ወደ ውስጥ ያልገባ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሊያያቸው አይችልም።

በግዮን ሆቴል ጀርባ በኩል የታችኛውን ቤተ-መንግስትና የመስቀል አደባባይን መድረክ የሚያገኛኝ ልዩ መንገድ እንዳለ በዐይኔ ያየሁት የዛን ዕለት ነው።መንግስቱ ሀይለማርያም መስቀል አደባባይ ንግግር ለማድረግ ይመጡ የነበረው በዛ ስውር መንገድ እንደሆነ ይወራል።ነገሩ እንደነ መለስ መንገዱን ጭር በማድረግ አገር ምድሩን ከማሸበር -ይህን ስውር መንገድ መጠቀሙ ይመረጣል ።
ዛሬም በመድረኩ ጀርባ አድፍጠው የሚጠባበቁት ታጣቂዎች ይህን መንገድ ሳይጠቀሙ አልቀሩም ብዬ እገምታለሁ።ያ ካልሆነ፤ ከአንድ ቀን በፊት- ልክ የኢህአዴግ ሰልፍ እንዳበቃ እዛው ቦታ ላይ ሆነው ሌሊቱን ሙሉ ሢጠባበቁ አድረዋል ማለት ነው።
መድረኩ ጫፍ ወጥተን ሥራችንን ጀመርን። የካሜራችንን “ዙም” እያስረዘምንና እያሳጠርን ልዩ ልዩ ትዕይንቶችን ማስቀረቱን ተያያዝነው።

ባንዲራ ተጎናጽፈው ዕልልታ የሚያሰሙ አዛውንቶች፣ በገላቸው ላይ የቅንጅትን አርማ የተነቀሱ ወጣቶች፣”ትናንት ለገንዘብ፤ዛሬ ለነፃነት”እያሉ መፈክር የሚያሰሙ ሴቶች፣ በወላጆቻቸው ትከሻ ላይ ሆነው ሁለት ጣታቸውን የሚያሳዩ ህፃናት፣”ይትባረክ እንደ አብርሐም!”እያሉ የሚዘምሩ የሰንበት ተማሪዎች፣ “አላህ ወአክበር!” የሚሉ መድረሳዎች፣”ኢየሱስ ጌታ ነው!”እያሉ የሚጮኹ ጴንጤዎች…ማን ነበር የቀረው?
እኚህ ሁሉ፤ በፍቅር ተያይዘው፣በአንድ ልብና በአንድ ሀሳብ ሆነው ዲሞክራሲን እያወደሱ ነው።ሥርዓትና ህግን በጠበቀና ሥልጡን በሆነ መንገድ።

“ሟርት በያዕቆብ ላይ አይሠራም!” ነው የሚለው ታላቁ መፅሐፍ?
አዎ! ኢትዮጵያውያን በአንድ አገራዊ አስተሣሰብ እንዳይቆሙ ለዓመታት ሢቀመም የቆየው የዘርና የሀይማኖት ሥራይ፤ውሀ እንደነካው የደብተራ ክታብ ፈስዶ ታዬ።
ዕልፎች፦
“የሀይማኖት ካብ- ብትክቡ፣
የዘር ገመድ -ብትስቡ፣
ደከማችሁ እንጂ- በከንቱ፣
እኛ ያው ነን-እንደ ጥንቱ፣
እኛ አንድ ነን-እንደ ፊቱ”
እያሉ ተቃቅፈው በዕልልታ ሲዘምሩ ተስተዋሉ።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ካሜራ ፤ ለዜና እንኳ የሚሆን ምስል አላገኘም መሰል፤ ገና ሥራ አልጀመረም።መድረኩ ላይ ካሉት በተጨማሪ ፤ለኢቲቪ ምሽት ዜና የሚሆን ትዕይንት የሚፈልጉ ሌሎች ጋዜጠኞችም በሰልፉ መሀከል ካሜራ ይዘው ተሰማርተዋል።ግን እንደታዘዙት፣እንዳሰቡትና እንደተመኙት ረብሻዎችንና ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ማግኘት አልቻሉም።
አሁን ግን ሰልፉ መካከል ላይ የሚሰማን ለየት ያለ ጩኸት ተከትለው ከተለያየ አቅጣጫ ካሜራቸውን ወደ መካከል ማነጣጠር ጀመሩ።
ከጀርባ ያደፈጡት ተኩላዎችም፤ ከአንገታቸው ቀጥ ብለውና ጆሯቸውን ቀስረው በተጠንቀቅ ሆኑ።
“በለው! በለው! በለው!…”
“እንዳትነኩት! እንዳትነኩት! እንዳትነኩት!”
የሚሉ ጩኸቶች ከወደመሀል እያስተጋቡ ነው።
ምክንያቱ ምን ይሆን?
በግምት ከ16 ዓመት የማይበልጠው ታዳጊ ህፃን የንብን(የኢህአዴግን) ቲ-ሸርት ለብሶ፤ በዛ የሚሊዮኖች ሰልፍ መሀከል መገኘቱ ነው።
እስኪ አስቡት፤ በዛ ማዕበል፣ በዛ ስሜትና ትርምስ መሀከል(የሰልፉ እንብርት ላይ) የንብን ቲሸርት የለበሰ ሰው፤ያውም ታዳጊ ህፃን! ለእርድ እየተነዳ የመጣ ንፁህ በግ!

ልጁ፤ የንብን ቲ-ሸርት ለብሶ እንዴት ቅንጅት ሰልፍ መሀል ሊገኝ እንደቻለ በአስተባባሪዎቹ ለቀረበለት ጥያቄ፤ ሰዎች፤ ቲ-ሸርቱን አልብሰውና ከላይ ጃኬቱን እንዲደርብ አድርገው እስከመሀከል ድረስ ካመጡት በሁዋላ፤”እንዳይሞቅህ” በማለት ጃኬቱን አውልቀው እንደያዙለት መጠፋፋታቸውን በማብራራት፤ ስለ ፖለቲካ ምንም ግንዛቤ የሌለው መሆኑን ይናገራል። ሆኖም፤ “እነዛ ሰዎች ማናቸው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀራል።
በዚህ ጊዜ ነው፦”በለው! በለው! ካልተናገረ በለው!…..” የሚል ድምፅ በዙሪያው ከነበሩ ወጣቶች የተሰማው። ሆኖም፦” እንዳትነኩት!” የሚለው ድምፅ በእጥፍ ብልጫ ነበረው።

”እንደውም፤ እሱን አውልቁለትና የቅንጅትን ቲ-ሸርት አልብሱት” የሚሉ ወጣቶች ተሰሙ። ሀሳባቸው የጭብጨባ ድጋፍ አገኘ። ልጁ ሲጠየቅም ፈቃደኛ ሆነ።ስማቸውን ያልጠቀሳቸው ሰዎች አልብሰው የላኩትን የጽልመት ግርዶሽ አውጥቶ በመወርወር ልቡ የፈቀደውን ለበሰ።ጭብጨባው ቀለጠ።ተንኮለኞች ይገደል ዘንድ ፈረዱበት።እግዚአብሔር ግን “አትሞትም፤ገና በህይወት ትኖራለህ!” አለው።
ተቀጥቅጦ ይገደል ዘንድ የተላከው ታዳጊ፤ከወገኖቹ ጋር ተቃቅፎ መዘመር ቀጠለ።
አዎ! የመጀመሪያው የተንኮል ድር በዚህ ሁኔታ ተበጣጠሰ።ህፃን ልጅ ቲ-ሸርት አልብሶ ሰልፈኛ መሀል ላይ በመጣል፤ በሱ ጉዳት ምናልባትም፦ በሞቱ ለመነገድ የተወጠነው ሴራ ከሸፈ። ቀጥ ብሎ የነበረው የተኩላዎቹ ጆሮ ረገበ።
”በቅንጅት አመራሮች አደገኛ ፕሮፓጋንዳ የተለከፉ ጥቂት ቦዘኔዎች ለምን የንብ ቲሸርት ለበስክ? በማለት የ 13 ዓመት ታዳጊ ወጣትን ደብድበው ገደሉ” ተብሎ ከወዲሁ ለምሽት የተዘጋጀው የኢቲቪ ዜና ውድቅ ሆነ። ህዝቡ “ነቄ ነን” አለ።
አሁን፤ ከቀኑ 8፡30 ሊሆን ነው።እስካሁን የተቋረጠው መብራት አልመጣም። ዕልልታውና ዝማሬው ግን ከጫፍ ጫፍ እያስተጋባ እንደቀጠለ ነው።ልደቱ አያሌው በአንገቱ ላይ የባንዲራ ስካርቭ አድርጎና በሰዎች ትከሻ ላይ ሆኖ ድንገት ብቅ አለ።
“ማንዴላ! ማንዴላ!ማንዴላ!…..” በማለት ህዝቡ በሆታ ተቀበለው።
ህዝቡ ለሰልፉ የተዘጋጀውን የመሪዎቹን ንግግር በመብራት መቋረጥ ምክንያት ለመስማት ባለመቻሉ፤ ብስጭቱ እየጨመረ መምጣቱን የተገነዘበው ልደቱም፤ሰልፈኞቹ በኤሌክትሪክ ሀይል አለመምጣት ሳቢያ ወዳልሆነ እርምጃ እንዳይገቡ ደጋግሞ ተማፀነ።
ሰዐታት ነጎዱ።

9፡00፣ 9፡30፣ 10፡00፣10፡15…..
የመድረኩ ዝግጅት በመብራት አለመኖር ሳቢያ መቅረቱ ተነገረ።ህዝቡ ዳግም ቁጣ ማሰማት ጀመረ።የመብራቱ ነገር፦”አውቆ የኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም”እንደሆነ በደንብ ገባው።”ካሁን አሁን ይመጣል”የሚለው ተስፋው ጨርሶ ተሟጠጠ።
አዲስ አበባ በጩኸትና በፉጨት ተናጠች።በእስጢፋኖስ ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ ካሉት ወጣቶች ፦
”ኢህአዴግ ሌባ!
አል-አሙዲ ሌባ!” የሚል ቁጭትና ንዴት የወለደው ጭፈራ ተሰማ።
ሦስት ሚሊየን ህዝቦች ለሦስት ሰዐታት መብራት ሲከለከሉ የሚፈጥረውን ስሜት በሰልፉ የነበራችሁ ታውቁታላችሁ፤ ያልነበራችሁም ትረዱታላችሁ።
ስለዚህም ወጣቶቹ ንዴታቸውን መግለጽ ጀመሩ።አደባባዩ በውጥረት ተሞላ።ሲቪል የለበሱ ሁለት ሰዎች በመገናኛ ሬዲዮ መልዕክት እየተቀበሉ ከመድረኩ ጀርባ ላሉት አጋዚዎች የሆነ ነገር ነገሯቸው።መሳሪያቸውን አንቀጫቀጩ። እጃቸውን ወደ ቃታ በመላክ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ሆኑ፡፡እርግጠኛ ነኝ፤ እየጠበቁ ያለው፦”ቀጥል!” የሚለውን ትዕዛዝ ብቻ ነው።
ሁኔታውን እያየን ያለነው ጋዜጠኞች የበለጠ ድንጋጤና ጭንቀት ውስጥ ገብተናል።
በወጣቶቹ የተጀመረው የተቃውሞ ጩኸት ዳር እስከ ዳር መቀጣጠል ጀመረ። ተኩላዎቹ ካደፈጡበት በመነሳት ወደ መድረኩ መውጫ በር ተንቀሳቀሱ።የሰልፉ አስተባባሪዎች መረጃ ደረሳቸው መሰል
፦”እባካችሁ ሰልፈኞች አደራ! ምንም ነገር እንዳታደርጉ! አደራ!አዳራ!…’እያሉ እንደ አዲስ አብዝተው መጮኽ ጀመሩ። ህዝቡ ግን፦” የአገራችንን ብርሀን የሚነፍገን ማነው?” እያለ መጠየቁን ቀጠለ።
“ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም፣
እናት ኢትዮጵያ-የደፈረሽ ይውደም!” የሚል ዝማሬ ተከተለ-በምልዓተ-ሰልፉ።

አስጨናቂ ሰዐት።

“አዲስ አበባ በደም ልትታጠብ ነው” የሚል የባህታዊ ትንቢት የሰማሁት፤ ኢህአዴግ ከተማዋን ለመያዝ በተቃረበበት ጊዜ ነበር።ለነገሩ፤ያኔ በመዲናዋ ውስጥ ሰፍረው ከነበሩት የቀድሞ ሥርዓት ወታደሮች ብዛት አኳያ፤ ” የአዲስ አበባ መሬት በደም ይታጠባል” ብሎ ለመናገር የነቢይነት ቅባት የሚጠይቅ አልነበረም።ለዚህም ነው ከባህታውያኑ ባሻገርም የፖለቲካ ተንታኞችም ፦’ስለ አዲስ አበባ የደም ጎርፍ’ ለመተንተን አፋቸው ያልተሳሰረው።
ትዝ ይለኛል፤ ህዝቡ በየአብያተ-ክርስቲያናቱና በየመስጊዱ በመሄድ ፦”አድህነነ ከመዓቱ ሰውረነ!” እያለ ከጧት እስከ ማታ ወደ ፈጣሪው ሲያለቅስ።

እግዚአብሔር ይመስገን!

በወጀብና በአውሎ ነፋስ መካከል መንገድ ያለው ጌታ ፤ትንቢቱንም፤ትንታኔውንም ሽሮ ከዛ አስጨናቂ ሰዐት ህዝቡን በሰላም አሳለፈው።
ዛሬስ ፤ ከዚህች አስጨናቂ ሰዐት እኚህን በጎች የሚታደጋቸው ማን ነው?ዛሬስ ከደቂቃዎች በሁዋላ በመስቀል አደባባይ ሊፈስ ያለውን የደም ጎርፍ ፤ማን ያቆመው ይሆን?
ማንም!
ተስፋ ቆረጥኩ።
አዎ!ስትዘምር የዋለችው ከተማ ማምሻዋን በዋይታ ልትሞላ ነው።”አኬልዳማ- የደም ምድር..”የሚለው የታምራት ዝማሬ ጆሮየ ላይ ደጋግሞ እያንቃጨለ ነው።
የህዝቡ ጩኸት እጅግ በረታ… አስተባባሪዎቹ ፦”ሰልፉ ስለተጠናቀቀ ወደየቤታችሁ ሂዱ!” ቢሉም ፤ህዝቡ እምቢ አለ። ተኩላዎቹ ፤ ከባለ ሬዲዮ መገናኛዎቹ የመጨረሻውን መልዕክት ተቀበሉ መሰል መሳሪያቸውን እንዳቀባበሉና እጃቸውን ቃታ ላይ እንዳደረጉ ከመኪናቸው በመውረድ ፈጠን ባለ እርምጃ ወደ ግቢው መውጫ በር ሄደው አደፈጡ።አስቀያሚው ትዕይንት ሊጀመር ትቂት ሰከንዶች ቀሩ….አንድ..ሁለ…ት….ሦ…ስ…..
ኦ!
ይህን ማን ያምናል?
በዛ ጠራራ ፀሀይ ዶፍ የቀላቀለ ሀይለኛ ዝናም በድንገት ወረደ።በአስተባባሪዎቹ ተማጽኖ አልነቃነቅ ያለው ሰልፈኛ በራሱ ጊዜ እየተሯሯጠ ተበታተነ።ገሚሱ በየቦታው ሲጠለል፤የተቀረው ዝናሙን ተቋቁሞ ወደ ቤቱ ገሰገሰ።ሰልፉ በዚህ መልክ በሰላም ተጠናቀቀ።
የተወጠነው የዕልቂት ድግስ ተጨናገፈ።
የዛን ቀን ምሽት ፦ “ወጥመድ ተሰበረ-እኛም አመለጥን፤ ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን እግዚአብሔር ይመስገን!” የሚለውን የዳዊት መዝሙር ደጋግሜ ማንበቤን አስታውሳለሁ።
በሆነው ነገር የተደነቁት ዶክተር ብርሀኑ ነጋ ከጊዜያት በኋላ ይህን ነገር አስታውሰው፦“ኢትዮጵያን የሚጠብቃት አምላክ አላት የሚባለውን ነገር ያስተዋልኩት ያንጊዜ ነው” ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ።
እኛም ከሞት አመለጥን-የ’ሱም እቅድ አልተሳካ፣
የደበደበን ዶፍ ዝናም- ከሞት ሊያድነን ነው ለካ። (ለበጎ ነው ከሚለው የራሴ ግጥም)

The post የተጨናገፈው፤የዕልቂት ድግስ – (ሚያዚያ 30ን ከስፍራው) – በደረጀ ሀብተወልድ፤ኢሳት appeared first on Zehabesha Amharic.

አሰፋ ማሩ –ልክ የዛሬ 8 ዓመት ወደ ቤቱ ሊገባ ሲል በወያኔ ተረሽኖ ሕይወቱ አለፈ

0
0

ልክ የዛሬ 18 ዓመት ሚያዝያ 30 ቀን 1989 ዓ.ም አቶ አሰፋ ማሩ ወደ ቤቱ ሊገባ ሲል በወያኔ ተረሽኖ ሕይወቱ አለፈ
የኢመማ ጀግኖች ሰማእታትን እናስብ።
asefa maru
የዛሬ 18 ዓመት ሚያዚያ 30 ቀን 1989 ዓ.ም አቶ አስፋ ማሩ ከቤቱ በሰላም ወጥቶ ወደ ሥራ በመሔድ ላይ እያለ በአዲስ አበባ ሐምሌ19 የሕዝብ መነፈሸ አካባቢ በጠራራ ጸሐይ በወያኔ/ኢህአዴግ ነፍሰ ገዳይ ፖሊሶች የጥይት እሩምታ ሰለባ የሆነ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነው።

አቶ አሰፋ ማሩ በጊዜው በወሎ ክፍለሀገር በላስታ አውራጃ መቄት ወረዳ በ1951ዓ.ም ተወለደ። በመምህርነት ሙያ ከማገልገሉም ባሻገር በሙያ ማህበሩ የአመራር አባል በመሆንም የመምህራንን መብትና ጥቅም ለማስከበር ፣ የትምህርቱን ጥራት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል በግምባር ቀደምትነት ከሚታገሉት አንዱ ሆኖ ሕይወቱ በግፈኞች እስካለፈበት ዕለት በጽናት ቆሞ ቆይቷል። በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤም በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የላቀ ድርሻ አበርክቷል።

The post አሰፋ ማሩ – ልክ የዛሬ 8 ዓመት ወደ ቤቱ ሊገባ ሲል በወያኔ ተረሽኖ ሕይወቱ አለፈ appeared first on Zehabesha Amharic.

ዲ ማሪያ –ከሮሳሪዮ እስከ ዩናይትድ

0
0

አንሄልዲ ማሪያ ወደ እግርኳስ የመጣው በአጋጣሚ ነው፡፡ ተጨዋቹ በልጅነቱ ቅዥቅዝ ያለ ነበር፡፡ ይህ ያሳሰባቸው ቤተሰቦቹ ወደ ሐኪም ቤት ወሰዱት፡፡ ዶክተሮቹ ልጃቸው ላለበት ችግር መፍትሄው እንቅስቃሴ የሚያደርግበትን መፍጠር መሆኑን ለቤተሰቦቹ አስረዷቸው፡፡ አል ቶሪቶን የተቀላቀለው ያን ጊዜ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚናገሩት ሮሳሪዮ ሴንትራል የስድስት ዓመቱን ተጨዋች በመውሰድ ጥያቄ ሲያቀርብ ኤል ቶሪቶ ለዝውውሩ እውን መሆን በምላሹ የጠየቀው 26 ኳሶችን ብቻ ነበር፡፡ የሚያስገርመው በ1974 የዓለም ዋንጫ ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገውን የሆላንድ ብሔራዊ ቡድን ለመዘከር ብርትኳናማ ማሊያ የሚለብሰው ኤል ቶሪቶ የጠየቃቸውን ኳሶች እንኳን ያልተቀበለ መሆኑ ነው፡፡
di maria Man united

ለዲ ማሪያ ዝውውር የወጣው ገንዘብ ጉዳይ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ዝውውሮች በአርጀንቲና እግርኳስ በየትኛውም እርከን ላሉ ቡድኖች የህልውና መሰረት ናቸው፡፡ ዲ ማሪያ ከቤንፊካ ወደ ሪያል ማድሪድ እንደዚሁም የብሪታኒያ ሪከርድ በሆነ ዋጋ ከማድሪድ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ያደረገው ዝውወር ለሮሳሪዮ ሴንትራል ጥሩ የገቢ ምንጭ ሆኖለታል፡፡ በስምምነታቸው መሰረት ዲ ማሪያ ከሚያደርጋቸው ዝውውሮች 2% የሚሆነውን ገንዘብ ለአርጀንቲናዊው ክለብ ገቢ ይሆናል፡፡ በ1978 የዓለም ዋንጫን ወዳስተናገደው ስታዲየም የሚገባው ገንዘብ ከዚህም በላይ ሊሆን የሚችልበትን አጋጣሚ ያልተጠቀመበት ክለብ ራሱ ነው፡፡ ተጫዋቹ ወደ ቤንፊካ ሲያመራ ሴንትራል 20% የዝውውር መብት ነበረው፡፡ በኋላ ላይ ግን ቤንፊካ የተወሰነ ገንዘብ ከፍሎ የዝውውር መብቱ እንዲያንስ አደረገ፡፡

‹‹ለሁሉም ተጨዋቾች ወደ አውሮፓ መጓዝ ህልም እንደሆነው ሁሉ እኔም ወደ ሴንትራ የመመለስ ህልም አለኝ›› ሲል ዲ ማሪያ ሴፕቴምበር ላይ ተናግሯል፡፡ አብዛኞቹ አርጀንቲናውያን ተጨዋቾች መነሻቸውን አይዘነጉም፡፡ በአውሮፓ መድረክ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እንዲችሉ መንደርደሪያ የሆነችውን ክለብ ተመልሰው የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ ዲ ማሪያ በአንድ ወቅት ከሜሲ ጋር እንዲቀራረቡ ያደረጋቸው በአንድ ከተማ ማደጋቸው እንደሆነ ሲጠየቅ ‹‹እንደዚያ ለማለት እንኳን አልችልም፡፡ ሜሲ ኔዋልስ እኔ ደግሞ ሴንትራል ነኝ›› በማለት ሮሳሪዮን ለሁለት የከፈላትን የእግርኳስ ባላንጣነት ያስታውሳል፡፡
ዲ ማሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለሮሳሪዮ ሴንትራል ያከናወነው በ17 ዓመቱ ነው፡፡ በወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ የነበሩት በክለቡ ጋር ሶስት ዋንጫዎችን ያነሱት እና በኖቬምበር 2014 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አንሄል ዞፍ ነበሩ፡፡ ዲ ማሪያ ለሴንትራል ዋናው ቡድን የተጫወተው ለሁለት ዓታት ብቻ ነው፡፡ ያ የሆነው ክለቡ ታዳጊን በጥሩ የዝውውር ዋጋ ለመሸጥ በመፈለጉ ነው፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ ከ40 ያነሱ ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈ ሲሆን ከስድስትየተለያዩ አሰልጣኞች ጋር ሰርቷል፡፡ በሮሳሪዮ ሳለ የተወሰኑ የአካባቢው ጋዜጣዎች ፕሴይሜከር ብለው ገልፀውት ነበር፡፡ ነገር ግን ቀጥተኛ አጨዋወቱ እና ፍጥነቱ በመስመር ለማጥቃት የተመቸ ነበር፡፡ ቤንፊካም ክለቡን ለቅቆ የሄደው ሺማኦ ምትክ አደረገው፡፡

ዲ ማሪያ ቤንፊክ የደረሰው የሊዝበኑ ክለብ አለመረጋጋት ውስጥ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ በ2007 የፖርቹጋሉን ቡድን ሲቀላቀል ዝውውሩ ወደ አውሮፓ ታላላቅ ክለቦች በሚያደርገው ጉዞ መሸጋገሪያ መሆኑን ገልጿል፡፡ በአስተያየቱ የቤንፊካ ታማኝ ደጋፊዎች መጠነኛ ቅሬታ ተሰምቷቸዋል፡፡ ነገር ግን ንግግሩ የታዳጊውን ወሳኝ ሰብዕና የሚገልጽ ነበር፡፡ በተሰጥኦው እንደሚተማመን ጠቋሚ ነበር፡፡ መጀመሪያ አካባቢ አጨዋወቱን ለመግለፅ ተቸግሮ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ የድንቅ ብቃት ባለቤት መሆኑን የሚጠቁሙ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ የዘለለ ተፅዕኖ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን ሆርጌ ጂለስ የቤንፊካ አሰልጣኝ ሆነው ሲሾሙ ሁሉም ነገር ተለዋወጠ፡፡ ‹‹በእኔ ላይ ከልቡ እምነት የጣለ የመጀመሪያው አሰልጣኝ ጃሰስ ነበር›› በማለት ዲ ማሪያ በኋላ ላይ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ አሰልጣኙም ቢሆኑ በአርጀንቲናዊው ላይ ያሳዩት አቋም ተገቢውን ዋጋ አስገኝቶላቸዋል፡፡

በ2010 ቤንፊካ በሚያስደንቅ ብቃት ወደ ዋንጫ ሲገሰግስ አርጀንቲናዊው እጅን በአፍ የሚያስጭን እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ አበርክቷል፡፡ ጄሰስ ተግባራዊ ያደረጉት ከፍተኛ ፍጥነት ያለው አጨዋወት እና በግራ መስመር ከፊቢዮ ኮኤንትራኦ ጋር የፈጠሩት ጥምረት አጨዋወታቸውን ለማቆም የሚያስቸግር አድርጎት ነበር፡፡ ንሰሮቹ በርካታ ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረጉበት በዚያ የውድድር ዘመን ዲ ማሪያ የማይዘነጉ አጋጣሚዎች ነበሩት፡፡ በዩሮፓ ሊግ ኤቨርተንን ሲገጥሙ እና በፕሪሜራ ሊጋው ሊይክሰስን ሲገጥሙ ድንቅ ነበር፡፡ አርጀንቲናዊው ብቻውን ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ተጋጣሚዎቻቸውን ከጥቅም ውጪ አደረጋቸው፡፡ በዚያ የውድድር ዘመን ዲ ማሪያ ምር ብቃቱን በማሳየቱ ቤንፊካ ሊያቆየው አልቻለም፡፡ በ2007 ለክለቡ ሲፈርም የተነገረው ነገር እውነት ነበር፡፡ አሁን ያንን በማለቱ የሚኮንነው የለም፡፡

ከኢንተር ሚላን ጋር የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግን ካሸነፉ በኋላ የስፔኑን ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ የተረከቡት ጆዜ ሞውሪንሆ 30 ሚሊዮን ዩሮ ከፍለው ወደ ቤርናቢዮ ያመጡት የመጀመሪያው ተጨዋች እርሱ ነበር፡፡ ዲ ማሪያ በቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች ለመሆን ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ በካርሎ አንቼሎቲ ዘመንም ወሳኝ ተጨዋች መሆኑን አስመሰከረ፡፡ ባለፈው ግንቦት ሪያል ማድሪድ ለአስረኛ ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ሲያነሳ በፍጻሜው ጨዋታ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው እርሱ ነው፡፡
di maria

በላሊጋ በቆየባቸው አራት የውድድር ዘመናት ዲ ማሪያ 49 ጎል የሆኑ ኳሶችን አቀብሏል፡፡ ለጎል አመቻችቶ በማቀበል የሚበልጠው በሊዮኔል ሜሲ ብቻ ነበር፡፡ በሁሉም ውድድሮች ላይ ባደረጋቸው 190 ጨዋታዎች 36 ጎሎችን ሲያስቆጥር 72 ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ እነዚህ ቁጥሮች ለምን ካርሎ አንቼሎቲ ለተጨዋቹ ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጡ ይጠቁማሉ፡፡ ነገር ግን አሃዛዊ መረጃዎቹ ብቻቸውን ሙሉውን ታሪክ አይነግሩም፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በ80 ሚሊዮን ፓውንድ የተገዛውን ጋሬት ቤል በአሰላለፍ ውስጥ ለማካተት ሲባል ወደ ግራ መስመር ቦታ እንዲለውጥ መደረጉን የተቀበለው በፍቃደኝነት አልነበረም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ዲ ማሪያ ያለመታከት ወሳኝ እንቅስቃሴዎችን ያደርግ ነበር፡፡ የተከላካይ መስመሩን ከአጥቂዎች ጋር በማገናኘት የታክቲክ ብስለቱንም አሳይቷል፡፡

አንቼሎቲ ዲ ማሪያን ማጣት አልፈለጉም ነበር፡፡ በተለይ በብራዚሉ የዓለም ዋጫ አርጀንቲናን ለፍፃሜ ለማብቃት የተወጣውን ሚና ከተመለከቱ በኋላ ለተጫዋቹ የነበራቸው ክብር ጨምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ዲ ማሪያ በማድሪድ የውስጥ ፖለቲካ እና ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ የኃይል ሚዛናቸውን አስጠብቀው ለመቆየት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተስፋ ቆረጠ፡፡

በዓለም ዋንጫ ድንቅ ብቃቱን ከማሳየቱ በፊት ኮሎምቢያዊው ሃሜስ ሮድሪጌዝ በማድሪድ የዝውውር ራዳር ውስጥ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ባላንጣቸው ባርሴሎና ልዊስ ሱአሬዝን በማስፈረሙ ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ትልቅ ስም ያለው ተጨዋች ወደ ቡድናቸው መቀላቀል ፈለጉ፡፡ የስፔኗ ዋና ከተማ ቡድን ቶን ክሩስን በማስፈረሙ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ወደ ቡድኑ ይቀላቀላል፡፡ የሮድሪጌዝ ቤርናቢዩ መድረስ ደግሞ ፔሬዝ በስልጣን ላይ በነበሩባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ እንደሚያደርጉት ትኩረት የሚሰጡ ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ መቀላቀላቸውን ይጠቁማሉ፡፡

ማድሪድ ለዲ ማሪያ አዲስ ኮንትራት አቅርቦለት ነበር፡፡ እንዲያውም ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ቀጥሎ ከፍተኛው ተከፋይ ተጨዋቾች ሊያደርጉት ተዘጋጅተው እንደነበር ፔሬዝ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ዲ ማሪያ በማድሪድ ቤት ተፈላጊነቱ እንደቀነሰ አሰበ፡፡ ከክለቡ ሌሎች ተጨዋቾች ያነሰ ትኩረት እንደሚሰጠውም አሰበ፡፡ በኋላ ላይ አስ የተባለው የማድሪድ ዕለታዊ ጋዜጣ ተጨዋቹ ክለቡን የለቀቀው ‹‹በበርካታ ማሊያዎችን ስለማይሸጥ›› በማለት ፅፏል፡፡ በዚህ ምክንያት ዲ ማሪያ ኦገስት ላይ የብሪታኒያ የዝውውር ሪከርድ በሆነ 59.7 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ አመራ፡፡ ‹‹ክለቡ እርሱን ለማቆየት የቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ነገር ግን የእርሱ ውሳኔ የተለየ ነበር፡፡ መልካሙን ሁሉ እንመኝለታለን›› በማለት አንቼሎቲ ያለውዴታቸው ያጡትን ተጨዋች ተሰናብተዋል፡፡

ኦልድ ትራፎርድ ሲደርስ ቀድሞ ጆርጅ ቤስት፣ ኤሪክ ካንቶና፣ ዴቪድ ቤካም እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ የለበሱት ሰባት ቁጥር ማሊያ ተበረከተለት፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ ልዊስ ቫን ሃል ማንቸስተርን በእንግሊዝ እግርኳስ ወደቀድሞ ክብሩ መመለስ እንዲችሉ ለመርዳት ክለቡ ከመደበው 150 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው በብራዚል ድንቅ ጊዜን ያሳለፈው አርጀንቲናዊ መሆኑ አያስገርምም፡፡

ሪዮን በምልሰት

አርጀንቲናዊያን በጁላይ 12 ቀን 2014 በሪዮ ደ ጄኔይሮው ማሬካኛ ስታዲየም የተከናወነውን ጨዋታ እያስታወሱ እንዲህ ቢሆን ኖሮስ ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ጎንዛሎ ሂጉዌይን በጨዋታው መጀመሪያ አካባቢ ያገኘው አጋጣሚ የተጠቀመበት ቢሆን ኖሮስ? በኋላ ላይ ሮድሪጎ ፓሊሲዮ ኳስ እና መረብ አገናኝቶ ቢሆን ኖሮ? ሜሲ ወይም ሰርጂዮ አጉዌሮ በቶርናመንቱ ላይ በተሻለ አቋም ላይ ቢሆንስ ኖሮ? ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚደመጠው ደግሞ በዕለቱ ዲ ማሪያ ለጨዋታ ብቁ ሆኖ ቢሆንስ ኖሮ? የሚል ነው፡፡
በሪያል ማድሪድ ቁልፍ ተጨዋቾች መሆን ሲጀምር በአርጀንቲናውያን ብሔራዊ ቡድንም ተፅዕኖው መጉላት ጀምሮ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ሜሲ፣ አጉዬሮ እና ሂግዊይንን የያዘውን የፊት መስመር ከአማካይ ክፍሉ ጋር በማገናኘት በኩል ሚናው የጎላ ነበር፡፡ የአማካይ እና የተከላካይ ክፍሉን ያለመታከት ያግዝም ነበር፡፡

በዓም ዋንጫው አሌሃንድሮ ሳቤላ ቡድናቸው ቀጥተኛ የሆነውን እና ከቶርናመንቱ በፊት ውጤታማነቱ የተረጋገጠውን የመልሶ ማጥቃት እንዳይተገብር አደረጉ፡፡ ይህም አርጀንቲና በሚገባው መጠን አስፈሪ እንዳትሆን አደረገ፡፡ ቡድኑ የምድብ ማጣሪያውን ማለፍ የቻለው ሜሲ ባስቆጠራቸው አራት ጎሎች ታግዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ሜሲ እራሱ በአንደበቱ እንደተናገረው ቶርናመንቱ እየገፋ ሲሄድ ድካም ተጫጭኖት ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሂግዌይንም ሆነ አጉዌሮ በምርጥ ብቃታቸው ላይ መገኘት አልቻሉም፡፡ ውድድሩ እየገፋ ሲሄድ የቡድኑ ዋነኛ ተስፋ ዲ ማሪያ ነበር፡፡ ወደ ሩብ ፍፃሜ የተደረገውን ጉዞ ያቃናው ስዊዘርላንድ ላይ ባለቀ ሰዓት ያስቆጠረው ጎል ነው፡፡ ምንም እንኳን ከቤልጅየም ጋር ሲጫወቱ ብቸኛውን ጎል ያስቆጠረው ሂግዌይን ቢሆንም በሙሉም የቶርናመንቱ መርሃ ግብሮች የማይዋዥቅ አቋም ያሳየው ዲ ማሪያ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው የፍፃሜ ጨዋታ አርጀንቲና ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ብትችልም እጅግ ወሳኝ ተጨዋች ሜዳ ላይ አልነበረም፡፡

ዲ ማሪያ ለአርጀንቲና ባደረገው የመጀመሪያ ቶርናመንት ላይም የፍፃሜው ጨዋታ አምልጦታል፡፡ በ2007 በካናዳ በተዘጋጀው እና በአርጀንቲና የአጉዌሮ ቶርናመንት በመባል በሚታወቀው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ አጋጣሚው ተከስቷል፡፡ ቶርናመንቱ በአርጀንቲና ያንን ስያሜ ያገኘው የሲቲው አጥቂ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ የወርቅ ጫማውን በመውሰዱ ነው፡፡ በዚያ ቡድን ውስጥ ከነበሩ እና በ2014 የብሔራዊ ቡድኑ አካል ከነበሩ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ግብ ጠባቂው ሰርጂዮ ሮሜሮ ነው፡፡ በፍፃሜው አርጀንቲና ቼክ ሪፐብሊክን 2-1 ስታሸንፍ ዳ ማሪያ ባጋጠመው የጡንቻ ህመም ምክንያት ሜዳ ውስጥ አልነበረም ሲሉ ቀልደዋል፡፡

ምንም እንኳን በወዳጅነት ጨዋታ ላይ ቢሆንም ባለፈው ሴፕቴምበር ዲ ማሪያ አርጀንቲናውያን ያጡትን ነገር አሳይቷቸዋል፡፡ ጥሩ እንቅስቃሴ ከማድረጉም በላይ አራት ኳሶችን ለጎል አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ አጋጣሚው ልዩ የሚያደርገው ተጋጣሚያቸው ጀርመን መሆኑ ነው፡፡

ዲ ማሪያ እስካሁን በቤንፊካ እና ማድሪድ ያሳየውን አይነት አቋም በዩናይትድ አላበረከተም፡፡ ጥሩ አጀማመር ቢያደርግም ተደራራቢ ጉዳት እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ ቫንሃል ምቹ ፎርሜሽን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ምክንያት የመሀል ሜዳ አማካይ ሚና እንዲወጣ እየተደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ገና 26 ዓመቱ በመሆኑ ብቃቱን የሚያስመሰክርበት በቂ ጊዜ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

The post ዲ ማሪያ – ከሮሳሪዮ እስከ ዩናይትድ appeared first on Zehabesha Amharic.

Health: ከዓይን ፍቅር እንዴት መውጣት እንችላለን?

0
0

Romantic copy
ከሊሊ ሞገስ

የዓይን ፍቅር /Sight love/ የምንለው አንድን ግለሰብ በተደጋጋሚ በመመልከትና አዕምሮአዊ ስዕል በመሳል የፍቅር ስሜትን ውስጣችን ውስጥ ማዳበር ማለት ነው፡፡ ንቁ የሆነው የአዕምሯችን ክፍል በአካባቢው ያሉ መረጃዎችን የማሰባሰብ ኃይል ያለው ክፍል ነው፡፡ ይህ የአዕምሯችን ክፍል ከአካባቢው ያገኘውን መረጃ የማጠራቀሚያ ቦታ ስለሌለው ወደ ሌላኛውና ንቁ ወዳልሆነው የአዕምሮ ክፍል /the unconscious mind/ መረጃዎችን በሙሉ ያስተላልፋሉ፡፡ ንቁ ያልሆነው የአዕምሯችን ክፍል የተሰጠውን መረጃ እውነት አድርጎ የሚቀበልና ኢ-ምክንያታዊ ስለሆነ ንቁ ከሆነው የአዕምሯችን ክፍል የመጣውን መረጃ በሙሉ ያጠራቅማል፡፡
ከአካባቢያችን ጋር መስተጋብር የሚፈጥረው ንቁ የሆነው የአዕምሯችን ክፍል ስለሆነና በአካባቢያችንም ብዙ ነገሮች ስላሉ ይህ የአዕምሯችን ክፍል የተወሰኑት ላይ ትኩረት በማድረግ ወደ ውስጠኛውና ንቁ ወዳልሆነው የአዕምሯችን ክፍል ይልከዋል፡፡
ወደ ዓይን ፍቅር ስንመጣ አንድ ግለሰብ አንድ የሆነ ሰውን በሚያይበትና ልዩ ሆኖ/ና በሚታይበት ወይም በምትታይበት ጊዜ ንቁ የሆነው የአዕምሯችን ክፍል ትኩረት ሰጥቶ መከታተል ይጀምራል፡፡ ልዩነቱንም ያደንቃል /በተደጋጋሚ መረጃውን ያውጠነጥናል/፡፡ ይህ በሚሆንበት ሰዓት አንድን መረጃ ንቁ ወደሆነው የአዕምሯችን ክፍል በተደጋጋሚ ይልካል፡፡ በዚህ ጊዜ ንቁ ያልሆነው የአዕምሯችን ክፍል በተደጋጋሚ የተሰጠውን መረጃ በመቀበል የታየውን /የታየችውን/ ሰው ምስል ቀርፆ ይይዛል፡፡ በማስታወሻ የአዕምሯችን ማዕከልም ውስጥ ይህ ስዕል በሚገባ ይሳላል፡፡ በተጨማሪም ንቁ የሆነው የአዕምሮ ክፍል ስለፍቅር ወይም ስለወሲብ ወይም በጠቅላላው ስለተቃራኒ ፆታ በሚያስብበት ሰዓት የሚያስበው/የሚያገኘው መረጃ ያን ስዕል ይሆናል፡፡ በመሆኑም ፍቅርን ሲያስብ የሚያስበው በአዕምሮው የሳላትን/የሳለውን ሰው ብቻ ይሆናል፡፡ ታዲያማ ይህ ሰው የዓይን ፍቅር ያዘው ማለት ነው፡፡
ይህንን ሃሳብ በደንብ ለማስረዳት የጠያቂያችንን ገጠመኝ መመልከቱ በቂ ነው፡፡ በአካባቢው ብዙ ሴቶች ያሉ ቢሆንም ከእነዚህ ውስጥ አንዷ ግን የተለየች ናት ማለትም ረጋ ያለችና ደብተሯን ደረቷ ላይ ለጥፋ የምትሄድ አይነት ነች፡፡ በመሆኑም ንቁ የሆነው የአዕምሮው ክፍል ትኩረት ሰጣትና በተደጋጋሚ ስለእሷ አውጠነጠነ፡፡

ይህም ሲሆን ንቁ ያልሆነው የአዕምሮው ክፍል የልጅቱን ስዕል መሳል ጀመረ፡፡ በተጨማሪም ከልጅቱ ጋር አብረዋት የተማሩ ልጆችና እርሷን በቅርበት የሚያውቋት ሰዎች ስለ እሷ ያወሩ ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ ንቁ የሆነው የአዕምሮ ክፍል ይህንን መረጃ ንቁ ወዳልሆነው የአዕምሮው ክፍል የልጅነቱን ስዕል በሚገባ ሳለው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ኤ.ኤም ፍቅርን ባሰበ ቁጥር የልጅቱን ስዕል እንዲያመላልስ አስገድዶታል፡፡ ይህንንም በጽሑፉ ላይ እንዲህ ብሎ ገልፆታል፡፡ ‹‹እኔም ሳላስበው ስለእሷ ሌት ተቀን ማሰብ ጀመርኩ›› በማለት እዚህ ላይ አንድ ነገር አስተውሉልኝ፡፡ ስለ እሷ የሚነገረው ኔጌቲቭ ነገር ብቻ ነው፡፡

ነገር ግን አንተ እንደሚወራለት አታስባትም፡፡ ይህ የሚያሳየው ንቁ ያልሆነው አዕምሯችን ነገሮችን ጥሩ ወይም መጥፎ ብሎ እንደማይመዝን ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ንቁ የሆነው አዕምሯችን የሚያስተላልፍለት መረጃ ዝም ብሎ የሚቀበል መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም ኤ.ኤም ንቁ የሆነው የአዕምሮ ክፍል ስለ ልጅቱ የሚሰበስበው መረጃ ወደ ንቁ ወዳልሆነው የአዕምሮ ክፍል በተደጋጋሚ ስለላከ ንቁ ያልሆነው የአዕምሮው ክፍልም አምኖ ተቀብሎ የልጅቱን ስዕል በሚገባ ስለሳልከው ኤ.ኤም ወደ አይን ፍቅር ገባህ ማለት ነው፡፡

ከዓይን ፍቅር እንዴት መውጣት እንችላለን?

ከዓይን ፍቅር መውጫ መንገዶችን ወደ መጠቆሜ ከመግባቴ በፊት አንድ አብይ ቁም ነገር ላካፍላችሁ፡፡ የዓይን ፍቅር በሚይዘን ሰዓት የምናፈቅረው ተፈቃሪውን ሳይሆን የተፈቃሪውን ስዕል ነው፡፡ አንድ ሰው እውነተኛ ፍቅር የሚይዘው የተፈቀረውን ግለሰብ ሰብዕና ጠንቅቄ አውቀዋለሁ በሚልበት ሰዓት ነው፡፡ ይህም ሲሆን የግለሰቡን ጥሩና መጥፎ ጎኑን ያጠናና ጥሩውን አድንቆ፣ መጥፎውን ደግሞ አንድ ቀን ይለወጣል ብሎ አምኖ ወይምንም የሆነው ቢሆን ተቀብዬው እኖራለሁ ብሎ ሲቀበል ነው፡፡ የዓይን ፍቅር በሚሆንበት ሰዓት ግን የግለሰቡን ሰብዕና ሳናውቅ ነገር ግን ስለ ግለሰቡ በሃሳብ የሳልነውን ስዕል በሚገባ ስላወቅነው ስዕሉን እንወደዋለን፡፡

ስለሆነም ከዓይን ፍቅር ለመውጣት የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት የግለሰቡን ትክክለኛ ስዕል ለመረዳት መሞከር ነው፡፡ የግለሰቡን ትክክለኛ ስዕል በሚገባ ለማወቅ ደግሞ የግለሰቡን ሰብዕና ወይም ማንነት በቅርበት መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ጠያቂያችን ኤ.ኤም ሁሌ የምታስባትን ልጅ በጥልቀት ቀርበህ ትክክለኛ ማንነቷን ካወቅክ በኋላ ስለ እሷ ያለህን ሃሳባዊ ስዕል በትክክለኛው የእሷ ስዕል መቀየር አለብህ፡፡

በተግባር በምናይበት ሰዓት ግን በዓይን ፍቅር የወደቅንለትን ሰው በአካል ቀርቦ ለማነጋገር ብሎም ለማጥናት አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምን አስቸጋሪ እንደሚሆንና ጠያቂያችንም ለምን የገዛላትን ስጦታ ለመስጠት እንደከበደህ ላብራራልህና የመፍትሄ አቅጣጫ ልጠቁምህ፡፡
ስለ አንድ ግለሰብ በተደጋጋሚ ይነገረንና ስለ ግለሰቡ የራሳችን የሆነ ሃሳባዊ ስዕል በአዕምሯችን እንስላለን፡፡ ያንን ግለሰብ በተግባር ስናገኘው ደግሞ አዕምሯችን የሰውዬውን ትክክለኛ ስዕል ይስላል፡፡ በአብዛኛው እነዚህ ሁለት ስዕሎች ይጋጩብናል፡፡ በዚህ ጊዜ አዕምሯችን የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ ግጭት ደግሞ አዕምሯችንን ሰላም ያሳጣዋል፡፡ የሰው ልጅ በባህሪው ደግሞ ሰላን የሚያሳጣውን ነገር ይፈራል፡፡ ስለሆነም መሸሽን ይመርጣል፡፡ ስለዚህም በአይን ፍቅር የወደቅንለትን ሰው በአካል ብንቀርበው ሊፈጠር የሚችለው አዕምሯዊ ግጭት ስለማንፈልገው እንፈራዋለን፡፡

በዓይን ፍቅር የወደቅንለትን ሰው ከተቀራረብነው በኋላ የሚከሰት አንድ አብይ ችግር አለ፡፡ የዓይን ፍቅር ሲይዘን ስለ ግለሰቡ የሳልነውን ሃሳባዊ ስዕል ይዘን ግለሰቡን ስንቀርበውና የግለሰቡን ማንነት እያወቅነው ስንመጣ ግለግለሰቡ ትክክለኛ ስዕል እየሳልን እንመጣለን፡፡ ነገር ግን አዕምሯችን የአንድን ግለሰብ ስዕል በሌላ ለመተካት ጊዜ ይወስድበታል፡፡

በተጨማሪም የቀድሞውን ስዕል በአዲስ መተካቱ ውስጣዊ ሰላሙን ያዛባዋል፡፡ ይህ ስለሆነም በዓይን ፍቅር ወድቀን ተፈቃሪውን እየቀረብነውና እያወቅነው እየመጣን እንኳ አዕምሯችን የሳለውን ስዕል በእውነተኛው ስዕል ሳይተካው ይቀርና ያፈቀርነውን ሰው በውል ሳንረዳው ወደ ትዳር ዓለም ዘልቀን ለመግባት እንሯሯጣለን፡፡

ይህ ደግሞ በትዳር ዓለማችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግርና በአፍቃሪው ላይ ከፍተኛ አዕምሯዊ ፀፀት ብሎም የአዕምሮ ጤና ችግር ያስከትልበታል፡፡ ምክንያቱም ሃሳባዊ ስዕሉ የሰውዬውን ማንነት በደንብ እንድንረዳ አድርጎን እውነተኛውን የግለሰቡን ሰብዕና ሳንረዳ ወደ ትዳሩ ዓለም እንዘልቅና በኋላ ላይ በትዳር ዓለም ስንሆንና የግለሰቡን እውነተኛ ማንነትና ትክክለኛ ነው ብለን የተቀበልነው ማንነቱ ሲጋጭብን ትዳራችንን ለግጭት አዕምሯችንን ደግሞ ለፀፀት ያጋልጠዋል፡፡ በመሆኑም አንተም ተፈቃሪዋን ቀስ በቀስ ቅረባት፡፡

ለምሳሌ መጀመሪያ በስልክ እየደወልክ ወሬዎችን ለረዥም ጊዜያት ማውራትን ተለማመድ፣ ስለራስህ በመግለፅ ስለ እሷ እንድትገልጽልህ በማድረግ፣ እራስህን ገልፀህላት የሆነ ቦታ እንድታይህ በማድረግ፣ አካባቢያችሁ በሚገኝ ቦታ እንድታይህ በማድረግ፣ አካባቢያችሁ በሚገኝ ቦታ ሁለታችሁንም የሚያውቁ ሰዎች ባሉበት ቦታ በመገናኘት፣ ቀስ እያላችሁም ብቻችሁን በመገናኘት ወዘተ… የመቀራረብ ሁኔታችሁን ማዳበር፡፡ በአዕምሮህ ሃሳባዊ ስዕል ከሳልከው በኋላ በአካል ያገኘኸውን ሰው ለማነጋገር፣ ለመቅረብ ቀስ በቀስ ግን እያወቅከው ትመጣና በስተመጨረሻ ለምደኸው ልክ እንደሌሎች ሰዎች አይነት እንደሆነና የተለየ እንዳልሆነ ትረዳዋለህ፡፡ ይህ ጊዜ ይወስዳል እንጂ መሆኑ አይቀርም፡፡ እዚህ ላይ ግን ላስጠነቀቅህ የምፈልገው ነገር ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልህ ከዚህ ቀደም ስለ እሷ የሳልከው ስዕል የአሁን ማንነቷን/እውነተኛ ማንነቷን እንዳታውቅ ሊያደርግህ ስለሚችል ሌላ በህይወት ወሳኝ የሆነ ውሳኔን ከመወሰንህ በፊት የእርሷን እውነተኛ ማንነት ከሞላ ጎደል በሚገባ ልታውቅ ይገባሃል፡፡

ያን ካላረግክ ግን በወደፊቱ ህይወትህ ለሚመጣው መመሰቃቀል ኃላፊነቱን በፍቃደኝነት ወስደሃል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ ቅረባት፣ ማንነቷን በሚገባ እወቀው፡፡ በስተመጨረሻም አስፈላጊውን ውሳኔ ወስን፡፡ አጠቃላይ ምክሬ ነው፡፡ አበቃሁ፡፡ መልካም የፍቅር ጊዜ ይሁንልህ፡፡

The post Health: ከዓይን ፍቅር እንዴት መውጣት እንችላለን? appeared first on Zehabesha Amharic.

ፖሊስ የፍ/ቤት ትዕዛዝን በመሻር የሰማያዊ አባላትን ዋስትና ከለከለ

0
0

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

ethiopia-blue-party-300x164በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የካዛንቺስ 6ኛ ፖሊስ በእስር ላይ የሚገኙትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመሻር ዋስትና ከለከለ፡፡

ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን የሽብር ድርጊት ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳትና በመሳተፍ›› ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲው አባላት ዛሬ ሚያዝያ 30/2007 ዓ.ም ጠዋት በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርበው የ6000 ብር የሰው ዋስትና ተፈቅዶላቸው ነበር፡፡

በእነ ወይንሸት ሞላ የምርመራ መዝገብ የተካተቱ አምስት ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ዋስትና ከማግኘታቸው በፊት ፖሊስ ‹‹ምርመራየን አልጨረስኩም፣ ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ይችላሉ›› እና ሌሎች ተደጋጋሚ ምክንያቶችን በማቅረብ ዋስትና እንዳይፈቀድ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ ከሀገር ሊወጡ ይችላሉ የሚለውን ምክንያት ባለመቀበል ከዋስትናው ጋር ለኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ተጠርጣሪዎቹ ከሀገር እንዳይወጡ የሚል ደብዳቤ እንዲጻፍ ትዕዛዝ በመስጠት የ6000 ብር ዋስ አቅርበው እንዲወጡ ሊፈቅድ ችሏል፡፡

በዚህ መሰረት የተጠርጣሪ ቤተሰቦች ዋስትናውን ጨርሰው ለማስፈታት በሄዱ ጊዜ ፖሊስ ‹‹ሰኞ ይግባኝ ብለን ፍርድ ቤት ስለምናቀርባቸው ሊፈቱ አይችሉም›› በሚል ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ተጠርጣሪዎቹ በእስር እንዲቆዩ አድርጓል፡፡

በእነ ወይንሸት የምርመራ መዝገብ የተካተቱት አምስት ሰዎች ወይንሸት ሞላ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ጸጋየ እና ማስተዋል ፈቃዱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ሲሆኑ፣ በዚሁ መዝገብ ላይ ፖሊስ የፓርቲው አባል እንደሆነች የሚገልጸው፣ እሷ ግን አባል አለመሆኗን የገለጸች ቤተልሄም አቃለወርቅም ትገኛለች፡፡

The post ፖሊስ የፍ/ቤት ትዕዛዝን በመሻር የሰማያዊ አባላትን ዋስትና ከለከለ appeared first on Zehabesha Amharic.

ኣላሙዲን ሶስት ዘፋኞችን ሚሊየነር አደረጉ


“ነብስ ይማር ቦቴንግ”! (አዋዜ፡አለምነህ ዋሴ ዜና)

በአይሲኤስ የተገደሉትን ቤተሰቦች ያልረዱት ኣላሙዲን ሶስት ዘፋኞችን ሚሊየነር አደረጉ

ኢትዮጵያዊ ማንነታችን የሚፈተንበት ቁጥር ፩ (እጅግ አስቸኳይ በደንብ በጥሞና እስከመጨረሻው ድረስ መነበብን የሚፈልግ ታሪክ)

0
0

የቤተክርስቲያን ታሪክ ተመራማሪውና የማከብረው ለእርሱም የተለየ ቦታ የምሰጠው ወንድሜ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ በሊብያ ስለተሰዋ አንድ ኢትዮጵያዊ ወንድማችን ጉዳይ ሰሞኑን ጽፈው አንብቤ ነበር ።

zemedkun 1
ይህ ሰው 2 የሚያማምሩ ልጆቹን ትቶ ማለፉንም እነዳኒ በጽሑፋቸው ጠቅሰውታል ። እውነት ለመናገር ሌሎቹ የሰማዕታት ቤተሰቦች ጋር እንደሄድኩት ሁሉ እዚህም ለመሄድ ኃሳቡ የነበረኝ ቢሆንም የግል ስንፍናዬም ተጨምሮ ጥቂት እረፍት አጥቼም ስለነበር ለሜሄድ ከማሰብ በቀር አልተሳካልኝም ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከልጆቼ ጋር በሰማዕታቱ ጉዳይ ስናወራ ልጆቼ የዚህ ሟች ከሌሎቹ ይልቅ በጣም የሚያሳዝን እንደሆነ ደጋግመው ይነግሩኛል ። እኔም የሁሉም ሰማዕታት ክብር አንድ እነደሆነ ፣ ሁሉም ቢሆኑ በግፍ መገደላቸው አሳዛኝ እነደሆነ ብነግራቸውም ለምን በዚህኛው ኢትዮጵያዊ አሟሟት ላይ በተለየ ሁኔታ ልባቸው እንደተነካ ግን በውስጤ ተረድቻቸዋለሁ ። ምክንያት አድርጌም ያየሁት ደግሞ የሟችን ህፃናት ልጆች ፎቶ በማየታቸው እንደሆነና ከእንግዲህ እነዚህ ህፃናት አባት የላቸውም በሚል በውስጣቸው የተፈጠረባቸው የሐዘን ስሜት እንደሆነም ገምቻለሁ ።
በእንዲህ አይነት ሁኔታ ላይ ስንፍ ብዬ በተቀመጥኩ ሰዓት ላይ ግን የሚያነቃ ሰው አገኘሁ። በአካል የማላውቃት “መስቱ” የምትባል በአረቢያ ምድር የምትኖር እህት እያለቀሰች እባክህ ከተቻለህ ሂድና ህፃናቱን እያቸው ፣ ለምንድነው መንግሥትም ህዝቡም የማይጠይቃቸው ብላ እያለቀሰች የድምጽ መልእክት በ what’s up አስቀመጠችልኝና ለመሄድ ወሰንኩ ።

ውድ ጓደኞቼ እስቲ አብረን ወደ አዋሬ እንሂድ ። ኑ በዓይነ ህሊናችሁም ተከተሉኝ ።
አድራሻውን ለማግኘት ብዙም አልተቸገርኩም ። ዲን ዳንኤል በማስታወሻው ላይ መሐመድ ካሳ የሚባል ልጅ ይረዳችኋል ብሎ ስልክ ቁጥሩን አስቀምጦ ስለነበር ከመሐመድ ካሣ የኃዘን ቤት አድራሻውን ተቀብዬ ከወንድሜ ከዘማሪ ዲ/ልዑልሰገድ ጌታቸው/ቋንቋዬ ነሽ/ ጋር ወደ ኃዘኑ ቤት ሄድን ።

የሟች ባለቤት በቅርቡ የባለቤቷን ሞት የተረዳች ቢሆንም እኔና ሉሌ በደረስን ሰዓት ግን 11 ሰዎችን ብቻ ነው በኃዘኑ ቤት ለማስተዛዘን ኃዘን ተቀምጠው ያገኘናቸው ። በየትም ቦታ ሰውን መርዳት መለያቸው የሆነው የቂርቆስ ሠፈር ልጆች ያመጡት የአበባ ጉንጉን እና የሟችን ፎቶ ከሚያሳይ ባነር በቀር እንደሌሎቹ ሟቾች የአበባና የኃዘን መግለጫ ምልክቶችም በሥፍራው አይታዩም ። ይህም ሟችን አለማወቅ ሳይሆን የሆነ ነገር እንዳለ እንድጠረጥር አደረገኝ ። ምክንያቱም ሌሎቹ አደጋው የደረሰባቸው ሰዎች ቤት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ እስላም ክርስቲያን ሳይል በአካል በመገኘት ጭምር ሲያጽኗኗቸው እንደነበር ተመልክተናል ።

አርቲስት ዮሴፍ ገብሬ /ጆሲም/ ከአዲስ አበባ ጎንደር ከጎንደር ትግራይ ከትግራይ ወልቂጤ እየዞረ ያዘኑትን ሲያረጋጋም አይቻለሁ እዚህ ግን ማንም ድርሽ አላለም ። ጆሲ እዚህም እንደሚሄድና ታሪክ እንደሚሠራ ተስፋ አደርጋለሁ ። ጋዜጠኞች ፣ አርቲስቶች ፣ ፖለቲከኞች ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ አንዳቸውም ድርሽ አላሉም ። ይህ የሆነበት ምክንያቱ ምንድነው ? ይህ ሟች ኢትዮጵያዊ አይደለም እንዴ ? ባይሆንስ ሰው እኮ ነው ሰው ። ዜናው በደንብ አልተሰራም እንዳንል በደንብ ተሰርቷል ። ያውም እንዲያውም በራዲዮ ፋና ፣ በኢቲቪ ና በኅትመት ሚድያዎች ሁሉ ተነግሯል ። ከዚህ በተጨማሪም ብዙ አንባቢያን ባለው በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ብሎግ እና በብዙ የፌስቡክ ጸሐፍያን ዜናው ተሰራጭቷል ። እንዲህም ሆኖም ግን ጠያቂ የለም ።

ባለቤቱ “ብርቱካን ጌቱ ትባላለች ” ሰሜን ሸዋ ሸኖ አካባቢ ነው የትውልድ ሀገሯ ። በስፍራው በደረስኩ ጊዜ ኩርምት ብላ በተሰበረ መንፈስ አንገቷን ደፍታ ተቀምጣለች ። ስለእውነት ማርያምን እላችኋለሁ ኃዘን ድቅቅ አድርጓታል ። ከአብራኳ ሁለት የሚያማምሩ ልጆችን ከሟች ባለቤቷ አፍርታለች ።
zemedkun 2

ብርቱኳን ህፃን ኢየሩስ ብርሃኑ የተባለች የ8 ዓመት ቆንጅዬ ሴት ልጅና ህፃን ዮናታን ብርሃኑ አሁን የ4 ዓመቱ ላይ የሚገኝ ከፊታችን በሚመጣው ነሐሴ 24 የተክለሃይማኖት ዕለት 5ተኛ ዓመት የልደት በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ የሚገኝ የሚያምር ወንድ ልጆች እናት ናት ። በዚህ ደግሞ እድለኛም ናት ። ምክንያቱም እስካሁን ባለኝ መረጃ መሰረት በግፍ ከተሰውት ውስጥ ዘር ተክቶ ያለፈው አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ብቻ ነው ። ህፃናቱ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ወዲያ ወዲህ እያሉ በዚያች ጠባብ ግቢ ውስጥ መቦረቃቸውን ቀጥለዋል ።

እኔም ተገብቶኝ ሳይሆን ከመጣሁ አይቀር በማለት ለማጽናናት ያህል ጥቂት የእግዚአብሔር ቃል መናገር ስጀምር የሟች ቆንጅዬ የምታምረዋ ሕፃን ኢየሩስ ቆሎ ይዛ መጥታ ልቅሶ ለመድረስ የመጡትን ሁሉ እየዞረች በፈገግታ ታዘግናለች ። ትንሹ ወንዱ ልጅ ዮናታን ግን ካለበት ሮጦ በመምጣት ከላዬ ላይ ተለጠፈ ። እኔም እቅፍ በማድረግ በኃዘን ስሜት ውስጥ ብሆንም እንደምንም ብዬ ማጽናናቱን ቀጠልኩና በግድ የማጽናኛ ቃሉን ፈፀምኩ ።

በወቅቱ የህጻኑ ሁኔታ ሌሎችን ቢያስለቅስም እኔ ግን በሀሳቤ ስንት ቦታ ሄድኩ መሰላችሁ ። ስለእውነት እኔ ብሆንስ ብዬ ልጆቼ እንዳሰቡት አሰብኩ ። በመጨረሻም የሟችን ባለቤት ብርቱካንን እና ታናሽ እህቷን ወደ ተከራየችው መኖሪያ ቤት በምትመስል ትንሽዬ ቤት ገብተን ብዙ ተወያየን ። በውይይታችን መኃልም ሟችን ለምን ብዙ ሰው ኃዘኑን እንደማይደርሰውም አሁን ፍንጭ አገኘሁ ። የሚገርም ነው ። በጣም ያሳዝናልም ።

ሟች በሃይማኖቱ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነው ። ይሄ ደግሞ መብቱ ነው ። ሚስት ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ። ፍቅር አንድ ላይ አብሮ 12 ዓመት ያህል ያኖራቸው ። የሚያኖራቸው ፣ በዚህም ምክንያት ያልተለያዩና በአብሮነታቸውም ሁለት የሚያማምሩ ሕጻናት ልጆችን ያፈሩ ናቸው ። እነዚህ ህፃናት ምንም እንኳን አባታቸው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ቢሆንም ወላጅ አባት ሟች አቶ ብርሃኑ ጌትነት የእናትየውን የወይዘሮ ብርቱኳንን መብት ሳይጋፋ ፍላጎቷን ጠብቆላት በባለቤቱ ወ/ሮ ብርቱኳን የእምነት ሥርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና መሠረት በመንበረ መንግሥት/ ግቢ / ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሴቷን በ80 ወንዱን በ40 ቀኑ ክርስትና አስነስታ ሰርተፍኬታቸውን በእጇ የያዘች እናት ናት ።

የሚያሳዝነው የቀበሌው ሴቶች ማኅበር እንግዳ ቢመጣ ብለው የቆሎ መግዣ ከሰጧትና ባለቤቷ ከሚከታተልበት የሃይማኖት ተቋም ከተሰጣት አነስተኛ ገንዘብ በቀር ማንም ዞር ብሎ አላያትም ።
የሚገርመው ሟችን ከባለቤቱና ከእህቷ ጋር በመጫወት እየቆየሁ ስመጣ በተለይ እህቷን የማውቅበት ቦታ ጠፋብኝ እንጂ የምንተዋወቅ እንደሚመስለኝ ስነግራት ” ሟች እኮ ደንበኛህ ነው ። የሚሠራቸውን ጥቅሶች እያስረከበህ ትሸጥለት ነበር ። እኔንም የምታውቀኝ አንዳንዴ እሱ ባልተመቸው ጊዜ ጥቅሶችን አመጣልህ ስለነበር ነው ብላ ስትነግረኝ ጊዜ የባሰ ደነገጥኩ ፣ አዘንኩም ።
birhanu getaneh
እውነት ነው “ብርሃኑ” ብዙ ሺህ በእንጨት ላይ የተቀረፁ ግሩም የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለ ” ጌልገላ መዝሙር “ቤቴ ያስረክበኝ ነበር ። እኔም እነዚያን ጥቅሶች ሽጬያቸዋለሁ ። ምናልባትም ይህን ጽሑፍ እያነበባችሁ ያላችሁ በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ የምትኖሩ ሰዎች በቤታችንም ሆነ በሥራ ቦታችን ተንጠልጥሎ የሚገኘው ጥቅስ የብርሃኑ የእጅሥራ ውጤት ሊሆን ይችላል ።
ይህ ኑሮ ነው እንግዲህ ከእጅ ወደ አፍ ለመሆን እንኳን አላደርሰው ቢለው ነው ብርሃኑ እነዚህን እንቦቀቅላና የሚያማምሩ ፍቅር የሆኑ ህፃናት ልጆቹን እና ወድ ባለቤቱን ሜዳ ላይ በትኖ የተሻለ ኑሮ ይኖሩ ዘንድ በማሰብ በሕይወቱ ተወራርዶ ስደትን የመረጠው ። ወንድማችን አውሮፓን በማሰብ ወደ ሊቢያ ሄዶ በዚያም በአራጆች እጅ ወድቆ እጁን የኋሊት ታስሮ ርኅራሄ በሌላቸው ጨካኞች አናቱ በጥይት ፈራርሶ ነው በሊብያ በበረሃ የቀረው ።

ብርሃኑ ይህ ይመጣል ብሎ ባለማሰቡ ቢያንስ ከ3 ወር በኋላ አውሮፓ ስገባ የተሻለ ገንዘብ እልካለሁ በማለት የ3 ወር የቤት ኪራይ ከፍሎላቸው ነበር የሄደው ። እንዳሰበው ሳይሆንለት ቀረ እንጂ ።
ይህን በሰማን ጊዜም እኔና ልዑልሰገድም ወሰንን ። ብናጣ ብናጣ ለምነንም እንኳን ቢሆን እኒህን አባታቸውን በግፈኞች የተነጠቁ ሕጻናት ለማስተማር ባንችል ዩኒፎርማቸውን እና ለበዓል የሚሆን ልብስ መግዛት አያቅተንም በማለት የሚቻለንን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል ገብተን ተመለስን ።

ልዑልሰገድ /ቋንቋዬነሽ/ እንዲህ አላቸው ” እኔ ሞቼ አበቃልህ ተብሎ እንዲያውም አንዳንዶች ” ቀብረነው እኮ መጣን ” ብለው እስኪናገሩ ድረስ በሰው ዘንድ የተፈረደብኝ ሰው ነበርኩ ። ለእኔ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይሉ ሁሉም ተረባርቦልኝ በጸሎታቸውም አግዘውኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጭምር ነፃ የአየር ትኬት ሰጥቶኝ ይኸው ታክሜ በእግዚአብሔር ቸርነት በድንግል ማርያም አማላጅነት በእናንተ ሁሉ ልቅሶና እንባ ድኜ እድሜ ሰጥቶኝ እዚህ ደርሻለሁ ። ቋሚ የሆነ ገቢ ባይኖረኝም ከማገኘው ላይ ለጊዜው አንድ ሺህ ብር እሰጣለሁ ። ለወደፊቱ ግን ዘመድኩን እንዳለው ለህፃናቱ ቢያንስ እኔና ዘመድኩን የተቻለንን እናደርጋለን በማለት ቃል የገባውን ዛሬ ፈጽሟል ።

ከሁሉም በላይ በእነ ያሬድ ሹመቴ አሳሳቢነት አዋሬ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃዘኑ ቤት ድረስ በመሄድ ራሳቸው የባንኩ ሠራተኞች በሟች ሚስት ስም አካውንት ከመክፈትም አልፈው በባንክ ሂሳቧ ላይ 600 ብር ጨምረው አስረክበዋታል ። ታዲያ የእኔ ልጆች ማኅተመ ዘመድኩን እና ማርያማዊት ዘመድኩን በስማቸው የሰጡት 1000 ብርና ዘማሪ ልዑልሰገድ የሰጠው 1000 ብር ሲደመር ከአሁኑ 2600 ብር ሆነላቸው ማለትም አይደል ። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን እና ይህን መልእክቴን ማንበብ ሳትፈልጉ በግድ ያነበባችሁ ብትሆንም ኢትዮጵያዊ የሆናችሁ በሙሉ ። እግዚአብሔር በረከቱን የሰጣችሁ በሰጣችሁ መጠን በብዙ ፣ ምንም በቂ የሆነ ገቢ የሌላችሁ በጥቂቱ ፣ ብትሰጡና የየአቅማችንን ከ10 ብር ጀምሮ ብናዋጣ በእርግጠኝነት የተሳካ ሥራን ሠርተን የልጆቹን ሕይወት በመለወጥ እግረመንገዳችንንም የጽድቅ ሥራን ሠራምን ማለት ነው ።

※※※ማሳሰቢያ ለአንዳንድ የፌስቡክ ጸሐፍት※※※

እንደሚታወቀው በሊብያ በረሃ ውስጥ በአሸባሪው ISIS አማካኝነት አንገታቸውን ተቀልተው ስለታረዱትና በጥይት ተረሽንው ስለሞቱት ሰዎች ማንነት በጻፍንበት አንቀጽ ላይ ከኦርቶዶክሳውያን በቀር ሌላ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ወገኖች አልሞቱም ብለን ሽንጣችንን ገትረን ስንሟገት እንደነበር ይታወሳል ። ዋቢ ያደረጋችሁትም ራሱን ISIS የተናገረውን ሰምተን ነው ብላችሁ ነበር ። ማርያምን ነው የምላችሁ እኔ በበኩሌ ISIS የተናገረውን አላምነውም ። ደግሞም መብቴ ነው ። ካልጠፋ መረጃ አሸባሪ የተናገረውን የማመን ግዴታ የለብኝም ። ISIS እንደሁ የተበቀለ የመሰለው ኢትዮጵያን ነው ። የተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞችንም እንዲሁ ። ነገር ግን እንዲያም ብለን የተሟገትን ቢሆንም እንኳ ነገር ግን አስካሁን የሟቾ ማንነት ገና በጥቂቱ ነው እየታወቀ ያለው ። የሟቾቹ ዜግነትም ቢሆን ይኸው ቀስ በቀስ እየታየና እየተለየም ነው ። እንዲያውም አብዛኛውን ቁጥር እየያዙ የመጡት ወንድሞቻችን ኤርትራውያን መሆናቸውም እየታየ ነው ።

እናም እኔ በበኩሌ ሙሉው ሰማዕታት ኢትዮጵያውያን ፣ ሃይማኖታቸውም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብቻ ናቸው ብዬ አልደመድምም ። በደንብ ማንነታቸው ተጣርቶ የመጨረሻውን ይፋዊ ውጤት እስክናገኝ ድረስ ረጋ እንበል የምለውም ለዚህ ነው ። አንዳንዶቻችን ግድያው ሲፈጸም ስምዝርዝር የሰጠን እና በቦታው የነበርን እስኪመስል ድረስ ከኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ውጪ የሌላ እምነት ተከታይ የሆነ ማንም አልሞተም እያልን የምንለውን ጽንፍ የያዘና ከሃይማኖተኛ ሰዎች የማይጠበቅ ድርጊት ከመፈጸምም ብንቆጠብ መልካም ነው ።

ቅዱስ ሲኖዶሳችንም በዚህ ላይ ያሳየውን ጥንቃቄ በግል ሳላደንቅ አላልፍም ። በአሁኑ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔም ላይ እነዚህን የሊቢያውን ሰማዕታት ” ሰማዕት ” እንዲባሉ መወሰኑ ተነገሯል ። ደስ የሚል ዜናም ነው ። እኒህን ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በ1999 ዓም በጅማ በሻሻ በሰማዕትነት ያለፉትን ወገኖቻችንም ጨምሮ የሰማዕትነት ማዕረግ ይሰጣቸዋል ብዬም እጠብቃለሁ ።

ለሁሉም ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ማንነታቸውን ለይቶ የክብር ማዕረጉን ለመስጠት ለጥቅምቱ የሲኖዶስ ጉባዔ አሸጋግሮታል ። እውነት ነው በቀኖና ቤተክርስቲያን መሠረት አስፈላጊውን መረጃ መሰብሰቡ የግድ ስለሆነ እንዲህ ማድረጉ አግባብም ነው ። የሞቱት ሰዎች ቢሆንም ቤተክርስቲያናችን በቀኖናዋ መሠረት ” ሰማዕት ” ብላ ሰይማቸዋለች ። ነገር ግን የቅድስናውንና የክብራቸውን ነገር የምታውጀው ግን ቀኖና ቤተክርስቲያን በሚያዘው መሠረት መስፈርቱን ያሟሉትን ብቻ ነው ።

ለዚህም እስከ ጥቅምት 2008 ዓም ድረስ ተጣርተው እንዲቀርቡ ብዙ አማራጮች ቀርበዋል ። ውይይት ተደርጎም ሰማዕታቱን የሚመጥናቸውን መልካም የሆነ ዜና እንሰማለን ። ሴኖዶሳችን ።
፩ኛ፦ ” ወበዛቲ ዕለት ” ተብሎ ዜናቸው በሚያዝያው ስንክሳር ላይ ተጽፈው የሚታሰቡ ፣
፪ኛ፦ በሰማዕታቱ ስም ቤተ ጸሎት በማነጽ የሚታሰቡ
፫ኛ፦ገድላቸውን በመጽሐፍ መልክ በማጻፍ የሚታሰቡ
፬ኛ፦ ምን አይነት ሃይማኖታዊ ግኑኝነት እንዳለው ባላውቅም የሃውልት ጉዳይም ተነስቷል ።
ይህን ለማድረግ ደግሞ ቤተክርስቲያን የልጆቹን ሙሉ የዓለም ስማቸውን ከነ ክርስትና ስማቸው ፣ የልጆቹን በወቅቱ ያሳዩትን የእምነት ተጋድሎ የመሳሰሉት ነገሮች በሙሉ በተሟላ መልኩ ተደራጅተው ተጽፈው ይቀርባሉ ። ቅዱስ ሲኖዶሳችን የግብጾቹን ሰማዕታት የግብጽ ኦርቶዶክስ ብሎ የተቀበለ ሲሆን የኢትዮጵያን ግን የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ብሎ ነው የተቀበለው ። ምክንያቱም እንዲህ አይነት ተጋድሎ በተፈፀመ ጊዜ የሰማዕትነትን ክብር ሰጥተው ፣ ገድላቸውንም ጽፈው ለትውልድ የማቆየት ታሪክ ያላቸው አምስቱ ጥንታውያኑ የኦረንትያል አብያተክርስቲያናት ብቻ ስለሆኑ ነው ። ይህም ማለት እንዲህ አይነት ባህልም ሆነ ስርአት በሌሎች ዘንድ አይታወቅም ማለት ነው ። ከሟቾቹ ውስጥ ከላይ የጠቀስናቸውን ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን ከመፈጸም ማሟላት ግድ ነው ።

አሁን እኒህን የሟች ልጆችን እንርዳ ። እናቋቁም ። እኛ ጀምረናል እናነተ ደግሞ ቀጥሉ ። ውጤቱን በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እናየዋለን ። የዛሬው 2600 ብር እመቤቴ ምስክሬ ናት ማርያምን ነው የምላችሁ ተትረፍርፎ ባናየው ምን አለ በሉኝ ።

ጅማ እያለሁ ለኮሄ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን ከመንበር ጀምሮ አብዛኛውን ንዋያተ ቅዱሳት እችላለሁ ያለችኝ እህቴ አሁንም ልጆቹ ጋር ይዘኸኝ ሂድ ብላኛለች ። ምን እንደሚከሰት አላውቅም ። ደስ ሲል ሐብት ከክርስትና ጋር ሲስማማ ። አረ እንደው የእኔ እህት ለአንቺ ወለተ አማኑኤልና ለባለቤትሽ ፍቅረ ሥላሴ እንዲያው ልዑል እግዚአብሔር ጨምሮ ጨማምሮ እድሜውን ፣ ሀብቱንና ጤናውን ይስጣችሁ ። አሜን ።

ማን ነበር ” ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻውን በቂ ነው ” ያለው ? ጀምሩ እንግዲህ ።
ቤተክርስቲያንም ኃላፊነቷን ትወጣ ። በመንፈስቅዱስ የወለደቻቸውን ልጆቿን ትከታተል ። ህጻናቱ አሁንም ኦርቶዶክሳውያን ናቸው ። ባለቤቱም ብርቱኳንም እንዲሁ ።
ኃሣቡን ያፈለቀው እስካሁን በአካል የማላውቀው በስልክ ብቻ የማውቀው ወንድማችን መሐመድ ካሳ ነው ። እኔም የመሐመድን ሐሳብ በመደገፍና በማጠናከር እንዲሁ እላለሁ ።

ማኅበረ ቅዱሳን ልጆቹን በማስተማር በኩል ያውም በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤት እስከ መጨረሻው ኃላፊነት ብትወስዱ ። ምክንያቱም ካሁኑ በልጆቹ ላይ ሌሎች ሽሚያ የመጀመር አዝማሚያ እየታየ ስለሆነ ብዬ ነው ። እስካሁንም የእናትየው የእምነት ጥንካሬ ይዞ ነው እንጂ ችግር አለ ። ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል አይደል የሚባለው ። እናም መፍጠን ነው ።

ይህች የልጆች እናት አሁን በተከራየችበት ቤት እንኳን እንግዶችን በደንብ እና በአግባቡ ለማስተናገድ አልቻለችም ። ትናንት የልደታ ሰንበት ትምህርት ቤት ሰንበት ተማሪዎች አንዲት ጠቦት አርደን የማጽናኛ መርሐግብር እንፈጽም ቢሉ አከራዩ ከኢትዮጵያዊነት ባህል ባፈነገጠ መልኩ አይደረግም ብሎ ሁሉን ማሳዘኑ አግባብም አይደለም ። የግድ ፕሮቴስታንት መሆን አለባት እንዴ ? ተው እንጂ ጎበዝ ። የከፋ ነገር ከመጣ ቤት እስክታገኝ እኔ እራሴ ቤቴን እለቅላታለሁ እንጂ የምን ማቨማቀቅ ነው ። እማምላክ ምስክሬ ናት ደግሞም ቤቴ አሳምሮ ይበቃናል ። ፓስተሮቹ መጥተው ሲዘምሩ ፣ ሲጸልዩም ፣ ማንም አልተቃወመም ። ምክንያቱም ሟች ሃይማኖቱ ስለሆነ መብታቸው ነው ። ኦርቶዶክሳውያኑ ሲመጡ የምን ማኩረፍና ያዙኝ ልቀቁኝ ነው ። እሷ የባሏን መብት ጠብቃ እናንተ እንፀልይ ስትሉ ሳትቃወም በክብር ተቀብላ እንደሸኘቻችሁ እናንተም የልጅቷን መብት አክብሩላት እንጂ ። መሐመድ ካሣ እኮ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው እንዲህ በዚህ ጉዳይ መከራውን የሚበላው ኢትዮጵያዊነቱ አስገድዶት እኮ ነው ። ተው እንጂ እንዲህ አይነት ኢትዮጵያዊ ባህል የለንም ።

እዚያው በቅርብ ያላችሁ አገልጋይ ካህናትና መምህራን ይህች እናት ቤት አግኝታ እስክትወጣ ድረስ አፅናኗት ። ልጆቿን ጎብኙ ። በተለይ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርት ፣ የግቢ ገብርኤል ፣ የበአታ ማርያም ፣ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልና የቀበና መድኃኔዓለም ሰንበት ተማሪዎች ምን ትጠብቃለችሁ ። እዚያው ከስራችሁ የተቀመጠችን እህት አጽናኗት እንጂ አይዞሽም በሏት ። እባካችሁ ሂዱና ዘምሩ ። “ማርያም ኃዘነ ልቡና ታቀልል” ብላችሁ ዘምሩ ። ዘምሩ እውነቴን ነው ። ዘማሪ ዲያቆን ልዑልሰገድ ዛሬ ብሩንም ሰጥቶ የደረገው እንዲሁ ነው ። ዘምሮ አፅናንቶ ፣ ነው የወጣው ።

እንደተለመደው ይህ ጽሑፍ ብዙ ሰዎች እንዲያዩት Share መደረግን ይፈልጋል ። በጉዳዩ ዙሪያ ተሳትፎ እያደረግህ ያለኸውና በእምነት ባትመስለንም በኢትዮጵያዊነትህ መልካሙን ሁሉ በማድረግ ላይ ያለኸው ወንድማችን መሐመድ ካሣ ፣ በሥነ ጽሑፋችሁ ችግራቸውን ለዓለም ሕዝብ ያሳወቃችሁ ዲን ዳንኤል ክብረትና ያሬድ ሹመቴን ሳላመሰግን አላልፍም ።

ይኸኛውን ጽሑፌን ቁጥር ፩ም አይደል ያልኩት ። ቁጥር ፪ ጽሑፌንም ይከተላል ። እንዲሁ ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ ፣ ነገር ግን በሚያምነው እምነቱና በንጹሕ ኢትዮጵያዊነቱ ብቻ በግፍ ስለተሰዋ ሌላ ኢትዮጵያዊ አሳዛኝ ታሪክ ይዤላችሁ እቀርባለሁ ። በጣም አሳዛኝ ጉዳይም አለውና ጠብቁኝ ።
ቁጥር 3 ም አለኝ በግፍ የተገደለ ሌላውን አሳዛኝና ተደብቆ እንዳይቀር የምፈልገው እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ተጠርቼ ከዘማሪ ዲን ልዑል ሰገድ ጋር በመሄድ ስናለቅስ ውለን ስለመጣንበት ታሪክም ደግሞ በቀጣይ ይዤላችሁ እቀርባለሁ ። እስከዚያው ሰላም ሁኑልኝ ጓደኞቼ ። አሜን በቸር ያቆየን ።
★★★ እነሆ የባንክ ሂሳብ ቁጥሩ ★★★
ወ/ሮ ብርቱካን ጌቱ ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
አዋሬ ቅርንጫፍ የባንክ ሂሳብ ቁጥር
1000126433108
+251911608054 የእጅ ስልኬ ነው ። ማንኛውንም አስተያየት ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ ። አክባሪ ወንድማችሁ ።
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ሚያዝያ 30/8/2007 ዓም
አዲስ አበባ — ኢትዮጵያ

The post ኢትዮጵያዊ ማንነታችን የሚፈተንበት ቁጥር ፩ (እጅግ አስቸኳይ በደንብ በጥሞና እስከመጨረሻው ድረስ መነበብን የሚፈልግ ታሪክ) appeared first on Zehabesha Amharic.

በጋሞጎፋ ዞን በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እየታደኑ እየታሰሩ ነው

0
0

ethiopia-blue-party-300x164በጋሞጎፋ ዞን በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እየታደኑ እየታሰሩ መሆኑን የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡ ከትናንት ሚያዝያ 30/2007 ዓ.ም ጀምሮ ጋሞ ጎፋ ዞን ጎፋ ወረዳ ሳውላ ከተማው ውስጥ በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች መታሰራቸውን የጋሞ ጎፋ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በትናንትናው ዕለት በጋሞጎፋ ዞን ዳራማሎ ወረዳ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ 17 የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ታስረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጋሞጎፋ ዞን ቦንኬ ወረዳ ለፖሊስ ‹‹ለሰማያዊ ፓርቲ የሚቀሰቅስ ማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ውሰዱ›› የሚል ትዕዛዝ መተላለፉን የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡

The post በጋሞጎፋ ዞን በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እየታደኑ እየታሰሩ ነው appeared first on Zehabesha Amharic.

መርካቶ በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ወድቃለች

0
0

ህልማቸው በሜዲትራንያን ባህር የተዋጠው 7ቱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች
ከኤልሳቤት እቁባይና አለማየሁ አንበሴ

በቅርቡ በሜዲትራኒያን ባህር ከዘጠኝ መቶ በላይ ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ ሰጥማ 28 ተጓዦች ብቻ በህይወት በተረፉባት ጀልባ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት መካከል በአደጋው የሞቱት የሰባት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አሳዛኝ መርዶ የተሰማው ከትላንት በስቲያ ነበር፡፡ የሰባቱም ሟቾች የትውልድ ሰፈር ደግሞ በአዲስ አበባ መርካቶ በሚገኘው የአባኮራን ሰፈር ውስጥ ነው፡፡ በትላንትናው ዕለት የሟቾች ቤተሰቦችን ለማነጋገር ወደ አካባቢው ስንሄድ ሰባት ድንኳኖች ተርታውን ተተክለው ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድና ጓደኞች ለቅሶ ተቀምጠው ነበር፡፡
merkato
ከሊቢያ ባህር ዳርቻ ተነስታ ጣሊያን ልትደርስ ስትል በሰጠመችው ጀልባ ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት የአባኮራን ሰፈር ልጆች መካከል ዘመን ኢብራሂም የተባለው ወጣት በአስገራሚ ሁኔታ ህይወቱ ሊተርፍ ችሏል፡፡ የጀልባዋን መስጠም አስመልክቶ በአልጀዚራ በተሰራጨ ዘገባ፣ ልጁ ከአደጋው ተርፎ በእርዳታ ሰራተኞች ድጋፍ ሲደረግለት ታይቶ ነበር። ይሄኔ ነው አብረውት የሄዱት የሰፈሩ ልጆች የት ገቡ የሚለው ጥያቄ በቤተሰብና በጓደኞች ዘንድ የተነሳው፡፡ ቀደም ሲል በተመሳሳይ መንገድ በባህር ተጉዘው ጣሊያን የገቡ የሰፈር ልጆች ባደረጉት ማጣራት ግን ከዘመን ኢብራሂም በስተቀር ሁሉም ባህር ውስጥ ሰጥመው እንደሞቱ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡ ወጣቱ ዘመን ኢብራሂም ተዓምራዊ በሚመስል ሁኔታ ነው ህይወቱ የተረፈው፡፡ ወደ ባህሩ ሲወድቅ በአጋጣሚ ውሃው ላይ ስትንሳፈፍ ያገኛትን አንዲት ጀሪካን ይዞ ለ2 ሰዓታት ያህል ራሱን ለማዳን ጥረት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ነው የነፍስ አድን ሰራተኞች የደረሱለት፡፡ እስከዚያው ግን ብዙ በመሰቃየቱ አሁንም በሙሉ ጤንነት ላይ እንደማይገኝ ጓደኞቹ ነግረውናል፡፡ ዘመን ኢብራሂም አሁን የሚገኘው በጣሊያን ነው ተብሏል፡፡መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ለማሻሻል አውሮፓን አልመው ከሰፈራቸው የወጡት 9 ወጣቶች ሲሆኑ ስምንቱ በአደጋው እንደሞቱ ቢነገርም የአንደኛው ወጣት ወላጆች ግን “ልጃችንን በቲቪ አይተነዋል፤ አልሞተም” በማለት መርዶውን አልተቀበሉትም፡፡

አብዱል ጅላል ወጉ ወይም በሰፈር ስሙ ሙራድ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን በቀን ስራና በሱቅ በደረቴ ይተዳደር ነበር፡፡ ኑሩ መሀመድ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ የትምህርት ክፍል አንድ አመት ተምሮ ቤተሰብ ለመርዳት ትምህርቱን አቋርጦ ነው የተሰደደው፡፡ አብዱልከሪም ዘይኒ ደግሞ የ20 ዓመት ወጣት ሲሆን በቀለመወርቅ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነበረ፡፡ ሰይድ ይመር የ22 ዓመት ወጣት ሲሆን በተለያዩ የጉልበት ስራዎች ራሱንና ቤተሰቦቹን ያስተዳድር ነበር ተብሏል፡፡ አሊ መሀመድ የ26 ዓመት ወጣት ነበር፡፡ የሚሰራበት ሱቁ እንዲፈርስ በመወሰኑ ነው እቃዎቹን ሸጦና ገንዘብ ተበድሮ ለስደት የወጣው፡፡ ነጃ ሳቢር አወል የ24 ዓመት ወጣት ሲሆን የተለያዩ ተባራሪ አነስተኛ የንግድ ስራዎችን በመስራት ይተዳደር ነበር፡፡ እንድሪስ አደም ደግሞ የ18 ዓመት ወጣት ሲሆን ከኢንፎኔት ኮሌጅ በቴክኒክና ሙያ ተመርቆ ስራ አጥ እንደነበር ከአካባቢው ያሰባሰብነው መረጃ ያመለክታል፡፡ የእነዚህ ወጣቶች መርዶ ሰሞኑን ቢነገርም ወላጆች፣ ቤተሰቦችና ጓደኞች መሸበር የጀመሩት ግን በሊቢያ በአይኤስ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን መርዶ ከተሰማ ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ በየጊዜው ወጣቶቹ በአይኤስ እጅ ወድቀዋል የሚል መረጃን ጨምሮ ብዙ ያልተጣሩ ወሬዎች ይመጡ ስለነበር፣ ቤተሰብና ጓደኞች በስጋት ውስጥ ነው የከረሙት። አብዱ ሀሰን አሊ የተባለው የሟቾቹ አብሮ አደግ መርዶውን እንዲያረዳ ከጣሊያን ሲደወልለት ሊሸከመው የማይችል ዱብ እዳ እንደወረደበት ነበር የቆጠረው፡፡ “ ማን ማንን ሊያፅናና ነው?” የሚል ከፍተኛ ጭንቀትና ፍርሀት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡

ሆኖም መርዶው በድንገት ደርሶ ቤተሰብ ከሚጎዳ በሚል የአካባቢውን ሽማግሌዎች ሰብስቦ መርዶው ከትላንት በስቲያ እንዲነገር ማድረጉን ገልጿል፡፡ በመርካቶ አባኮራን ሰፈር መርዶው ለቤተሰብ ከተነገረበት ሰአት ጀምሮ በከፍተኛ ሀዘን የተዋጠ ሲሆን ሰባቱም ሟቾች ጎረቤታሞች በመሆናቸው በመደዳ በተጣለው ሰባት ድንኳን ሰዎች ሀዘን እየደረሱ ነው፡፡ ይሄ አሳዛኝ ክስተት ለመላው ኢትዮጵያውያን መሪር ነው – በተለይ ደግሞ ለወላጆችና ቤተሰቦች፡፡ ህልማቸው በሜዲትራኒያን ባህር የተዋጠው ወጣቶች ወላጆች እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ብዙዎቹ ልጆቻቸው የሚጦሯቸው ናቸው፡፡ መተዳደሪያ ያላቸው ደግሞ ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ በጥበቃ፣ በፅዳት፣ ልብስ በማጠብ፣ ጉሊት በመቸርቸርና እንጀራ በመጋገር ነው የሚተዳደሩት፡፡ ልጆቻቸው ሊቢያ፣ ቤንጋዚ ሲደርሱ ወደ አውሮፓ ለመሻገር በመቃረባቸው ገንዘብ እንዲልኩላቸው ጠይቀው፣ ከሰፈር ሰዎች ተዋጥቶና አንዳንድ ወላጆች በዋስ ተበድረው እንደላኩላቸው ለማወቅ ችለናል፡፡ ወጣቶቹ ሊቢያ ለመድረስ እያንዳንዳቸው ወደ 80ሺ ብር የሚጠጋ ገንዘብ እንደፈጀባቸው ታውቋል፡፡ በህይወት የተረፈው የዘመን ኢብራሂምን ወላጆች ለማግኘት ብንሞክርም ልጁ ወላጆቹን ያጣው በለጋ እድሜው እንደነበርና ጎረቤቶች እንዳሳደጉት ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ በጓደኞቻቸው ላይ ያጋጠመው አደጋ ያስደነገጣቸው አብሮ አደጎቻቸው በግራ መጋባት መንፈስና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ያሉ ሲሆን አሁንም ጣሊያን መግባት የቻሉ ሁለት የሰፈሩ ልጆች ወደ ሌላ ከተማ ለመሻገር ሁሉም የቻለውን አዋጥቶ እንዲልክላቸው በመማፀናቸው የአካባቢው
ነዋሪዎች የሚችሉትን እያደረጉ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡

ምንጭ – በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ

The post መርካቶ በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ወድቃለች appeared first on Zehabesha Amharic.

Viewing all 15006 articles
Browse latest View live