Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all 15006 articles
Browse latest View live

Health: ኩላሊትዎን ሊጎዱ የሚችሉ 7 ነገሮች

0
0

(በዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም ቱፈር)
Dr Honilet
1. በቂ ፈሳሽ አለመውሰድ

በቂ ውሃን አለመጠጣት የኩላሊት ሥራ የሆነውን አላስፈላጊ ቆሻሻን ከሰውነታችን ማስወገድ በሚገባ እንዳያከናውን ስለሚያደርግ ቆሻሻው በኩላሊታችን ውስጥ ተከማችቶ ጉዳት እንዲያስከትል ያደርጋል፡፡

2. የውሃ ሽንትን መቋጠር

የውሃ ሽንትን ማስወገድ በሚገባን ጊዜ ሳናስወግድ የምንይዘው ከሆነ እና ይህን ተግባር የምናዘወትር ከሆነ የሽንት ፊኛችንም ሆነ ኩላሊታችንን አደጋ ላይ የምንጥል መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡

3. ጨው የበዛበትን ምግብ መውሰድ

ጨዋማ ምግቦችን መመገብ የኩላሉትን ጨውን (sodium) ከሰውነታችን የማስወገድ ሥራ ጫና እንዲበዛበትና ሲቆይም ለችግር እንዲጋለጥ ያደርጋል፡፡

4. ካፊን በብዛት መውሰድ

በሚጠማን ጊዜ ውኃ ከመጠጣት ይልቅ ለስላሳ መጠጦችን እንደ ጥም ቆራጭነት እንጠቀማለን፡፡ ካፌን የደም ግፊት መጠናችንን በመጨመር ኩላሊትን ይጎዳል፡፡

5. ሕመም ማስታገሻ አለአግባብ መውሰድ

ቀላል ለሚባል የሕመም ስሜት ሕመም ማስታገሻዎችን መውሰድ አላስፈላጊ እና አልፎ ተርፎም ከባድ የሆነ የኩላሊት ጉዳትን ሊያደርስ ይችላል፡፡

6. የአልኮል መጠጥን በብዛት መጠጣት

ከልክ ያለፈ የአልኮል መጠጥን ማዘውተር የኩላሊት ችግር ያስከትላል፡፡

7. ሲጋራ ማጤስ

ለኩላሊት መድረስ የሚገባውን የደም መጠን ስለሚቀንስ ሲጋራ ማጤስ እንዲያቆሙ ይመከራል፡፡

ጤና ይስጥልኝ


በለገጣፎ ከተማ ከ32,000 ሺህ በላይ ዜጐች ቤት አልባ ሊሆኑ ነው

0
0

(ፍኖተ ነፃነት) የአዲስ አበባ ተዋሳኝ በሆነው ለገጣፎ ከተማ ከ3,000 ሺህ በላይ ቤቶች እንዲፈርሱ በመወሰኑ ከ32,000 ሺህ በላይ ዜጐች ቤት አልባ ሊሆኑ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ገለፁ፡፡
legetafo Addis ababa
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ለ12 ዓመታት በአካባቢው መኖሪያ ቀልሰው ኖረዋል፡፡ ሆኖም “የከተማ ሰው ወሮናል” የሚል ተቃውሞ በገበሬው እንዲነሳ ያደረጉ የከተማው ባለሥልጣኖች በ2 ቀናት ውስጥ ቤታችን ሊያፈርሱ ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡ የካ ሰዴን ወረዳ የሚገኙት የጉራ፣ሰፈራ፣ድሬ፣ ዳሌ እና ቀርሳ የሚባሉ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ወደ 3000 ሺህ የሚጠጉ ቤቶች እንዲፈርሱ ምልክት ተደርጎባቸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ቅዳሜ ህዳር 13 ቀን 2007ዓ.ም በከተማው በመሰባሰብ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ በነጋታው እሁድ ዕለትም ከ1000 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች በመሰባሰብ ባጋጠማቸው አደጋ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ የነዋሪዎቹን ችግር ለማዳመጥ ፈቃደኛ ያልሆኑት የከተማው የመንግስት ባለስልጣናት ግን በቅዳሜው በስብሰባው ላይ ባለመገኘታቸው ነዋሪዎቹ በነጋታው እሁድ ከ1000 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች በወረዳው ጽ/ቤት በመገኘት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ሰኞ ህዳር 15 ቀን 2007 ዓ.ም በድጋሚ በመሰባሰብ 10 ተወካዮቻቸውን ወደ 4 ኪሎ ፓርላማ መላካቸውን በስፍራው የተገኘው የፍኖተ ነፃነት ዘጋቢ አረጋግጧል ፡፡

ቆንጆ መጽሔት ተከሰሰች

0
0

ከመጽሔቷ ዋና አዘጋጅ ቴዎድሮስ ካሳ
1507102_562094813935307_9108390875166530007_nከሁለት ሳምንት በፊት ከማዕከላዊ የምርመራ ቢሮ ከወዲያኛው ጫፍ የደወለው ሰው እንደነገረኝ ‹‹ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ነው›› ብሎ ደወለልኝ፡፡ ደዋዩ ቆንጆ መጽሔት መሆኑን ካጣራ በኋላ ዋና አዘጋጇ ስልክ ላይ ብደውል ዝግ ነው ፤ ጥር ወር ላይ ባወጣችሁት ዘገባ እኛ ጋ ክስ ተመስርቶባችኋል አለኝ፡፡ ስለሆነም ለዋና አዘጋጇ መልዕክት አድርሱ መጥታ ቃሏን ትስጥ አለኝ፡፡ ለጊዜው በቅርብ እንደሌለች ነገርኩት፡፡ ‹‹እሺ›› ብሎ ስልኩን ዘጋው፡፡ ድጋሚ ባለፈው ሳምንት አንድ ስልክ ተደወለ፡፡ በወቅቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለነበርኩ ስልኩን ማንሳት አልቻልኩም፡፡ ስወጣ ግን ደወልኩ፡፡ ስልኩን ያነሳችው ሴት ‹‹የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዋና (ማዞሪያ ስልክ)›› መሆኑን ነገረችኝ፡፡ እንግዲህ ይህ ስልክ ግቢ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ የሚጠቀሙበት በመሆኑ እንደ እኔ ሞባይሉ ላይ ሚስድ ኮል አይቶ መልሶ ለደወለ ማን እንደደወለለት ገና ተጠያይቆ ነው የሚታወቀው፡፡


ትናንት የደወለችው ግን ቁጣ በተቀላቀለው ንግግር ‹‹ለምንድነው ስልክ የማታነሱት›› አለች፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኢንተርቪውና ሌሎች ጥሞና የሚፈልጉ (የስልክ ድምጽ የሚረብሹ) ስራዎች ላይ ለሆነ ጋዜጠኛ ስክል ያለማንሳት የተለመደ ጉዳይ መሆኑን ላስረዳት ሞከርኩ፡፡ ስንትን በስንት እንዳባዛችው ባይታወቅም በተደጋጋሚ ጊዜ መደወሏን ተናግራ ‹‹ለረቡዕ ጠዋት ማዕከላዊ መጥተው ቃሎትን እንዲሰጡ›› አለች፡፡


በዚህ ጉዳይ ጥር ላይ ያሳተማችሁት ዕትም ስለተባልኩ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ያሳተምናቸውን ሁለት ዕትሞች ደግሜ ለማየት ሞከርኩ፡፡ የታየኝ ነገር የለም፡፡ እንግዲህ እነሱ የታያቸው ነገር ይኖራል፡፡ በዚያ ላይ ከሳሽ ማን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ አቃቤ ህግ? መንግስት? ግለሰብ? ማህበር?. . . የታወቀ ነገር የለም፡፡


ባለፈው ዓመት የዛሬው ኢቢሲ የአምናው ኢቲቪ በሰራው ተከታታይ የዶክመንተሪ ፊልም ምክኒያት በብዙ መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ ክስ ተመስርቶ የቆንጆ መጽሔት አዘጋጆችን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ተመስገን ደሳለኝንና ብዙ ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ዶክመንተሪው የግል የህትመት ውጤቶችን በሙሉ ሀጢአተኛ አድርጎ ስለፈረጀ ማተሚያ ቤቶች ጋዜጣና መጽሔቶችን ማተም ፈርተዋል፡፡ ዶክመንተሪው የግል ሚዲያውን ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የግንቦት 7 እና የሻዕቢያ ተላላኪ፤ የታሰሩ ሙስሊሞችን ገና ጉዳያቸው በፍ/ቤት እየታየ ባለበት ሁኔታ ላይ አክራሪ፤ ብሎገርና ሌሎችንም ስም እየሰጡና እየፈረጁ በፍ/ቤቶች ላይ ጫና እስከማሳደር የሚደርስ ዘገባዎች ሲሰራጩ ኢቲቪ ነውና ማንም አይጠይቀውም፡፡ የግሉ ሚዲያ ላይ ሲሆን ግን. . .
አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ቅዳሜ ለንባብ እንዳበቃው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ላይ አሁንም ክስ የሚመሰረትባቸው የህትመት ውጤቶች መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡ በዚህ መልኩ ወደ ፊት በኢትዮጵያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ውጪ የህትመት ውጤቶች ስለመኖራቸው እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡


ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሳደድ የቀዳሚነቱን ስፍራ የተቆናጠጠችው ሀገራችን የወደፊት የዴሞክራሲ እጣ ፈንታዋ ምን ይሆን? ይህ ነገር በዚሁ እንዳይቀጥል፤ የጋዜጠኞች እስርና ስደት እንዲቆም ከመንግስት ኃላፊዎች ጋር ቀርቦ ለመነጋገር የተደረገው ጥረት በኃላፊዎቹ ግትርነት መፍትሔ ማግኘት አልቻለም፡፡ ‹‹የተሰደደና የታሰረ ጋዜጠኛ የለም›› እስከማለት ደርሰዋል አይናቸውን በጨው አጥበው፡፡ የጋዜጠኞች እስርና ስደት የሀገርንና የመንግስትን ስም ጥቁር ጥላሸት ከመቀባት ውጪ ለሀገርም ለህዝብም የሚጠቅም ነገር ያለመኖሩን በተደጋጋሚ ቢነገርም ሹማምንቱ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል፡፡
የነገው የማዕከላዊ ቀጠሮዬን እያሰብኩ ይህቺን ሰነቅኩላችሁ፡፡

 

በአማራ ክልል ቅርሶች በከፍተኛ ሁኔታ እየዘረፉ ከሐገር እየወጡ ነው፡፡

0
0

ዳር ፲፮(አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል የደቡብ ወሎና የሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳዎችና አብያተክርስቲያናት ተገቢ ጥበቃ ባለማግኘታቸው የተለያዩ ቅርሶች የተዘረፉና የጠፉ መሆኑን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በአመት አንድ ጊዜ በሚዘጋጀው የቅርስ ጉባኤ ላይ ገለጸ፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በተለያዩ ወረዳዎች 37 ቅርሶች መሰረቃቸውን ይፋ ያደረጉት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ አለበል ደሴ ፣በክልሉ ከ2001 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ 2006 መጨረሻ ባለው ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች 124 መድረሳቸውን ተናግረዋል።

artበክልሉ ብቸኛ የሆነው የደሴ ሙዙየም በስተደቡብ አቅጣጫ ጫካ በመሆኑና ዙሪያውም ምንም ዓይነት አጥር ስለሌለውየጥበቃ ቢሮው ተሰብሮ በውስጡ የነበሩ ሁለቱም የጦር መሣሪያዎች ከነሙሉ ጥይታቸው ከመሰረቃቸውም በላይ እስከአሁንም አለመገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ቅርሶች በመስታውት ዉስጥ ተቆልፈው ስላልተያዙ ለአቧራና ለአላስፈጊ ንክኪ መጋለጣቸውም ሃላፊው ተናግረዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ ጥንታዊ አብያተክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች ተገቢውን ጥበቃ ባለማግኘታቸው በሌቦች መሰረቃቸውንና አብዛኛዎቹ አለመገኘታቸውን በውይይቱ ላይ የተወሳ ሲሆን የአንኮበር ማሪያም ቤተክርስቲያን 3 የብር መቋሚያዎችና 7 የብር ጸናፅልች፤ በአንፆኪያ ወረዳ በ03 ቀበሌ አጥቆ በዓታ ማሪያም ቤተክርስቲያን 9 የብራና መጽሃፍት፣ 3 ሌሎች የመገልገያ መጽሃፌት እና 1 የመፆር የነሃስ መስቀል ተሰርቀው እስካሁን አልተገኙም።

በሞረትና ጅሩ ወረዳ የሚገኘው ይማደጋ ቅደስ ሚካኤሌ ቤተክርስቲያን ውስጥ ዘራፉዎች ገብተው 2 የቅዱስ ሚካኤል ጽላት ፣ 1 የመስቀለ እየሱስ ጽላት ፣ 3 የነሃስ የመፆር መስቀል፣ 1 መጎናፀፉያ የተዘረፉ መሆኑ ለአብነት በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ በቅርስ ዘረፋው የባለስልጣናት እጅ አለበት ሲሉ ሃሳብ ያነሱት ተወያዮች እንዴት በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሳተፉ ባለስልጣናት ቅርስ ዘረፋን ይከላከላሉ ተብሎ እንዴት ይገመታል ሲሉ ሞግተዋል፡፡

በጋይንት አካባቢ ብቻ ከ30 ያላነሱ አብያተክርስቲያናት ቅርሶች መዘረፋቸውን ጥቆማ እንደደረሰው የክልሉም ሆነ የፊደራል ባህል፣ቱሪዝምና ፓርኮች ልማት ሚኒስቴር ቢያሳዉቅም ጉዳዩ ተጣርቶ የተወሰደ እርምጃ የለም፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ የቅርስ መገኛ ተቋማት 3ሺ እንደሚደርሱ ቢገመትም ሙዙየም በማሰራት ቅርሶቻቸውን በጥንቃቄ ለእይታ እያቀረቡ ያሉት ግን 13 ብቻ ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ በብሄራዊ ሙዚየም ውስጥ ይገኙ የነበሩ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚዘክሩ መጽሃፍት በተቀነባበረ መልኩ በርካሽ ዋጋ ለነጋዴዎች የተሸጡ መሆናቸው የተዘገበ ሲሆን፣ እስካሁን ለኢሳት በደረሰው መረጃ የጆብ ሎድፍ 1664፣ 1700፣ 1800፣ የጀምስ ብሩስ፣ የካርሎ ሮሲኒ፣ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ይታተሙ የነበሩ የቄሳር መንግስትና የሮማ ብርሃን የተባሉ ጋዜጦች፣ 2 ሺ ኪሎ ግራም ይመዝናሉ የተባሉ የአጼ ቴዎድሮስ፣ የአጼ ዮሃንስና የአጼ ሚኒሊክ ደብዳቤዎች ተቸብችበዋል።

Source:: Ethsat

ጋዜጠኛውን ደብድቧል የተባለው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በዋስ ተፈታ

0
0

(ሰንደቅ ጋዜጣ) ነሐሴ 20 ቀን 2006 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ገልፍ ኢዚዝ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላይ የግል ተበዳይ በሆኑት ጋዜጠኛ ግዛቸው እሸቱ ላይ የቀላል የአካል ጉዳት አድርሰዋል ተብለው በወንጀል ተጠርጥረው ቦሌ ምድብ በመጀመሪያ ደረጃ 4 ወንጀል ችሎት ሕዳር 16 ቀን 2007 ዓ.ም ቀርበው ጉዳያቸው ተሰምቷል።
Daniel tegegne
የወንጀል ችሎቱ ግራና ቀኝ አከራክሮና የሶስት ምስክሮችን ቃል ካዳመጠ በኋላ ሕዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም ለብይን ቀጠሮ ሰጥቷል።
ከዚህ በፊትም በካራማራ ፖሊስ ጣቢያ ለምርመራ የተጠራው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በቀረቡ ጊዜም በ3ሺ ብር ዋስትና መለቀቃቸው ይታወሳል።

በጋምቤላ ክልል ያለው የኤች አይቪ ስርጭት በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው ስርጭት በላይ መሆኑ ተገለፀ

0
0

በ2 ሰዓታት 2ሺ ሰዎችን ለመመርመር ታቅዷል

በሀገራችን ለ26ኛ ጊዜ የፊታችን ህዳር 22ቀን 2007 ዓ.ም የሚከበረውን የአለም የኤድስ ቀን አስመልክቶ ትናንት በካፒታል ሆቴል እና ስፓ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የኤች አይ ቪ ስርጭት 1ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን፤ በጋምቤላ ክልል ያለው ስርጭት ግን 5 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ተገኝቷል። በክልሉ ያለው የኤች አይ ቪ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ በተለይ በሴት ወጣቶች ላይ ያለው ስርጭት አሳሳቢ ነው ተብሏል። በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ ለኤች አይቪ ተጋላጭ ናቸው በተባሉት ሴቶች ዘንድ ያለው ስርጭት 8 በመቶ ሲሆን፣ በወንዶች ላይ ደግሞ 5 በመቶ መሆኑ ተገልጿል። በክልሉ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ 380 አዲስ የኤች አይቪ ተጠቂዎች መመዝገባቸውንም ይፋ ሆኗል።
news
በክልሉ ያለው የኤች አይቪ ስርጭት ከፍተኛ እንዲሆን ያደረገው በህብረተሰቡ ዘንድ ስለኤች አይ ቪ በሽታ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ነው ያሉት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲዱሞ አደር፣ ከዚሁ በተጨማሪም ክልሉ ከተለያዩ አምስት ብሔረሰቦች የተዋቀረ እንደመሆኑ የየብሔረሰቡ ባህል በዚህ ስርጭት ከፍተኛ መሆን የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል። በክልሉ በተለይ የውርስ ጋብቻ የተለመደ መሆኑን የገለፁት አቶ ዲዱሞ፤ በዚህም አንድ ወንድ ሲሞት የሞተበትን ምክንያት ሳያጣራ ልጅ ወይም ወንድም የዚያን ወንድ ሚስት ስለሚወርስ ይህም የበሽታውን ስርጭት ከፍ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ሆኗል። ከሌሎች አካባቢዎች ለየት ባለመልኩ ወንዶች እና ሴቶች በነፃነት የሚገናኙበት “ፍሪ ዴይ” የሚባለው ባህልም ሌላኛው የዚህ ምክንያት እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል ያለውን የኤች አይ ቪ ስርጭት ለመግታት ያግዝ ዘንድም የዘንድሮው የዓለም የኤድስ ቀን በጋምቤላ ክልል “አንድም ሰው በኤድስ እንዳይያዝ፣ እንዳይገለል እና እንዳይሞት ኃላፊነታችንን እንወጣ” በሚል ቃል ይከበራል። በዚህ በዓል ላይ ከፍተኛ የሆነ የምክር አገልግሎት እና ምርመራ የሚካሄድ ሲሆን፤ ይህንንም በአለም አቀፍ የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ለማስመዝገብ ታስቧል። ከበዓሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ህዳር 21 ቀን 2007 ዓ.ም በጋምቤላ ስታዲየም በሚካሄደው የምክርና ምርመራ አገልግሎት በ8 ሰዓታት ውስጥ 2ሺህ ሰዎችን ለመመርመር ታስቧል። ይህን በማድረግም ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት አሜሪካ እና አርጀንቲና በ8 ሰዓታት ውስጥ 1ሺ 380 ሰዎችን በመመርመር ይዘውት የነበረውን ሪከርድ ለማሻሻል ታስቧል።

ሰዎች በእለቱ ተገኝተው ምርመራ እንዲያደርጉ በመቀስቀስ እና ወደ ምዝገባም በመግባት ላይ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ዲዱሞ፣ በተያዘው እቅድ መሠረት እያንዳንዱ ቀበሌ እንዲሁም ሁለት ቤተክርስቲያናት እያንዳንዳቸው ከሁለት መቶ በላይ ሰዎችን እንዲያስመረምሩ ይደረጋል። ይህ የምክር እና ምርመራ አገልግሎት በክልሉ ለአንድ ሳምንት የሚቀጥል ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከ5ሺህ በላይ ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ በአለማችን ከተቀሰቀሰ ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ 78 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 35 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ 800ሺህ ኢትዮጵያውያን ለቫይረሱ የተጋለጡ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን መካከልም 200ሺዎች ህጻናት ናቸው። በአለፈው የፈረንጆች 2013 ዓ.ም ብቻ በአለማችን ላይ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን አዲስ የቫይረሱ ተጠቃሚዎች መመዝገባቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል በፖስታ የተላከውን የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ደብዳቤ አልቀበልም አለ

0
0

ነገረ ኢትዮጵያ

blue partyየአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል 9ኙ ፓርቲዎች ህዳር 21 ለሚያደርጉት የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ በፖስታ ቤት የተላከለትን ደብዳቤ አልቀበልም ማለቱን የስብሰባው አስተባባሪ የሆነው የመኢዴፓ ፀሀፊ አቶ ዘመኑ ሞላ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ህዳር 21/2007 ዓ.ም ለሚያደርጉትና መኢዴፓ ለሚያስተባብረው ስብሰባ ረቡዕ ህዳር 10 የመኢዴፓ አመራሮች ደብዳቤውን ለማስገባት ሄደው የነበር ቢሆንም አቶ ማርቆስ ብዙነህ እና እሳቸውን ተክተው ሲሰሩ የነበሩት አቶ ፈለቀ ታመዋል በሚል የከንቲባ ጉዳይ የካቢኔዎች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ማሳወቂያ ደብዳቤውን አንቀበልም ማለታቸው ይታወቃል፡፡

በተመሳሳይ ህዳር 12 ወደ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ ያቀኑት የትብብሩ አመራሮች ደብዳቤውን የሚቀበላቸው ሲያጡ ጠረጴዛ ላይ ጥለውት የመጡ ሲሆን በፖስታ ቤት በሪኮመንዴ eg156846735et እንደላኩ የትብብሩን ፀኃፊ አቶ ግርማ በቀለን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ለአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል በፖስታ የተላከውን ደብዳቤ ቢደርስም አመራሮቹና ሰራተኞቹ ደብዳቤውን ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ፖስታ ቤት ድረስ በመሄድ እንዳረጋገጡ አቶ ዘመኑ ሞላ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ሰራተኞችና አመራሮች ፖስተኛው ደብዳቤው የሚሰጥበትን ቢሮ ሲጠይቅ ለማሳየት ፈቃደና እንዳልሆኑና በስተመጨረሻም ‹‹ተቀባይ የለውም ብለህ መለስ፡፡›› እንደተባሉት አቶ ዘመኑ ሞላ ገልጸዋል፡፡

አንድነትና መድረክ ተለያዩ

0
0

ሪፖርተር

ላለፉት ስድስት ዓመታት ገደማ ያህል በጋራ ለመሥራት ተስማምተው የተቃውሞ ጐራው ላይ በጋራ ሲሠሩ የነበሩት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የነበራቸውን አብሮ የመሥራት ስምምነት አቋርጠው ተለያዩ፡፡

UDJAEUPሁለቱ ፓርቲዎች የቀድሞው የአንድነት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ሰጥተውታል በተባለው አስተያየት የተነሳ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አስተያየቱን አንድነት ያስተባብል በሚል ከመድረክ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ለፓርቲዎቹ መለያየት ከፍተኛውን ድርሻ መውሰዱን የሁለቱ ፓርቲዎች ባለድርሻ አካላት መግለጻቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

ከሁለት ሳምንታት በፊት ዳግም የመድረክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለአንድነት እስከ ኅዳር 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ገደብ መስጠታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም መሠረት አንድነት ለመድረክ ኅዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፈው የመልስ ደብዳቤ፣ ከመድረክ አባልነት መውጣቱን ገልጾ መጻፉን የመድረክ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ‹‹ከመድረክ ጋር በይፋ ተለያይተናል፤ ፊርማችንን ቀደናል፤›› በማለት ከመድረክ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ለሁለቱም የፓርቲ አመራሮች ምርጫ በተቃረበበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ መውሰድ አጠቃላይ ሰላማዊ ትግሉን አይጐዳውም ወይ የሚል ጥያቄ ሪፖርተር አቅርቦ ነበር፡፡ የሁለቱም ፓርቲ አመራሮች ጉዳት ማስከተሉን ተቀብለው ነገር ግን ከአቅም በላይ በመሆኑ መለያየት መፍትሔ እንደሆነ አስረግጠው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህ ረገድም ‹‹ይሄ እኮ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የተቃውሞ ፓርቲዎች የጋራ ትብብር አለመኖር፤ ውህደት አለመኖር የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ይጐዳዋል፡፡ ይህንን እናውቀዋለን፡፡ ነገር ግን ትግሉን እየጐዳው ቢሆንም አብሮ የማይሄድና የማይሆን ነገር ሲታይ አብረህ መቀጠል አትችልም፡፡ መለያየት አለብህ፤›› በማለት ልዩነቱ በመስፋቱ መለያየቱ የግድ እንደሆነ አቶ አበበ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች ትግሉን እንደሚጐዳ ይታወቃል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ጥላሁን በበኩላቸው፣ ‹‹የተቃውሞ ጐራውን ለመጉዳት የተነሱና የተመኙ ሰዎች የሠሩት ሥራ ጠቅላላ አንድነትና መድረክን ወደ መለያየት ወስዷል፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሁለቱም ፓርቲ አመራሮች ወደፊት ስለሚያደርጉት የትግል አቅጣጫ የየራሳቸውን ዕቅድ ማዘጋጀታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹እኛ ቀድሞውኑ በአፍራሽ መልኩ የመጣውን እንዴት እንደምንቋቋምና እንዴት ትግላችንን በዚህ ጉዳት ምክንያት ሳይዳከም ሊቀጥል እንደሚችል የራሳችንን ሥራ ስንሠራ ስለቆየን ይህን ጉዳይ አሁን እንደ አዲስ አናየውም፡፡ በእኛ በኩል የራሳችንን ትግል በተጠናከረ ሁኔታ እንቀጥልበታለን፤›› በማለት አቶ ጥላሁን ቀጣይ ሥራቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ አቶ አበበ በበኩላቸው፣ ‹‹መድረክ አንካሳ ነው ያደረገን፡፡ ነገር ግን አንካሳ ሆነን ከምንቀጥል ባለን ነገር ሮጠን ምርጫውን እኛ ባለን መዋቅር ብንጋፈጠው የተሻለ ውጤት እናገኛለን፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡


ናሽናል ኤርዌይስ 50 በመቶ የባለቤትነት ድርሻውን ሸጠ

0
0

5692b01d9e74d575c8790b9b14ebc2a0_Lበኢትዮጵያ የግል በረራ አገልግሎት ውስጥ በመሳተፍ ከሚታወቁ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ናሽናል ኤርዌይስ 50 በመቶ ድርሻውን ሸጠ፡፡

ናሽናል ኤርዌይስ 50 በመቶ ድርሻውን የሸጠው በኢትዮጵያ የመጀመርያው የግል የበራራ አገልግሎት በማቋቋም ወደ ሥራ ገብቶ ለነበረው የጎሽ አቪዬሽን ባለቤት ለአቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ናሽናል ኤርዌይስ በአሁኑ ወቅት አራት አውሮፕላኖችን በመከራየት በአገር ውስጥ የበረራ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝና በአትራፊነት የሚታወቅ ነው፡፡

በአቶ ዳዊትና በናሽናል ኤርዌይስ መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት የባለቤትነት ድርሻውን መስጠቱ የኩባንያውን አቅም በማሳደግ አገልግሎቱን ለማሳደግ ያስችለዋል ተብሏል፡፡ እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ አቶ ዳዊት ለ50 በመቶው የባለቤትነት ድርሻ ግዢ ምን ያህል ወጪ እንዳወጡ ባይገልጽም፣ ስምምነታቸውን በቅርቡ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አቶ ዳዊት፣ ጎሽ አቪዬሽንን በመመሥረት በአገር ውስጥ የበረራ አገልግሎት ጀምረው የነበሩ ቢሆንም፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት አገልግሎቱ መቋረጡ ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት መቀመጫቸውን ዱባይ ያደረጉት አቶ ዳዊት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ ሲሆን፣ በተለይ በቅርቡ የራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ላይ 25 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ በመግዛት ከፍተኛ ባለአክሲዮን ሆነዋል፡፡

በዋናነት ግን ኢንቨስትመንታቸውን ዱባይ በማድረግ በአውሮፕላንና በሔሊኮፕተር የመለዋወጫ ዕቃዎች ቢዝነስ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በመድኃኒት አቅራቢነትም የሚታወቅ ኩባንያ ባለቤት ናቸው፡፡

በካፒቴን አበራ ለሜ የተቋቋመው ናሽናል ኤርዌይስ የመንገደኞች በረራ አገልግሎትን ጨምሮ የካርጎና የአየር አምቡላንስ አገልግሎቶችን በመስጠት በዘርፉ ልምድ ያለው ኩባንያ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ በበረራ አገልግሎት ላይ የሚገኘው ይህ ተቋም፣ የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት አባል ነው፡፡

Source:: Ethiopian Reporter

በቀለ ገርባ

0
0

የሚሊዮኖች ድምፅ ቀጣይ መርሀ ግብሮች

አቶ በቀለ ገርባ

10734019_734141523337451_8980381146422839409_n

አቶ በቀለ ገርባ

ነሐሴ 21/2003 ዓ/ም ከምሠራበት ቦታ በስልክ ተጠርቼ በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ ከሚጠራው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ተወስጄ ከአንዲት ትንሽ ጨለማ ክፍል ውስጥ ከተወረወርኩ በኋላ በማግስቱ አራዳ ወረዳ ፍ/ቤት ቀርቤ የሃያ ስምንት ቀን የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆብኝ ተፈቅዶላቸው ያም ሲያልቅ እንደገና ሌላ ቀጠሮ ተጠይቆ ተፈቅዶላቸው፣ የማይመለከቱኝን ጥያቄዎች ስጠየቅና ስመልስ ቆይቼ ጥቅምት 3/2004 በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቤ የክስ ወረቀት ደርሶኝ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተልኬ እነሆ እስከዛሬ ድረስ ዞን አንድ ቅጣት ቤት ተብላ በምትጠራው ቤት እገኛለሁ፡፡


የቀረበብኝ ክስ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 241 የተመለከተውን በመተላለፍ የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት ወንጀል ሲሆን ዝርዝሩ፡- “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦ.ነ.ግ/ አባል በመሆን ሶሎሎ ጐልቦ ሥልጠና ወስደሃል፤ በጥር ወር 2002 ዓ/ም በአምቦ ከተማ ኦ.ነ.ግ በቅርብ ወደ አገር ውስጥ አሸንፎ ይገባል፤ ከጐኑ ቆመን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት መጣል አለብን ብለህ መመሪያ ሰጥተሀል፤ በሐምሌ 2003 ዓ/ም ተማሪዎችንና ህዝቡን ለአመጽና ለብጥብጥ እንዲነሳሱ ቅስቃሳ አካሂደሀል፤ እንዲሁም በ2004 ዓ/ም በመላው ኦሮሚያ አመጽና ብጥብጥ በማስነሳት በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት መጣል አለብን በማለት ትዕዛዝ አስተላልፈሀል፤ በዚሁ ወር የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነትህን ሽፋን በማድረግ ቢሮህ ተገኝተው የመመረቂያ ጽሁፍ ሊሰጡህ የመጡትን ተማሪዎች በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት በሃይል ከሥልጣን እናውርድ በማለት መመሪያ ሰጥተሀል” የሚል ነው፡፡


እነዚህ የቀረቡብኝ ክሶች ፈጽሞ የሀሰት ውንጀላዎች መሆናቸውን ለማስረዳት በመጀመሪያ ደረጃ ትጥቅ ትግልና ሰላማዊ ትግልን አስመልክቶ ያለኝን አቋምና እምነት ባጭሩ ከገለጽኩ በኋላ በቀረቡብኝ ምስክሮችና የሠነድ ማስረጃ ላይ ያሉትን እውነታዎች አቅርቤ በአጭሩ የማጠቃለያ ሀሳብ እደመድማለሁ፡፡


1.የትጥቅ ትግል በአንድ ወገን ድል አድራጊነት የሚጠናቀቅ እንደመሆኑ አሸናፊውን ወገን ክብርና የበላይነትን ሲያጐናጽፍ ተሸናፊውን ወገን ደግሞ የውርደትና የበታችነት ስሜት ይፈጥርበታል፡፡ በዚሁ የተነሳ ተሸናፊው ወገን ቂም አርግዞ ጊዜውን ጠብቆ አድፍጦ የሚያደባበት ስለሆነ እውነተኛ ያልሆነ አሉታዊ ሠላም የሰፈነበት ነው፡ ፡ ፖለቲካውም የምሬት፣ የጥላቻ የበቀልና የጠላትነት ስለሚሆን እስራት፣ ስደት፣ ከሥራ መፈናቀልና ሌሎች ምስቅልቅሎችን ያስከትላል፡፡ ይህን የትግል ዘዴ በታሪካችን ደጋግመን ሞክረነዋል፡፡ መዘዙንም ቀምሰነዋል፤ ለኋላ ቀርነታችን አንደኛው ምክንያት ሆኗልና፡፡ በአንፃሩ ግን ሠላማዊ ትግል አሸናፊና ተሸናፊ ስለሌለው መቋጫው እርቅ ወንድማማችነትና ዘላቂ ሰላም ነው፡፡ አውንታዊ ሠላም ፖለቲካውም ልዩነትና ብዙሀንነት ስለሚያስተናግድ የሚማረር ወገን አይኖርም፡፡ ስለዚህ ተመራጭ ብቻ ሳይሆን ብቸኛ የትግል ዘዴ መሆን አለበት የሚል እምነት ስላለኝ ህጋዊ በሆነ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ የድርሻዬን በማበርከት ላይ እገኛለሁ፡፡


2.የትጥቅ ትግል አሸናፊው ቡድን የአልበገር ባይነት ስሜት እንዲሰማውና እብሪተኛና ጨካኝ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ድሉን ለማግኘት ለከፈለው መስዋዕትነት ካሳ ፈላጊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሥልጣንንና የሀብት ምንጮችን ጨምድዶ በመያዝ በትግሉ ያልተሳተፉትን በማግለል ፍትሀዊ ክፍፍልን አዛብቶ የዜጐችን የእኩልነት መብት ወደ መርገጥ ያመራል፡፡ ውሎ ሲያድርም ይህን ስህተቱን ማረም ስለሚሳነው የሃሳብ ልዩነትን የማይቀበል አምባገነን ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት መብታቸውን የሚጠይቁ ዜጐችን በጠላትነት ፈርጆ ሊያጠፋቸው ሕጋዊ የሚመስል ህገወጥ ድርጊቶችን በስውርና በግልጽ በመፈጸም ለሌላ ትጥቅ ትግል በር ይከፍታል፡፡ ይህን የትጥቅ ትግል ዑደት አንድ ቦታ ላይ ሰብሮ በማቆም አገሪቱን ከትርምስና የመገዳደል ባህል መታደግ የሚቻለው ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ሳይገድሉ እየሞቱ እየታሠሩና ከሥራ እየተፈናቀሉ በሠላማዊ መንገድ ብቻ በሚታገሉ ኃይሎች አማካኝነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መርጬ እየተጓዝኩበት ያለሁትም ይህን ነው፡፡


3.የትጥቅ ትግል ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብትን ከማውደሙም በላይ ጊዜያዊም ቢሆን ሥርዓተ አልበኝነትን ያስከትላል፡ ፡ በጣም ውስን በሆነች የሀገር ሀብት አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰ የሚሄድ ከሆነ መጨረሻችን የት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ የትጥቅ ትግል ለዜጎች ስንዴና ዘይት እንኳን ማቅረብ የማይቻል እንደኛ ያለ አገር ቀርቶ የሚዋጉበት በጦር መሳሪያ ለሚያመርቱ አገሮች እንኳን አዋጭ ስላልሆነ ዘለው አይገቡበትም፡፡ ብጥብጥና ሁከት በሚነሳባቸው አገሮች ዋነኞቹ ተጐጂዎች ተራ ዜጎች እንጂ እንደከሳሾቼ ያሉ ባለሥልጣናት ወይም የመንግሥት መሪዎች አይደሉም፡፡
በኛ አገርም ይህ ሁኔታ ቢከሰት ግንባር ቀደም ሰለባ መሆን ከሚችሉት ውስጥ እኔና ቤተሰቤ እንገኛለን፡፡ ምክንያቱም የምጓዘው በተራ ትራንስፖርት፤ የምኖረው በተራ መንደር በተራ ቤት፣ ልጆቼ የሚማሩት በተራ ትምህርት ቤት ሲሆን ከሳሾቼ ግን ይህ ሁሉ የማይመለከታቸውና የማያስጋቸው በመሆኑ ከነሱ የበለጠ ሠላም ለኔ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ስለዚህ ነው ምንም ዓይነት ዜግነት፣ ቀለም ወይም ዘር ይኑርው ስብአዊና ቁሳዊ ውድመትን የሚያስከትል ጦርነትም ሆነ ብጥብጥ ከሚራምድ አካል ጋር የማልተባበረው


4.በትጥቅ ትግል ወደ ሥልጣን የሚመጡ መንግስታት ከውይይትና ድርድር ይልቅ በኃይል መፍትሔ ስለሚያምኑ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ከማቀጨጭ አልፎ እስከነአካቴው ይፃረራሉ፡፡ ለይስሙላ በሚገኙባቸው የድርድር መድረኮችም ሌላም ወገን እንዲቀበል የሚፈልጉትን ለመንገር እንጂ ሰጥቶ ለመቀበል ስላልሆነ በድርድሩ ማግስት ወደ ቀድሞ የኃይል ተግባራቸው ይመለሳሉ፡፡ ህዝቡ የጦር ሜዳ ገድሎቻቸውን አይቶና ሰምቶ አይበገሬነታቸውን ተረድቶ በፍርሃት እንዲገዛላቸው ሚዲያውን በጦርነት ወሬ ያደምቃሉ፡፡


በሰላማዊ ትግል አግባብ ስልጣን የሚይዙት ግን የስልጣናቸው ምንጭ የሆነው ሕዝብ ጥቅሙና መብቱ ካልተጠበቀለት ነገ ደግሞ ለሌላ መስጠት እንደሚችል ስለሚገነዘቡ ዜጐቻቸውን ያከብራሉ፤ ከመፍራት ይልቅ መከበርን ይሻሉ ከመናገር ይልቅ ማዳመጥን ያስቀድማሉ፡ ፡ እውነተኛ ዴሞክራሲን በማስፈን ሕዝባቸውን ወደ ዘላቂ ሰላምና እድገት ይመራሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰላማዊ ትግል ነው እንዲካሂድ የምሻውና ዋጋ እየከፈልኩበት ያለው፡፡


5.በእምነት ዝንባሌዬ ነፍስ የፈጣሪዋ ብቻ ስለሆነች የሰውን ልጅ ነፍስ ማጥፋት ከወንጀል አልፎ ኃጢአት መሆኑንና ይህን ክቡር ነገር በኃይል ከሰው የሚነጥቁ ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ እንደሚነጠቁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ሠይፍ የሚመዙ በሠይፍ ይጠፋሉ” የሚለውን መለኮታዊ ቃል አምናለሁ፡፡ ስለዚህ የኃይል ተግባርን እንደአማራጭ ወስጄ አላውቅም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፈጣሪ እውነት ነው፤ በፈጣሪ የሚያምን ሁሉ እውነትን ያመነ ማለት ይገባዋል፡፡ “እውነትን ሲሻና ለፍትህ ሲከራከር በፍቅር ብቻ ማድረግ አለበት” የሚለውን የጋንዲ “ሳትያግራሀ” ፍልስፍና እቀበላለሁ፡፡ “ሳትያግራሀ” “የእውነት ኃይል፤ የፍቅር ኃይል” ማለት ሲሆን ጥቃት ለሚሰነዘር ሰው አፀፋ ሳይመልሱ በፍቅር ቀርቦ በውስጥ ያለውን መልካም ነገር በማንቀሳቀስ በህሊና ወቀስ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ማድረግ ይቻላል፡ ፡ የሚል ፍልስፍና ነው፡፡ ይህ የሰላማዊ ትግል የመጨረሻ ተሞክሮ በሰላማዊ ታጋዩ ወይም ሳትያግራሂው ላይ ከፍ ያለ ሥቃይን የማያስከትል እንደመሆነ በአስተሳሰቦች በሞራላዊነታቸውና በትዕግሥታቸው የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች ብቻ የሚተገብሩት ነው፡፡ ከሳትያግራሀ የሰላማዊ ትግል ስልቶች አንዱና ዋነኛው ከክፉ ሥራ ጋር ያለመተባበር ነው፡፡ እኔም አንድን ዓላማ ለማሳካት ኃይልን ከመጠቀም የበለጠ ክፉ ነገር አለ ብዬ ስለማሰብ ከእንዲህ አይነት ተግባር ጋር ተባብሬ አላውቅም፡፡ እንግዲህ ትጥቅ ትግል ውስጥ ያልተሳተፍኩት እላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች እንጂ በማንምና በምንም ፍራቻ አሊያም አጋጣሚ አጥቼ አልነበረም፡፡ ከሳሾቼ እንደሚሉት ልጆች ሳላፈራና በትምህርት ሳልገፋ በአፍላ የወጣትነት ጊዜዬ ያላሰብኩትን ድንገት በሃምሳኛ ዓመት እድሜዬ ላይ በተራ የኦ.ነ.ግ ተዋጊነትና ካድሬነት ለመሠልጠን ኬንያና ሰሎሎ አልሄድኩም፡፡


ነፍስ ካወቅሁ ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጆች መብት እንዲከበር ጽኑ ፍላጎና አቋም የነበረኝ ቢሆንም ሁሉም ሰው ፓለቲከኛ መሆን አለበት የሚል እምነት ስላለነበረኝ እስከ 2002 ዓ/ም ድረስ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኜ አላውቅም፡፡ ተሰጥኦውና ዝናባሌው ያላቸው ጥቂቶች የፖለቲካ ማህበር መስርተው ለስልጣን ተወዳድረው ህዝባቸው በፍትሀዊነት ማስተዳደር ከቻሉ ሌሎች ዜጐች በተለያየ ሙያ ተሰማርተው አገራቸውን ማገልገል አለባቸው ብዬ ስለማምን እኔም በመምህርነት ሙያ ብቻ ተሰማርቼ ተግባሬን በትክክል ስወጣ ኖሬያለሁ፡፡


ይሁን እንጂ የፖለቲካ ድርጅቶች የሰዎች ስብሰብ እንደመሆናቸው መጠን ሁሉን ነገር ያለእንከን ይፈጽማሉ ብሎ ማመን ስለማይቻል ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በመረዳት ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ፓርቲ የሚሰብከውን መተግበር እየተሳነው ሲሄድ ወይም በተፃራሪው ሲተገብር ሆን ብሎ አለመሆኑን ለራሴ ለማሳመን ሃያ አመታት ያህል ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ በመጨረሻም በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በተለይ ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል ዝም ብሎ መመልከትን ህሊናዬ አልቀበል አለኝ፡፡


– ሦስት መቶ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጥያቄ እንኳን ሳይቀርብላቸው በአንድ ቀን ሲባረሩ
– በየዩኒቨርስቲው ያሉ ሌሎች ደግሞ በየዓመቱ ሲደበደቡና ሲንገላቱ
– የፋብሪካ ዝቃጭ አተላዎች በማንአለብኝነት ህዝብ ወደሚጠጣቸው ወንዞች ሲለቀቁና አደጋ ሲያስከትሉ
– ለፌዴራሉ መንግስት ከፍተኛውን ገቢ የሚያስገባ ህዝብ በአንፃሩ ግን በነፍስ ወከፍ እጅግ ዝቅተኛው የፌዴራል በጀት ድጐማ ሲመደብለት
– መሬቱ በስበብ አስባቡ በግፍ እየተወሰደ ተቸብችቦ ሌሎችን ባለፀጋ ሲያደርግ፤ የሱ ቤተሰቦች ግን የትም ሲበተኑ
– ቋንቋው ቀድሞ ሲነገር ከነበረበት ቦታ እየጠፋ ሲሄድ
– ከኤኮኖሚው ዘርፍ ወጥቶ የበይ ተመልካች ሲሆን
– የዛሬ 120 ዓመት የኦሮሞ መንደር በነበረቸው ፊንፊኔ በቋንቋው የሚማርበት አንድ ት/ቤት ወይም አንድ የእምነት ሥፍራ እንኳ ሲነፈገው
– የፌዴራል ሠራተኞች ቅጥርና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራር ብሔራዊ ተዋጽኦ አግባብ ባልሆነ መልኩ ሲከናወን
– ከሁሉም በላይ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ሥልጣን ሲይዝ በእስር ቤት ከነበሩ ኦሮሞ፣ ዛሬ በብዙ እጥፍ የሚሆኑት በፌዴራል ወህኒ ቤቶች ሲማቅቁና ቤተሰቦቻቸው በረሃብ አለንጋ ሲገረፉ እያየሁ ዝም ማለት እንዴት ይቻለኛል?
እነዚህ ነገሮች እንዲሰተካከሉ ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት በሠላማዊ መንገድ አስተዋፅኦ ለማድረግ የአንድ ፓርቲ አባል መሆንን ሳውጠነጥን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኦ.ፌ.ዴ.ን/ ጥሪ አድርጐልኝ በ2002 ዓ/ም ለመጀመሪ ጊዜ አባል ሆንኩ፡፡ ከዚያም የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆንኩ፡፡ በ2002 ዓ/ም ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ሆኜ መላው ሕዝባችን በሚያውቀው ሁኔታ ተሸነፍኩ፡፡ በምርጫ ዘመቻ ወቅትም በግልና በቡድን የተካሄዱብኝን ትንኮሳዎች ተቋቁሜ መንግሥት ባሰማራቸው ሁከት ፈጣሪዎች መካከል ቆሜ ለሠላማዊ ትግልና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ያለኝን ቁርጠኝነት አስመስክሬያለሁ፡፡ ምርጫውን እንደማላሸንፍና መጨረሻዬም አሁን ያለሁበት እስር ቤት እንደሆነ እየተነገረኝ አንድ ሰላማዊ ታጋይ ማድረግ ያለበትን አድርጊያለሁ፡፡


በፖርቲዬ ውስጥ በተሰጠኝ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ድርሻ ምክንያት በእስር ላይ ስላሉ ኦሮሞዎች ሁለት ጊዜ ያህል ለውጪ ሚዲያዎች ቃለ መጠይቅ በመሰብሰብ ከሳሾቼን እንዳላስደስታቸው ከራሳቸው ተነግሮኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰጠሁት መረጃ ሀሰትም፣ ምሥጢርም እንዳልሆነ ነግሬያቸው በተያየን በሃያ ቀናት ከቢሮዬ ተጠርቼ ታሰርኩ፡ ፡ ከመታሰሬ ጥቂት ቀናት በፊት ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመጡ ሰዎች አነጋግረውኝ ነበር፡፡ የእነዚህ ነገሮች ድምር ነው “የአገርና የሕዝብን አንድነት በማፍረስ” ወንጀል አስከስሶ ለእስራት የዳረገኝ፡፡


በሕዝቦች መካከል ግልጽ ልዩነት እየፈጠረ አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠር ኅብረቱ እንዲላላና አንድነቱ እንዲፈርስ እያደረገ ያለ ሥርዓቱ ነው ወይስ ይህ ሁኔታ እንዲሰተካከል በሰላማዊ መንገድ እያሳሰበ በመታገል ላይ ያለ ሰው ነው የአገሪቱን የግዛትና የፖለቲካ አንድነት በማፍረስ ወንጀል የሚጠረጠረው? ህገ መንግሥቱን በተግባር እየጣሰ ያለውስ መብቴ ይከበር የሚለው ነው ወይንስ መብቱን የገፈፈው ነው?
ድርጅታችን በኢ.ፌ.ዴ.ን ህዝቦች መብታቸው እስከተከበረላቸው ድረስ የመገንጠል ጥያቄ አያነሱም መለየትንም አይፈልጉም የሚል እምነት ስላለውና የአገር አንድና ቁልፍ እውነተኛ እኩልነት የሰፈነበት ሥርዓት ማስፈን መሆኑን ያምናል፡፡


ስለዚህ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ያለው እስከመገንጠል የሚለው ሀረግ ጠቃሚ አይደለም በሚል እምነት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክረሲያዊ አንድነት መድረክ መለስተኛ የፖለቲካ ፕሮራም ውስጥ እንዲካተት ከፈረሙት አባል ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እኔም የድርጅቱ አባልና አመራር ይህን ለማሳመን ጉንበስ ቀና በምልበት ሰዓት የአገር አንድነትን ለማፍረስ በመሞከር እንዴት ልከሰስ እችላለሁ?
ማንኛውም ኦሮሞ መብቱን የመጠየቅ አዝማሚያ ወይም ከሥርዓቱ ጋር ያለመተባበር ዝናበሌ ያሳየ እንደሆነ በኦነግነት ፈረጆ ማናቸውንም የግፍ ተግባር መፈፀም ከተጀመረ ሃያ አመታት ተቆጠሩ፡፡ ይህ አድራጎት በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ሲታይ ወደር የለሽ ነው፡፡ ናይጄሪያ በየጊዜው ፍንዳታ እያደረሰ ኃላፊነት በሚወስደው የቦኮሃራሞ ድርጅት አግባብ ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩና ተመሳሳይ እምነት የሚከተሉ ዜጐቿን ቁም ስቅል አላሳየችም፡፡ የወደቀው የግብጽ መንግስት እንኳን ህገወጥ ነው ብሎ በፈረጀው የሙስሊም ወንድማማቼች ፓርቲ አመካኝቶ ተቀናቃኞችን ለማጥፋት ዘመቻ አልከፈተም፡ ፡ ከአንድ የዘር የተገኘ ሁሉ አንድ አይነት የፖለቲካ አመለካከት አለው ብሎ የሚገምት ቢኖር በሥልጣን ላይ

ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ይመስለኛል፡፡ አገር የሚያፈርሰው እንዲህ አይነት አመለካከት ነው፡፡ እኔ ግን ይህን በመርህም ተቀብዬ በተግባርም ሞክሬ አላውቅም፡፡
ነገር ግን ለሥርዓቱ ካለመመቸት ውጪ በሀገሬና በሕዝቤ ላይ አንዳች ጥፋት እንዳልፈፀምኩ ጠንቅቀው የሚያውቁት ከሳሾቼ በወህኒ ቤቶች አካባቢ “አዳፍኔ” በመባል የሚታወቁ የሀሰት ምስክሮችን አቅርበው አስመስክረውብኛል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ 1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 21 ላይ አጽመርስቴን አልለቅም ስላለ “ንጉሡንና እግዚአብሔርን ሰድቧል” ብለው የሀሰት ምስክሮችን አስመስክረው ናቡቴን በድንጋይ አስወግረው እንዳስገደሉት የአክአብ ባለሥልጣኖች የሰው ልጆች መብት ይከበር ባልኩ ኢትዮጵያዊው ናቡቴ ሆኜ ቀርቤያለሁ፡፡ ይህ ድርጊት ከዚህ መዘምር ከሳሾች እራሳቸው ሲኒማ ቤት ውስጥ የእጅ ቦምብ ወርውረው ብዙ ሰዎችን ካቆሰሉ በኋላ ይህን ያደረገው ማሞ ነው በማለት በሀሰት አስመስክረው ሞት ተፈርዶበት አለም በቃኝ እስር ቤት ውስጥ በስቃላት ተቀጥቷል፡፡
በኔ ላይ የቀረቡት የአቃቤ ህግ ምስክሮች በቁጥር አራት ሲሆኑ ሁለቱ ቤቴ ሲፈተሸ ታዛቢ የነበሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም ያዩትን በመመስክራቸው በምስክርነት ቃላቸው ውስጥ ወንጀለኛ የሚያሰኘኝ ነገር ባለመኖሩ ሌሎች ሁለት ምስክሮች በሰጡት የሀሰት ምስክርነት ቃል ላይ አተኩራለሁ፡፡ የአቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ የቀረበብኝ አንደኛው ሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዬ ሆኖ የተመደበ የክረምት ተማሪ ኢዮስያስ አበራ ማሞ ከሌሎች ተማሪዎች ተነጥሎ ቢሮዬ መጥቶ የገዥው ፓርቲ አባል እንደሆነ ይህን ያደረገውም የደህንነት አባል የሆነውን አባቱን በመፍራት እንደሆነ አሁን ግን በፓርቲው ውስጥ የሰፈነውን ኢፍትሐዊነት በመፀየፍ የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን እንደሚፈልግ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክን እንደሚያደንቅ ነግሮኝ እንድመለምለው ጠይቆኝ ነበረ፡፡ እኔም እኔ ያለሁበት ፓርቲ የኦሮሞ ድርጅት እንደሆነና የመድረክ አባላት ከሆኑ ህብረብሔር ፓርቲዎች ውስጥ ወስኖ አንዱን መጠየቅ እንዲሚችል ነግሬው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር አባል የሆነውን የአቶ አንዱአለም አራጌን ስልክ ቁጥር ሰጠሁት፡፡


ግለሰቡ ክቡር ፍ/ቤቱ ፊት ቀርቦ ቃሉን ሲሰጥ ተማሪዬ እንደሆነ ኮርስ ሰጥቼው እንደማላውቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው ሐምሌ ወር 2003 ዓ/ም የመመረቂያ ጽሁፉን ሊያስረክብ ቢሮዬ በተገኘበት ዕለት መሆኑን በዚሁ የመጀመሪያ ግኑኝነታችን “መንግሥት የኦሮሞንና የደቡብን ህዝብ ስለሚጠላ ይጨቁናቸዋል፣ ስለዚህ ተነሳስተን በአመጽ እናስወግደው” እንዳልኩት ተናግሯል፡፡ ሌሎችንም ተማሪዎች ጨምሮ እንደተወያየን አስመስሎ መስክሯል፡፡


ይህ ግን ፈጽሞ ሀሰት ነው፡ ፡ ግለሰቡ አግኝቶኝ የማያውቅ ከሆነ በሐምሌ 2003 ዓ/ም ሊያስረክበኝ የመጣው የመመረቂያ ጽሁፍ ማን ያማከረውን ነበር? ከአማካሪው ጋር አንዳች ግንኙነት ሳያደረግ ምንነቱ ያልታወቀ የመመረቂያ ጽሁፉን ይዞ ከመጣ ተማሪ ጋር ያውም በመጀመሪያው ግንኙነት ከአካዳሚ ነክ ጉዳዮች ወጥቶ ስለ መንግስት ግልበጣ ማውራት ይታሰባል ወይ? ለአንድ የዩኒቨርስቲ መምህር ተመካሪ ተማሪዎች የሚመደቡት በሚመለከተው ትምህርት ክፍል እንደመሆኑ የተለያየ ፖለቲካ ዝናባሌ እንዳላቸው እየታወቀ አንድን ወገን ብቻ በሚመለከት ፖለቲካ ውይይት መክፈት እንዴት ይታሰባል? የተከሰሰኩት በአሽባሪነት ከተፈረጀ የኦሮሞ ድርጅት ሆኖ ሳለ ግለሰቡ ደግሞ የዚህ ማህበረሰብ አባል አለመሆኑን በግልጽ እየተናገረ፤ ኦሮሞዎች ተበድለዋልና በመንግስት ግልበጣ ተባብረን ልል እንዴ እችላለሁ? ይህ ሰው ኦሮሞዎችን ከጭቆና ለመታደግ ከሰማየ ሰማያት የተላከ አዳኝ ነው ብዬ ልገምት አልችልም፡፡ ይልቅ እሱስ ፍትህን ሲገድል የተመደበ የአክአብ ምስክር ኖሯል፡፡
ሌላኛው ስሜን እንኳን በትክክል ያላስጠኑት የአቃቤ ሕግ ምስክር አመና አርኮ በክቡር ፍ/ቤቱ ፊት ቀርቦ ቃሉን ሲሰጥ “በጥር ወር 2002 ዓ/ም አቶ ጉቱ ሙሲሳ ቤት ተገናኝተን ለአመጽ አነሳስቶኛል” ሲል ተናግሯል፡፡


እኔ ይህን ግለሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ከዚሁ ፍ/ቤት ውስጥ ነው፡፡ ነገሩ የማይታመንና ዱብዕዳ ስለነበረ በዕለቱ ጥያቄም አላቀረብኩለትም፤ ስለማንነቱ ለማወቅ ባደረግሁት ጥረት በቂና ተጨባጭ መረጃዎችን ለማግኘት ችያለሁ፡፡ ግለሰቡ እውነተኛ ማንነቱ ኢመና ኢርኮ ሳይሆን ሺፈራው ኤቢዳ ሲሆን የትውልድ ሥፍራው በምዕራብ ሸዋ ዞን ሸነን ወረዳ ሆኖ አድራሻዬና የሥራ ቦታዬ ነው ያለውን ነቀምቴ ከተማ 01 ቀበሌን ረግጦ እንኳን አያውቅም፡፡


ይህ ግለሰብ የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ /ኦ.ህ.ኮ /አባል የነበረ ሲሆን በ1997 ዓ/ም የምርጫ ታዛቢ ስነበር በ1998 ዓ.ም ታስሮ የተሠቃየ በ1999 ዓ.ም አጣሪ ኮሚሽን ፊት ቀርቦ ቃሉን የሠጠ በ2000 ዓ/ም ኦህኮን ወክሎ ለወረዳና ለቀበሌ ምርጫ የተወዳደረ፡ ፡ በ2003 ዓ/ም እንደገና ታስሮ የነበረ ሲሆን ይህን ሁሉ ያደረገው በእውነተኛ ስሙ ነበር፡ ፡ በመጨረሻም ከደረሰበት ስቃይ የተነሳ እንዲሁም የሚሉትን እሺ ካላለ መኖር እንደማይችል ስለተገለጸለት ያሉትን ሁሉ ለማድረግ ቃል ግብቶ በመፈታት በኔ ላይ በምስክርነት የቀረበ ነው፡፡ ይህንን የመከላከያ ምስክሮች ያስረዱልኛል፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት ከግለሰቡ ጋር በአካልም ሆነ በማንኛውም የመገናኛ ዘዴ ተገናኝተን የማናውቅ ከመሆን አልፎ ቤቱ ተገናኘን ያለውን አቶ ጉታ ሙሊሳን እንኳን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ማረሚያ ቤት ሁለታችንም እስረኞች ሆነን ነው፡፡ ይህንንም ምስክሮቼ ያረጋገጡልኛል ለመሆኑ በ2002 ዓ.ም ህገ መንግሥቱን አምኜና አክብሬ በምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት ላይ የነበርኩ ሰው እንዴት ሆኖ ለአመጽ ቅስቀሳ ማካሄድ የምችለው?

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ግለሰቡ በኔ ላይ ስለመሰከረው ነገር ብቻ ሳይሆን ማንነቱንና አድራሻውን ጭምር እንዲዋሽ የተገደደ እንደመሆኑ መጠን ክቡር ፍ/ቤቱ ይህን ተመልክቶ የሰጠውን የምስክርነት ቃል ውድቅ እንዲያደርገልኝ እጠይቃለሁ፡፡
አቃቤ ህግ ወንጀለኛ ለመሆኔ እንደአስረጂነት ያቀረበው ሌላው የሠነድ ማስረጃ በ1989 ዓ/ም መጀመሪያ ላይ የተነሳሁት የኦነግ አርማ ተሰቅሎ የሚታይበት ፎቶ ግራፍ ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም መጨረሻ ደረግ እሠራበት የነበረችውን ዓለም ተፈሪ ከተማ ለቆ ሲሄድ ብዙ ሰዎች አካባቢውን ለቀው ሲሰደዱ ሠላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የተቋቋመውን ኮሚቴ እንድመራ በህዝብ ተመርጬ እስከ 1984 ዓ/ም መጨረሻ ድረስ ሰርቻለሁ፡፡ በዚህ ወቅት በከተማው ፍ/ቤት ከፍተው በይፋ ይንቀሳቀሱ ለነበሩ ሁለት የኦሮሞ ድርጅቶች ኦህዴድና ኦነግ ስብሰባዎችን እየጠራሁና እየመራሁ በገለልተኝነት ሥሰራ ቆይቻለሁ፡ ፡ በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ለኦህዴድ በርካታ ስብሰባዎችን ለኦነግም ጥቂት ሰብሰባዎችን ከተማው መሃል በሚገኝ የወረዳው አስተዳደር ግቢ ሜዳ ላይ መጥራቴን አስታውሳለሁ፡ ፡ ከነዚህ ስብሰባዎች በአንዱ የተወሰደ ነው የተጠቀሰው ፎትግራፍ ያ ወቅት ሁለት ድርጅቶች እንኳን በመሰብሰቢያ ቦታዎች ቀርቶ በየምሶሶዎቹና ዛፎቹ አርማቻቸውን ይሰቅሉ የነበረ የትኩሳት ጊዜ ነበር፡፡
ኢፍትሐዊነትንና አድሎን …
ከ ገፅ 15 የዞረ….
በፎቶግራፍ ላይ እንደሚታየው ቁጥሩ ብዙ የሆነ ህዝብ ሜዳ ላይ ተሰብስቦ ይታያል፡፡ እንደሚታወቀው ኦነግ በ1984 ዓ/ም በመጨረሻ ሽግግር መንግሥቱን ለቆ ከወጣ በኋላ እንዲህ ዓይነት ስብሰባ በመሀል ከተማ አደባባይ ሊደረግ ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በፎቶ ግራፉ ላይ የሚታዩ ሰዎች ብዙዎች በህይወት የሉም፡፡ በፎቶግራፉ ላይ የሚታየው የራሴ ገጽታም ከዛሬ ጋር ሲስተያይ የፎቶውን ዕድሜ ይናገራል፡፡ በፎቶግራፉ ላይ የሚታየው ቦታም ዓለምተፈሪ መሆኑ ተለይቶ ይታወቃል፡፡ እኔ ደግሞ በ1985 ዓ/ም ከዚያ ተዛውሬ ስለሄድኩ እና ወደዚያ ለመመለስ እድሉ ስላልነበረኝ፣ ቢኖረኝ ኖሮም ያንን ሰብሰባ ማካሄድ እንደማልችል ይታወቃል፡፡
በአጠቃላይ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት በወቅቱ ህጋዊ የነበረና በሚኒስትሮች ም/ቤት አራት የካቢኔ ሚኒስተሮች የነበሩትና መዲናዋን (አዲስ አበባን) ጭምሮ በአርማዎቹ አጥለቅልቆት በነበረ ድርጅት አርማ ጋር የተነሳኸው ፎቶ ግራፍ የአገር ግዛትና ፖለቲካዊ አንድነት ለመንካትህ ማስረጃ ነው ተብሎ ሊቀርብብኝ ስለማይገባ ክቡር ፍ/ቤቱ ውድቅ እንዲደረግልኝ እጠይቃለሁ፡፡
ማጠቃለያ
ያለመተደል ሆኖ በአገራችን መልካም አስተዳደር አፈአዊ እንጂ ተግባራዊ ሆኖ ስለማያወቅ አንዱ የሠራውን ሌላው እያፈረሰ በዓለም ፊት በኩራት አንገታችንን ቀና የምናደርግበት ሳይሆን በሀፍረት የምንሸማቀቅበት፤ ለልጆቻችንም ተስፋን ሳሆን የስጋት ቅርስ እየተውንላቸው አበሳን እንደ ዱላ እየተቀባበልን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ እንዳይቀጥል የሳተው በጊዜ እንዲመለስ የተጣመመው እንዲቃና የተበላሸው እንዲስተካከል ጎረቤት ሳይሰማ፣ ፈረንጅ ገመናችንን ሳያውቀው አድብተን ሰንጠፋፋ ችግራችን ገለጥለጥ አድርገን ተወያይተን ተከራክረን ተወቃቅሰን መፍትሔ እናበጅለት፡፡ ይህንንም አንዱ ባንዱ ላይ ዱላ ሳይሰነዝር ቃታ ሳይስብ፣ ወደ እስር ቤት ሳይጎትተው በሠላማዊ መንገድና በፍቅር እናድርገው የሚል ጽኑ አቋም ነው፡፡ እኔና ድርጅቴ የምናራምደው፤ ይህ በኛ በጎ ጥረትና ፍላጎት ብቻ የሚሳካ ባይሆንም እኛ ግን በዚሁ መንገድ እንጓዛለን፤ ኢፍትሃዊነትንና አድልኦን አሜን ብሎ ውርደት ከመቀበል መከራና ስቃይን በክብር ማስተናገዳችንን እንቀጥላለን፡፡ በመጨረሻም ፍትህ ከጎናችን
ትቆማለች፡፡

ource-  Millions of voices for freedom – UDJ

የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ከአውሮፓ ህብረት ልዑካን ጋር ተወያዩ

0
0

የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ትላንት ህዳር 16 ቀን ከአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ኃላፊ ሻንታል ሄበርረሼት እና ከልዑኩ ተቀዳሚ ቆንስል እንዲሁም የፖለቲካ፣ የፕሬስና የኢንፎረሜሽን ኃላፊ ከሆኑት ሳነዲ ዋዴ ኦቤ ጋር በ2007 ምርጫ ዙሪያ መወያየታቸውን ከፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ለፍኖተ ነፃነት የደረሰው መረጃ አመላከተ፡፡
ህብረቱ ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት ውይይቱን ያደረጉት የአንድነት አመራሮች “እኛ በሀገራችን ለውጥ ለማምጣት የምንታገለው ሙሉ ለሙሉ ዕምነታችንን የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጥለን ነው፡፡” ካሉ በኋላ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳይ አሳስቦት ያቀረበውን ጥሪ አክብረው መምጣታቸውን ለህብረቱ ልዑካን አስረድተዋል፡፡ ምርጫ 2007ን በሚመለከት “አንድነት በምርጫ ለመሳተፍ ወስኗል፤ የምርጫውም ነፃ፣ ፍትሀዊና ተአማኒ እንዲሆን ይታገላል፡፡” በማለት የአንድነትን አቋም አስረድተዋል፡፡ አክለውም “ከምርጫ መውጣት ቀዳሚ ምርጫችን ባይሆንም፤ ምርጫው ለውጥ የማያመጣ ሆኖ በተገኘበት በየትኛውም ጊዜ ከምርጫው እንወጣለን” በማለት ተናግረዋል፡፡
አመራሮቹ አበክረው ለልዑካኑ ያስረዱት በየትኛውም ሁኔታ ኢህአዴግ አይን ያወጣ የምርጫ ዝርፊያ ቢያደርግ አንድነት በዝምታ እንደማይመለከት ማስረዳታቸውን የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ለፍኖተ ነፃነት አስታውቋል፡፡

Millions of voices for freedom – UDJ

UDJ

የግሪክን ብሔራዊ ህልውና የተፈታተነ ”ሶቨሪን ቦንድ” ለኢትዮጵያ እንዴት ይሰራል?

0
0

ministry of financeኢትዮጵያ ከእዚህ በፊት ከመንግሥታት፣አህጉራዊ ወይም ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር ወስዳለች።አሁን ያለባት የብድር መጠን ከ20 ቢልዮን ዶላር ወይንም ከ400 ቢልዮን ብር በላይ መሆኑ ይታወቃል።ወደ ”ሶቨሪን ቦንድ” እንድትገባ በዝግ ምክርቤት ወሰነ የተባለው የብድር አይነት ግን ኢትዮጵያ ከግል አበዳሪዎች ሁሉ በደላሎች ብድር እየፈለገች እንድትበደር የሚያደርግ፣በሙስና ለተሰነገ ሀገር ፈፅሞ የማይመከር ነው።ለመሆኑ የሶቨርን ቦንድ ምን ማለት ነው? ”ኢንቨስቶፕድያ እንዲህ ይገልፀዋል።

”ሶቨሪን ቦንድ” ማለት በመንግሥታት በውጭ ምንዛሪ የሚቀርብ የብድር ዋስትና ሲሆን የውጭ ምንዛሪው በጠንካራ አለም አቀፍ ገንዘብ (ሃርድ ከረንሲ) የተደገፈ ነገር ግን ለቦንድ ያዥው የበለጠ አደጋ ያለው ” ይላል

”DEFINITION OF ‘SOVEREIGN BOND’
A debt security issued by a national government within a given country and denominated in a foreign currency. The foreign currency used will most likely be a hard currency, and may represent significantly more risk to the bondholder.” www.Investopedia.com

ምዕራባውያን እና ሶቨርን ቦንድ

ብድሩን የምዕራብ ሃገራት ፍላጎት የታዳጊ ሀገሮች ወደገበያው መግባት ነው። ምክንያቱም አበዳሪ ሁል ጊዜ ተበዳሪ ማግኘት ስራው ነው።ይህ ማለት ተበዳሪ በአዋጭም ይሁን በማያዋጣ መንገድ ላይ ቢሆን ለአበዳሪ ጉዳዩ አይደለም። አበዳሪ ገንዘቤ ባይመለስ በምን ሌላ አስገዳጅ ነገር ውስጥ አስገብቼ ያልታሰበ ሲሳይ ይገኛል? ነው ጥያቄው።ለእዚህ ነው የ”ፋይናንሻል ታይምስ” ጨምሮ የኢትዮጵያን ወደ እዚህ ብድር መምጣት አሰማምሮ የፃፈው።ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ተጠጋች የሚለውን ስጋት ለማራቅ ”በሶቨሪን ቦንድ” መያዙ ለወደፊት ‘ስልታዊ ጥቅም’ አለውና።በሌላ በኩል ይህ ብድር የሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ማስፈፀምያ አንዱ ስልት ነው።

ግሪክን ያየህ ተቀጣ

ግሪክ ባለፉት ሁለት ዓመታት የምጣኔ ሃብቷ ያን ያህል ያሽቆለቆለው ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ሃገራት ስር በተለይ ጀርመን ስር እንድትንበረከክ የተደረገው በእዚሁ ”ሶቨርን ቦንድ” አማካይነት ነው።የሀገሪቱ ህዝብም አደባባይ ወጥቶ የገዛ መንግስቱን የተቃወመው በእናንተ ሙስና ምክንያት ሀገሪቱ ከማትችለው ብድር ውስጥ አስገባችሁ በሚል ነበር።ይህንን ለመረዳት ”የሶቨሪን ብድር ቀውስ የዘመናዊዋ ግሪክ አሳዛኝ ሁኔታ” ”The Sovereign Debt Crisis: A Modern Greek Tragedy”በሚል ርዕስ የወጣውን ”የሴንት ሉዊስ ባንክ” ፅሁፍ ያንብቡት።

ሉዓላዊነታችን አደጋ ላይ የመውደቅ እድል አለው

በኢትዮጵያ ላይ የረጅም ጊዜ ስልታዊ ፍላጎት ያላቸው ሀገሮች በግለሰብ ወይንም በኩባንያ ስም ከአውሮፓ ወይንም ከአሜሪካ ብቅ ቢሉስ? ለምሣሌ የገንዘብ ችግር የሌለባቸው እንደ ሳውዲ አረብያ ያሉ ሀገሮች ገንዘባቸውን በባንክ ከማስቀመጥ በእደዚህ አይነት ብድር ለድሃ ሃገራት ቢሰጡ ያተርፋሉ።ኢትዮጵያ ላይ በብዛት ብድር ሰጥተው መልሰው የነገር መቆስቆሻ ሊያደርጉት እና እስከ ጦርነት የሚያደርስ ብሎም በሉዓላዊነታችን ላይ የሚጋረጥ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል።በእንደዚህ አይነት መንገድ የሚነሱ ግጭቶች ደግሞ ወደ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲደርስ ምንም አይነት የዲፕሎማሲ ድጋፍ የማያስገኝ ስለሆነ አበዳሪዎች በዓለም መድረክ የመሰማት እድላቸው ከፍተኛ ነው። ለእዚሁም ምክንያቱ ኩባንያዎቹ በተለያየ ጥቅም ከብዙ ሃገራት ጋር የጀርባ ንግግር ስላላቸው እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ብድሩን መክፈል አለባት የሚሉ ቃላትን እንጂ ሌሎች ሁኔታዎችን የምያገናዝብበት ዕድል ፈፅሞ አይፈጥርለትም።በመሆኑም ሕጋዊ በሚመስል መንገድ ሀገር ለአደጋ ያጋልጣል ማለት ነው።

ባጭሩ የሶቨሪን ብድር በአለማችን የገንዘብ ስርዓት ውስጥ ያለ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት ግን የሚገቡበት አግባብ የራሱ የተገደበ መስመር መያዝ ይገባው ነበር። ይህ የተገደበ መስመር ማለት-

1/ ስለ ብድሩ ምንነት፣አስፈላጊነት እና የመክፈል አቅም በዝርዝር በስሙ ለሚበደሩት የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልፅ መነገር ነበረበት፣
2/ ህዝቡ በጉዳዩ ላይ መወያየት ነበረበት፣
3/ ሙስናው ቅጥ ባጣበት ሀገር እዴት ሊሰራ እንደሚችል መጤን ነበረበት፣
4/ብድሩ ለየትኛው ፕሮጀክት እና ምን ያህል እንደሚወሰድ ለሕዝብ መታወቅ ነበረበት፣
5/ መንግስት የሚበደረውን የገንዘብ መጠን በሕግ ገድቦ ማስቀመጥ ነበረበት። ለምሳሌ ገንዘብ ባነሰው ቁጥር በደላላ አበዳሪ እየፈለገ የሚበደር ከሆነ መጨረሻው የት ሊሆን ነው?
6/ ኢትዮጵያ ብድሩን ተበድራ ለመክፈል የምታስበው ከየት እና ምንን ታሳቢ አድርጎ ነው? የሚለው በግልፅ ለሕዝቡ መቅረብ ነበረበት።

እነኝህ ሁሉ ባልተደረጉበት ሁኔታ ኢትዮጵያን አፏን ለጉመው፣የመገናኛ ብዙሃንን ዘግተው፣የግል ጋዜጦችን አሽገው፣ፓርላማውን በዝግ ስብሰባ አስፈራርተው በእኛ እና በልጆቻችን ስም የመበደር መብት እንዴት ያለ ሕዝብን የመናቅ ደረጃ ነው? በትክክል ከላይ ከተባለው አንፃር ስንመለክተው አደጋ ላይ ነን።ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በተድበሰበሰ መንገድ የሚሰራው ሥራ ”ምን ያህል ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ የያዙ ሰዎች አመራር ላይ አሉ?” ብሎ የመጠየቂያው ጊዜ ነው።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከእራሷ ሀብት አፍርታ፣ወደውጭ የሚላክ ምርት ጨምራ የውጭ ምንዛሪ አግኝታ የመኖር አቅሟን ላለፉት 23 ዓመታትም መፍጠር አለመቻሏ አመላካች አንዱ መንገድ ይህ አሁን በቅርብ ቀናት ውስጥ አውሮፓ ላይ ”ልንበደር ነው አድገናል” የሚለው መግለጫ በኢህአዲግ/ወያኔ ባለስልጣናት ሊሰጥ መሆኑ ነው።የእድገታችን መገለጫ መበደር እንዴት ሊሆን ይችላል? ፖለቲካዊ ዝናን ለማግኘት የተገቡባቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ወሳኝ ግን ጠቃሚ የነበሩትን እንደ በምግብ እራስን መቻል፣ወዘተ ፕሮጀክቶች ችላ እንዲባሉ አላደረገም ወይ? ይህ የተሳሳተ የፖሊሲ ውሳኔ ዛሬ ዋጋ እያስከፈለን አይደለም ወይ? ነገሩን በአንክሮ ለተከታተለው ሰው አሳዛኝ ነው።ጥያቄው ግን አይቆምም የግሪክን ብሔራዊ ህልውና የተፈታተነ ”ሶቨሪን ቦንድ” ለኢትዮጵያ እንዴት ይሰራል?

ጉዳያችን
ህዳር 18/2007 ዓም (ኖቬምበር 27/2014)

Source:: gudayachn

የስደተኞትና የስደት ተመላሾች እጣ

0
0

8EF5BDEB-55F0-43A5-9205-44A05F770A20_w268_r1የምሥራቅ አፍሪቃ አገሮች በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ላይ የጋራ ራእይና እቅድ እንዲኖራቸው ለማስቻል የታለመ የሁለት ቀናት ውይይት አዲስ አበባ ላይ ተጀምሯል።

የስደተኞች አንዷ መዳረሻ በሆነችው የወቅቱ የአውሮፓ ሕብረት ፕሬዝዳንት ጣልያን አነሳሽነት የሚካሄደው ይህ ውይይት በአጭርና ረዥም ጊዜ የሚተገበሩ ግቦች ያመነጫል፤ ተብሎ ተጠብቋል።

በሌላ በኩል የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ-ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ ትላንት ስትራስበርግ ፈረንሳይ ለሚገኙት የአዉሮፓ ፓርላማና ምክር ቤት ንግግር ስለ ስደተኞች ሰብአዊ መብትና መከበር ንግግር አድርገዋል።

ርእስ ሊቃነ-ጳጳሱ በሁለቱም ስፍራዎች ባደረጉት ንግግር አዉሮፓ የቆመችለትን ሰብአዊ መብትን የማክበር መርህና ዴሞክራዊ እንድታከብር ጥሪ አድርገዋል።

የሮማው ርዕሰ ሊቃነ-ጳጳስ በ25 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአውሮፓ ተቋማት ያሰሙትን ንግግር ተንተርሶ የተጠናቀረ ዘገባ ነው።

በርዕሶቹ ላይ የተጠናቀሩትን የእነዚህን ዘገባዎች ዝርዝር ከዚህ ያድምጡ፤

Source:: voanews

ቅኝ ግዛት እና ሕዝቡን ቢራ እንዲጠጣ ማበረታታ ምን እና ምን ነበሩ? ዳቦ ሳንጠግብ እና የምናነበውን ጋዜጣ ሁሉ ዘግተው አዕምሯችንን እያደነዘዙ የቢራ ፋብሪካ መደርደር ምን ይባላል?

0
0
addis_biraበባዕዳን በቅኝ ግዛት ተይዘው የነበሩ ሀገሮች ሁለት ዋና ዋና ሀብታቸውን አጥተዋል።( በነገራችን ላይ በባዕዳን ቅኝ ግዛት የተያዙቱኑ ነው ያልኩት እንጂ ፕሬዝዳንት መሆን ያማረው ሁሉ ቅኝ ግዛት ነበርኩ እያለ የእራሱን እና የህዝቡን ክብር ገደል የሚጨምረውን አይመለከትም።)
እነኝ በቅኝ ግዛት የተያዙ ሃገራት ካጡት ሀብት መካከል የመጀምርያው ምጣኔ ሀብታቸው የባዕዳን ገዢዎቻቸውን ምጣኔ ሀብት እንዲያገለግል ተደርጎ መዋቀሩ ሲሆን ሌላው የነበራቸውን ከቀደሙት የወረሱት ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ ነው።ሃገራቱ እንዲያመርቱ የተደረጉትም ሆነ ወደውጭ የሚልኩት ምርት የገዢዎቻቸውን የጥሬ ዕቃ ፍላጎት ብቻ ላይ እንዲያተኩር ተደረገ።ዛሬ እነ ኬንያ፣ታንዛንያ እና ዑጋንዳን ብንመለከት ሃገራቱ ለንግድ የሚሆኑ የእርሻ ምርታቸው በወቅቱ እንግሊዝ ትፈልገው ከነበረው ምርት ጋር ብቻ እንዲቆራኝ የተደረገ ነው።
በአንፃሩ ደግሞ አውሮፓውያን በእነርሱ ክህሎት ብቻ የሚሰራውን ምርት ቅኝ ተገዢዎች እንዲቀበሉት አደረጉ።አፍሪካውያን ቡና ከመጠጣት ቢራ እንዲጠጡ እና እንዲለማመዱ ተደረጉ።እንድያውም አንዳንድ ቦታ ቢራ ለመጠጣት ያልደረሱ ታዳጊዎች ሁሉ በሰሩት ሥራ ልክ የሚከፈላቸው ቢራ የነበረበት ወቅት ነበር።የቢራ መጠጥ ከቅኝ ግዛት በኃላም በሰፊው ተለመደ።ብርጭቆ ተጋጨ።በዓል የሚከበረው በቢራ እና በቢራ ብቻ ሆነ። ዛሬ በዑጋንዳ እና በታንዛንያ ቢራ የሚጠጣውን ያክል ቡና አይጠጣም።በአውሮፓ ደግሞ ቡና የሚጠጣውን ያክል ቢራ አይጠጣም።አፍሪካውያን የሚጠጡበት ቢራ በትንሹ ግማሽ ሊትር የሚይዝ ነው።አውሮፓውያን ቡና የሚጠጡበት ስኒ የሻይ ብርጭቆ ያክላል።ቡናው ለንቃት ወደ አውሮፓ ይላካል።
የመንገድ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ የቅኝ ገዢዎች የሰሩት አሁንም የሀገራቸውን ምጣኔ ሃብት እንዲገነባ ነው።ለምሳሌ የወደብ ቦታዎች የሚመረጡት የሀገራቱን አንጡራ ሀብት በተገቢ መልክ ለማውጣት ከማመቸቱ አንፃር እንጂ ለሕዝብ ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር አይደለም።በምዕራብ አፍሪካ እና በምስራቅ አፍሪካ በቅኝ ገዥዎች የተሰሩትን ወደቦች መመልከት ይቻላል።
bira_logo_dashenኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ካልተገዙ ጥቂት ሃገራት አንዷ ነች።ኢትዮጵያውያንን ቡና አትጠጡ ቢራ ብቻ ጠጡ ብሎ ያስገደዳቸው ቅኝ ገዢ አልነበረባቸውም።እድሜ በደማቸው ሀገራቸውን አስከብረው ለኖሩት አባቶቻችን እና እናቶቻችን።እኛ እንደ ብዙ የአፍሪካ ሃገራት ዋና ከተማችንን የቅኝ ገዢዎች አልመረጡልንም። አለመምረጥ ብቻ አይደለም የከተሞቻችን ህንፃዎች እና መንገዶች በአብዛኛው የተሰሩት በእራሳችን መሀንዲሶች ነው።የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃቤት ፕላን ሲቀርብ አንድ ፈረንሳዊ መሃንዲስ ባለ ብዙ ፎቅ እንዲሆን አድርጎ አቅርቦ ነበር።በኃላ ግን ኢትዮጵያዊው መሃንዲስ (ስማቸውን አላስታውስም) ወደ ንጉሡ ቀርበው ”ይህንን ያህል ፎቅ ብዙ ሕዝብ በእየለቱ በሚወጣበት እና በሚገባበት ህንፃ ላይ አይሆንም።ይህ ማለት ከሀገሩ ሊፍት እንድናስገባ ሊያደርገን ነው።ከእዝያ ይልቅ ወደጎን ነው መለጠጥ ያለበት” ብለው ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ማዘጋጃ ቤቱ ወደጎን እንዲሰፋ ተደረገ።በእዚህም ብዙ ሕዝብ ለጉዳዩ በቀላሉ ለመውጣት እና ለመግባት ቻለ።ቅኝ ገዢዎች መሰረተ ልማቱን እንዴት ለሀገራቸው ኢንዱስትሪዎች መጋቢ እንዲሆን አድርገው እንደሚቀርፁ የሚያመላክት አንዱ ማሳያ ነው የማዘጋጃ ቤቱ ህንፃ ጉዳይ።

ቅኝ ግዛት መዘዙ ብዙ ነው።ጉዳቱ የሚታወቀው ትውልድ በተቀያየረ ቁጥር ነው።

ዛሬ ግን ያልገባኝ ጉዳይ በኢትዮጵያ የቢራ ፋብሪካ እንደ አሸን መፍላት ነው።በምግብ እራሷን ያልቻለች ሃገር ለምንድነው የእህል ቀበኛ የቢራ ፋብሪካዎች እንዲበዙላት የተደረገው? ብዙ ተመጣጣኝ ምግብ ማቀናበርያ በምትፈልግ ሀገር ውስጥ ለምን ለቢራ ፋብሪካ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲወጣ ይደረጋል? በኑሮ ውድነት በሚንገላታ ሕዝብ መካከል አማላይ የሆኑ የቢራ ማስታወቅያዎች ምን ይሰሩለታል? ቢራ ከሀገር ይጥፋ አይባልም።ሰው እንደ ምርጫው እና ፍላጎቱ ሊጎነጭ ይችላል።ግን እንደ ፖሊሲ ትኩረት ተሰጥቶት ሊደከምበት አይገባም።የኢህአዲግ የንግድ ድርጅቶች ሳይቀሩ የቢራ ምርት ላይ በከፍተኛ ትኩረት ሲሰሩ ይታያል።የቢራ ፋብሪካ መመስረት ብቻ ሳይሆን የማስፋፋት ሥራ በጣም እየተሰራበት ነው።በቅርቡ ወደ ገበያ ሊመጣ ነው የተባለው የራያ ቢራን ጨምሮ 8 የቢራ ፋብሪካዎች አሉ።እነርሱም አዲስ ቢራ፣በደሌ ቢራ፣ሐረር ቢራ፣ዳሸን ቢራ፣ሜታ ቢራ፣ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ፣ባቲ ቢራ እና በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው ራያ ቢራ ናቸው።
ባጠቃላይ ይህንን ማለት ይቻላል። ፋብሪካዎቹ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ።ግን የቢራ ፋብሪካዎች እንደ አሸን መፍላት እህልም ሆነ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ከሚገመተው በላይ ይበላሉ።ፋብሪካ ይኑረን። ግን አዋጪ እና ሌሎች አንገብጋቢ ፋብሪካዎች ለምን አይበልጡብንም? ነው ጥያቄው። ደግሞስ ቅኝ ገዢዎች ከብዙ ጥቅማቸው አንፃር አደረጉት።እኛ ቅኝ ያልተገዛነውስ? ኢህአዲግ/ወያኔ በወሎ እና በጎንደር ብቻ አዳዲስ የቢራ ፋብሪካዎችን ከፍቷል።አንድ ቢራ ለመጥመቅ ከፍተኛ የምግብ እህል ፍጆታ እና ብዙ ሺህ የተጣራ ንፁህ ውሃ እንደሚፈልግ ይታወቃል።ቅኝ ገዢዎች አፍሪካውያን ቢራ እየጠጡ እንዲናውዙ ማድረግ አንዱ የተሳካላቸው ስራ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።የኛ ገዢዎች በየመንደሩ የቢራ ፋብሪካ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያወጡ የሚከፍቱልን ለምንድን ነው? ዳቦ ሳንጠግብ እና የምናነበውን ጋዜጣ ሁሉ ዘግተው አዕምሯችንን እያደነዘዙ የቢራ ፋብሪካ መደርደር ምን ይባላል? ከየት የተማሯት ”ጥበብ” ነች?

ጉዳያችን
ህዳር 18/2007 ዓም (መጋቢት 4/2006 ዓም ወጥቶ የነበረ)

Source:: gudayachn

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ለአዳሩ ሰልፍ የእውቅና ደብዳቤ አስገባ • ቦታው መስቀል አደባባይ እንዲሆን ወስኗል

0
0

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ከህዳር 27/2007 ዓ.ም እስከ ህዳር 28/2007 ዓ.ም ለሚደረገው የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ህዳር 18/2007 ዓ.ም ለአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል የእውቅና ደብዳቤ አስገባ፡፡
semayawi
ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል የገባው ደብዳቤ በሰማያዊ፣ መኢዴፓ እና ኢብአፓ ተፈርሞ የገባ ሲሆን የእውቅና ደብዳቤውንም ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የሰማያዊ ፓርቲና የትብብሩ ሊቀመንበር፣ የከንባታ ህዝቦች ሊቀመንበርና የትብብብሩ ም/ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርጌሎ፣ አቶ ግርማ በቀለ ከኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና የትብብሩ ፀኃፊ እና የመኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ አቶ ኑሪ ሙደሲር አስገብተዋል፡፡

የትብብሩ አመራሮች ወደ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ በሄዱበት ወቅት የአቶ ማርቆስ ተወካይ ለሆኑት አቶ ፈለቀ አበበ ደብዳቤውን ለመስጠት ጥረት ቢያደርጉም ተወካዩ ‹‹የከንቲባ ጉዳዮች ጽ/ቤ ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው የለም፡፡ እሱ ካልመራበት መቀበል አንችልም›› በሚል ደብዳቤውን አልቀበልም እንዳሏቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ አመራሮቹ ወደ አቶ አሰግድ ቢሮ ቢያቀኑም እንዳላገኙዋቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የትብብሩ አመራሮች ደብዳቤ መስጠት እንጂ ደብዳቤ ማስመራት የሰራተኞቹ እንጂ የእነሱ ስራ እንዳልሆነ በመግለጽ ደብዳቤውን ዛሬ ህዳር 18/2007 ዓ.ም ታመዋል የተባሉት የአቶ ማርቆስ ተወካይ የሆኑት አቶ ፈለቀ ቢሮ በአራት ምስክሮች ፊት አስቀምጠው መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ አመራሮቹ የእውቅና ደብዳቤውን አቶ ፈለቀ ቢሮ አስቀምጠው ከመውጣታቸውም ባሻገር በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በፈጣን መልዕክት (ኢ ኤም ኤስ) በሪኮመንዴ ቁጥር eg157416502et መላካቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዳር ሰላማዊ ሰልፉ ህዳር 27 ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተጀምሮ ህዳር 28 ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሲሆን ቦታውም መስቀል አደባባይ ላይ እንደሚሆን መወሰኑ ታውቋል፡፡

የትብብሩ አመራሮች የእውቅና ደብዳቤውን ለማስገባት በሄዱበት ወቅት በቦታው የትብብሩ አመራሮች የሚያውቋቸው ደህንነቶች ባለ ጉዳይ በመምሰል ይመላለሱ እንደነበርና ፖሊሶችም ይከታተሉ እንደነበር ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡


የማለዳ ወግ …በጅዳ ኮሚኒቲ የምርጫው ሽሽት አንድምታ   … (ነቢዩ ሲራክ)

0
0
*የልጆቻችን ት/ቤት ለመታደግ ለምን እንትጋ?
* በጅዳ ኮሚኒቲ የተጠራው ስብሰባ ለሶስት ሳምንት ተራዘመ
* 80 ሽህ ነዋሪ ባለበት ሃገር ከ130 በላይ ነዋሪዎች አልተገኘም ፣ ለምን ?yenma2ከ 80 ሽህ በላይ ነዋሪ እንዳለበት በሚገመተው የቀይ ባህር ዳርቻ ውብ ከተማችን ጅዳ 600 የኮሚኒቲውን መታወቂያ ያደሱ አባል አሏት፣ ትናንት ሃሙስ ህዳር 18 ቀን 2007 ዓም በተጠራው በስብሰባ የተገኘው በጣት የሚቆጠሩ አዳዲስ ነዋሪዎችንና ወደ መቶ የሚጠጉት ሰራተኞችን ጨምሮ በአጠቃላይ  ከ130 ያልበለጠ ነዋሪ ነበር ።  ነዋሪው በተለይም ወላጁ በዚህ ወሳኝ ቀን ዝር ማለት አልቻለም፣ ስብሰባውም እንደተለመደው በደንቡ መሰረት ” ምልአተ ጉባኤ አይሞላም ” ተብሎ ተበትኗል ! ይህ የነዋሪው ዝምታና ኩርፊያ መግለጫ ሽሽት የገዘፈው ችግር ማሳያ ከሆነ መልካም ነው !  ግን ነዋሪው ለምን ከወሳኙ ተሳትፎ ሸሸ ?

መቸም ያልተመቸ ነገር አለና ነዋሪው በአንድ ያደመ ይመስል ከመቅረብ መራቅን መርጦ ዝም ፣ ጭጭ ብሏል ። በተለይም የሶስት ሽህ ተማሪዎችን በጅዳ የኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ  ት/ቤት የሚያስተምረው ወላጅ ት/ቤቱን ለመታደግ የሚያስችለው የኮሚቲ መ/ቤት ሪፖርት ለመስማትም ሆነ ፣  አዲስ ምርጫ ለማካሔድ ፍላጎት አለማሳየቱን በውል ላጤነው ያሳስባል።

እኔ የማውቀው …

እኔ እስከሚገባኝ ልክና እስከማውቀው ነዋሪው ዝምታ  ኩርፊያና ሽሽት መምረጡ በዓመት የሚከፈለው የአባልነት መዋጮ ከብዶት አይደለም።  ጥቅማ ጥቅሙ ጎድሎበትም ከአባልነት የሸሸ ነዋሪ እንደሌለ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ ።  ዳሩ ግና በቆንስሉም ሆነ  በኮሚኒቲው ዙሪያ በማህበራዊ ችግሩ ፣ በመብት ማስጠበቁ እና በዙሪያው በሚሰጠው ግልጋሎት ነዋሪው ከፍቶታልና ሸሽቷል ፣ በውስጥም በውጭም አሰራሩ ተፈጥርቆ ወደ ቀናው ጎዳማ አልላወስ ያለው ትልቁ ማህበር እያደር መኮስመኑ ፣ በብቸኝነት በሚያስተዳድረው ካፊቴሪያ ፣  ሻንጣ ቅበላና በትምህርት ቤቱ  በአደባባይ በሚታይ በሚሰማው ኢ ፍትሃዊ አካሄድ መደፍጠጡ  ፣ የተቋሙ ሁለንተናዊ አገልግሎት አሰጣጥ እያደር መዝቀጥ ፣  ብሎም በማዕከሉ ግልጽነት የሌለው ተደጋጋሚ  የተውሸከሸከ አካሔድ ነዋሪው ተስፋ መቁረጡ እውነት ነው!  ይህ ሆነና እውነቱ ነዋሪው በነቂስ ዝምታ ፣ ኩርፊያ ሽሽት መምረጡን ነው የማውቀው …ሁሉም ትክክል ነው …
ከካፍቴሪያ እስከ ት/ቤቱ ችግር አለ ? …አዎ  !
ቤቱ ፍትሃዊ ባልሆነ አሰራር ይሰራል? ቅጥር አሰራሩ በቤተሰብ የተጨማለቀ ነው ? …አዎ  !  ቤቱ የአስተዳደር ብልሹነት የነገሰበት ነው ? …አዎ  !

* ነባራዊ ሁኔታውን ያላገናዘበው የእኩዮች ዘመቻ …

ከትናንት ጀምሮ በአደገኛ መንታ መንገድ ስላለው የኮሚኒቲው መስሪያ ቤት ” ለምን የሰላ ሂስ ታቀርባላችሁ “,በሚል አንድምታ እዚህ ግባ የማይባል የስም ማንቋሸሽ ዘመቻም ተጀምሯል።  የስም ማጥፋት ዘመቻው አቀንቃኞችም ሆኑ ኮሚኒቲውን ለዚህ የከፋ አደጋ የጣሉት የጥፋቱ ባለድርሻ አካላት ከቧልት ስድባቸው ተቆጥበው መመርመር ያለባቸው እውነታ ግን ” ኮሚኒቲውን ነዋሪው ለምን ሸሸው?  ” የሚለውን ውሃ የሚያነሳ ጥያቄ ቢሆን ለሚያወዛግባቸውና ለሚያንቀዠቅዣቸው መልስና ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት በቻሉ  ነበር ።

ኮሚኒቲውን ህዝባዊነት አሳጥተው የአንድ ወገን መፈንጫ ለማድረግ ምላሳቸውን ብቻ አሹለው ለዲስኩር  ፣ ለስድብ፣ ለድንፋታና ለከንቱ ውዳሴ የሚፏልሉት ወገኖች  ይህን ደረቅ እውነት በትክክል መረዳት ቢችሉት መልካም በሆነ ነበር  ።  ግን አልሆነም  ! አዙሮ ማየትን ለታደለ ትናንት ያየነውን ጨምሮ በተደጋጋሚ በኮሚኒቲው ምርጫ በግላጭ የታየው እውነታ የሚያሳየው ከዚህ ያለፈ እውነታን አይደለም ። ሌላው ቢቀር  ወላጁ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ያለው የትምህርት ቤቱን ጉዳይ አሳስቦትና የራሴ ጉዳይ ነው ብሎ ለምን ንቁ ተሳትፎ አላሳየም?  ለምንስ ስብሰባ አለ በተባለ ቁጥር በዙሪያው ዝር ማለት አልፈለገም  ? ብለን መጠየቅ አለብን  ፣ ከፍጹም የጎጥ ስሜት ፉክክር ወጥተን ፣ በቤተሰብ የተማከለውን ማዕከል ሰርተው ውለው እንዲገቡ የምንፈልጋቸው ቤተሰቦቻችን ከመከላከል የመነጨ ተራ ጉዳይ ወደ ጎን ትተን ለመሰረታዊ ችግሩና ለነዋሪው  ዝምታ  ኩርፊያና ሽሽት መልስ ልናገኝለት ይገባል። መፍትሔ እንኳ ማምጣት ቢገድ ትክክለኛ መልሱን ማወቅ ለቀጣዩ ጉዞ ይጠቅማል ። መልሱን ከተረዳችሁ ለምንወተውተው እውነት ምላሽ ማግኘት ነውና የነዋሪውን ችግር በመጠኑም ቢሆን እንድትረዱት ያደርጋችሁ ይመስለኛል  !

ሃቅ ስንናገር የጥላቻ ዘመቻ ማቅናት የሚቀድማችሁ እነ እንቶኔ በግለሰቦች ማንነታችን ላይ ውርጅብኙን ትታችሁ በቀረበው አስተሳሰብ ዙሩያ ምላሽና መፍትሔ ሃሳብ አፍልቁ …  እከችኋለሁ  ! የቆማችሁት ለህዝብ ከሆነ አቅሙ እንኳ ባይፈቅድላችሁ በቅንነት ከተነሳችሁ አይገዳችሁም  ” ሰው ለምን ዝም ይላል?  “የፈራ ይመስል ” ሰው ለምን ይሸሻል? በማለት ራሳችሁን ጠይቁ ፣ አማክሩት ፣ አንክሮም ሰጥታችሁ ለሽሽቱ ምላሽ ብትፈልጉለት መልካም ነው …

* ሁለቱን መከራዎች እንዴት እንቻል …?

ነዋሪው ሙሉ ባይባል ቢያንስ የኮሚኒቲው አባል የሆነው ከ80 ሽህ 600 ያልነው ንቁ አባል አኩርፎም በሉት ተማሮ ዝምታን መርጦ ሸሽቷል  !  … በዝምታና ኩርፊያ ሽሽትን ለመረጠውን ውስን አባል ሳይሆን በነቂስ የጅዳ ነዋሪ መጻኤ ህይወት መሻሻል ” አሳስቧቸው”የኢህአዴግ አባላት በኮሚኒቲው ምርጫ ዙሪያ ሲመክሩ ነው የሰነበቱት ፣ ይህም በማድረግ በአዲሱ ምርጫ የራሳቸው የሚሉትን አካሔድ ለመከተል ተስማምተዋል።  የአባልነት መብታቸውን ተጠቅመው በመምከር ማዘከራቸው ተቃውሞ የለኝም ። ኮሚኒቲውን ማስተዳደር ቢችሉ ከፖርቲው በመምጣታቸው ብቻም አልቃወማቸውም ፣ መስራት ከቻሉ ማህበራዊ ችግራችን ይቀርፋሉና መልካም ነበር ። ነገር ግን የስራ ክህሎትም ብቃት ሆነ የወገን ተቆርቋሪነት ስሜታቸውና የትጋታቸውን ልኬታ በተለያዩ አደረጃጀቶች ፣ ማህበራትና በራሱ በኮሚኒቲው ውስጥ እናውቀዋለን ፣  በተደጋጋሚ አይተነዋልና የድርጅት አባላቱን ኮሚኒቲን የመቆጣጠር አዝማሚያ አንደግፈውም ። የድርጅቶች ቀረቤታ ለጤና ነው የማንለው ኮሚኒቲው የቀረውን ሽርፍራፊ ነጻነት ተነጥቆ ስራ ሳይሰራ መልሶ አዘቅት የሚያገባ አካሔድ ብለን እንሰጋለንና ነው ! እናም ነጻነትም አጥተን ስራም ሳይሰራ ሁለት መከራ መሸከም ይከብደናልና …ተውን  !   ….

*  ተቋሙን ለማዳን ወሳኙ ተሳትፎ …

ነዋሪው ኮሚኒቲውን ለመታደግ ከወዲሁ ካልተጋ አደጋው ሃያል ነው። ምልአተ ጉባኤ ሳይሞላ ቀርቶ ለሶስት ሳምንት የተላለፈው ስብሰባም ሲቀጥል መከረኛውን ህግና ደንብ ይጠቀስና እንደለመድነው በመጣው ሰማንያና መቶ ሰው ምርጫ ከማድረግ የሚመልሰው እንደሌለ ልብ በሉ !  በዚህ ሁኔታ በዝምታ፣ ኩርፊያና  ሽሽት ከነጎድን ተመልሰን ወደ መከራው አዙሩቱ እንደሚያስገቡን አትጠራጠሩ  !  ዝምታን የመረጠውና የሸሸው ነዋሪ ምክንያት አለው ብንልና ብንዘረዝረውም ችግሩን ለመቅረፍ ዝምታ ፣ ኩርፊያና ሽሽቱ ግን አዋጭ አይደለም ። የኮሚኒቲው አባል በመሆን ንቁ ተሳይፎ በማድረግ ለውጥ ለማምጣት ይቻላል።  ሰአቱ አሁን ብቻ ነው ! ሌላው ቢቀር በት/ቤቱ የሚያስተምር ወላጅ ብሶቱን  ” እህ ” ብሎ ችሎ የኮሚኒቲው አባል በመሆን በነጻነት የሚፈልጋቸውን መምረጥ አለበት … በአደጋ ላይ ያለውን የትምህርት ተቋም ለጥቂት አፈ ቀላጤዎች በትጉህ ስራቸው ለማናውቃቸው የመንግስት ባለሟሎች ኮሚኒቲውን  ማስረከብ የለበትም።  በቀጣይም ለበከተው አስተዳደርና አሰራር  ሲሳይ አድርጎ በራሱ ጉዳይና ቤት መሸሸቱ አዋጭ አይደለም !
ሲደቆስ ለከረመ ለባጀው ነዋሪ መሰረታዊ ችግር እንዴት መፍትሔ እናምጣ  ?

እንደኔ እንደኔ …
ዝምታን ሰብሮ ፣ ኩርፊያን ድል ነስቶ ሽሽትን በማቆም ፣ የኮሚኒቲው አባል በመሆንና በመምረጥ የልጆቻችን ት/ቤት ላይ መወሰን ከቻልን ብቸኛ የተ/ቤታችን ባለቤቶች እንሆናለን ! ይህን እውን ለማድረግ  አማራጩ ዝምታ ፣ ኩርፊያና መሸሸት ሳይሆን በቀጠይ ሶስት ሳምንት በተቀጠረው ስብሰባ ለመገኘት የኮሚኒቲው አባል በመሆን አደጋ ያንዣበበበትን ማዕከል መታደግ ይቻላል  !

እስኪ ቸር ያሰማን  !

ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 19 ቀን 2007 ዓም

የሕወሐት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት ፒ.ኤች.ዲዎችን ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት መግዛታቸውን ቀጥለዋል

0
0

(ከኢየሩሳሌም አርአያ)

የሕወሐት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት ፒ.ኤች.ዲዎችን ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት እየገዙ እንዳሉ የቅርብ ምንጮች አስታወቁ።
news
የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሐጐስ ጐደፋይና ምክትላቸው አቶ አታክልቲ እንደሚገኙበት የጠቀሱት ምንጮቹ ለሁለቱ ባለስልጣናት በመቀሌ ሆስፒታል የሚሰራ የባዮስታቲክስ ባለሙያ በኩል የጥናት ፕሮፖዛላቸውን አሰርተው ፕሮፖዛሉ ፀድቆ ዋናውን ጥናት ይህ ባለሙያ ግለሰብ እየሰራላቸው እንደሚገኝ አያይዘው ገልፀዋል።

ባለስልጣናቱ ስለጥናቱ አንዳችም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ምንጮቹ አጋልጠዋል። ሌሎች ስድስት የህወሀት ባለስልጣናትም የማስተርስና ፒ.ኤች.ዲ ጥናት እየፃፈላቸው እንደሚገኝ ምንጮቹ አክለው ገልፀዋል። ሌሎች የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችም የዚህ ህገወጥ ተግባር ተሳታፊዎች ናቸው ያሉት ምንጮቹ በተለይ ሪፍት ቫሊ የተባለውን የግል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚስተካከል የለም ብለዋል። የኦህዴድ ባለስልጥናት ባለድርሻ የሆኑበት ይህ ዩኒቨርሲቲ ገንዘብ ለከፈለ ሁሉ ሰነድ አዘጋጅቶ ዲግሪና ማስተርስ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

የወያኔ ምርጫ –ገረጭራጫ! (ሥርጉተ ሥላሴ)

0
0

ይሄ አዲስ የሚሉት የነጮቹ ዓመት ደግሞ አይደክመው መጣሁ እያለ ሃገር ምድሩን አካሎታል። አልኳችሁ እሱ ለሚመላለሰው፤ የእሱ ጫማ እልቅ ለሚለው እኔኑ ድክም – ግን አልገርምም?! ህም – ስገርም። እርግጥ ነው ለእነሱ አዲስ ነው – ያደላቸው።

2007 electionወይ አቶ ምርጫ፤ ወይ አንተ ወይ እኛ አንደክም ያው አራት አመትህን እዬጠበቅህ ለማጥበቅ – ለማክረር በገረጭራጫ ባህሪ ለመቁላትና ለመፍጨት መጣሁ – መጣሁ ትለናለህ። እኔ የማዝነው በፍታዋራሪ ሂደት ነው። ባዶን አዝሎ እስከ መቼ እንደሚዳክር ግርም ይለኛል።

እንደ እኔ እንደ ሥርጉተ ምርጫ የሚመረጥ ነገር ሲኖር ወይንም ለማማረጥ የሚያስችል ጠረን ሲኖር ነው። በምድረበዳ ላይ – … ግን እኔ እንጃ ነው – ሁልጊዜ ኩታራ፣ አንድም ቀን ግርጫ ጸጉሩ በመንፈሱ ላልሰከነ አረግራጊ ዬጎጥ ማንፌስቶ ሩህ መባዘን ግን – ህም ነው እም።

አሁንም እኔው እላለሁ ምርጫ መከባበሩም፣ መደማመጡም፣ ትብስ ትብሺ መባባሉ፣ ቀና ፉክክሩ ሲኖር ነው ለዛ ወግ የሚደረሰው። ግን ግን ክብረቶቼ ከላይ ከደርቡ ጉብ ያደረኳት እርእስ ቃሏ አዲስ ከሆነች ትርጉሟ እንዲህ – „ገረጭራጫ“ ፈጽሞ – ለምንም ነገር የማይመች – ጸባዬ ጎርባጣ፣ ጸባዩን ለመተርጎምም የማይቻል – ውጥንቅጥ፤ ወጣገብ የሆነ፤ ቁርጥርጥ ያለ ሥነ ምግባር ያለው፤ ቋሚ ባህሬ የሌለው፤ ነጭናጫና ሰላምን ፋቂ፤ የሚወራጭ – ተናካሽ ጦሮ* እንደ ማለት ነው በጥቂቱ። ጥሎበት ደግሞ የወያኔ የምርጫ ሂደት እኔ ከሰጠሁት ትርጓሜ በከፋ ሁኔታ እጅግ ወልደ -ግራ ወልጋዳ ነው። የሆነ አይሉት በረዶ አይሉት እሳት አይሉት እረመጥ አይሉት ወጀብ- በቃ መቀቀያ ኮንቴይነር ነገር፤ ውሎው ጉዞው የማይታወቅ ቅብጥርስ – ምንትስ ነው … እንደ ተፈጥሮው ….

የወያኔ የምርጫ ሂደት መሰረቱ የስታሊን ዶክተሪን ነው። በዚህ መስማማት አለብን። እኛ ብቻም ሳንሆን ብድሩንም እርዳታውንም የሚያጎርፉለት የውጭ ሀገር ዲታዎች፤ በአንድ በኩል ፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር አይንህ ላፈር እያሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጎጡን ሶሻሊሳታዊ ጎፈሬ የባጣጥራሉ እነ-አሜሪካ። ስታሊን ማን እንደሆነ ደግሞ አቶ ጉጉል ቢጠዬቅ ቀልጣፌ ዘረጋግፎ ከነዝክንትሎ በቃኝ እስክትሉ ድረስ ያመጣዋል …. ለሚፈልግ ማለት ነው። የሾሻሊዝም ርዕዮት ብዙኃኑን የዳቦ እኩል ተጠቃሚ ይሆናል ከሚል እሳቤ የመነጨ ቢሆንም ወደ ተግባር በስው እጅ ሲድበለበል ግን ፍጹም ነጭናጫና አንባገነን፤ ገርጭራጫና አውሬ ባህሪ ነው ያለው። ይወራጫል – ይፎነጫጭራል – ይናከሳል – ያቆስላል — በአሳቻ* ከአገኝም አጋድሞ – ቅርጥም።

ምርጫና ሾሻሊዝም /ምርጫን ህብረተሳባዊነት።/

ምርጫ የሚባለው ነገር በሶሻሊዝም ሽሙንሙን ብለው፣ ዝንጥ ባሉ ቄንጠኛ፤ እንደ ዘመነኛው የፋሽን ዕይታ ሽቅርቅር ባሉ ብራናዎችና – ብዕሮች ይሰተናገዳል። ከህገ መንግሥቱ ጀምሮ መዋቅሩ፣ የአፈጻጸም መመሪያው ማኒፌስቶው ኩሉም ሻዶውም ሳይቀርባቸው አምረው ሽክ ብለው ይሰናዳሉ። የተግባር ሂደቱ ግን አሹቅ ነው። የመንግሥት መዋቅር ለመዘርጋት ከታች ወደ ላይ ምርጫው የሚከናወነው ንጥር ባለ ድርጅታዊ ሥራ ነው። ማጣሪያውም ድርጀታዊ ሥራ በቃ! ገዢው ፓርቲ የህዝቡን ፍላጎት ሳይሆን የፓርቲውን ህልውና ሊያስቀጥሉ የሚችሉትን፤ ለፓርቲው ፍላጎት ጥበቃ ሊያድርጉ ይችላሉ የሚላቸውን የራሱን ደምና ሥጋ ከታች እስከ ላይ የሚደረድረው ከዓመት በፊት ነው። ቀድሞ። ፎቷቸው ቢያምረውም ባያምረውም – ብቻ አንቀልባ ይሁኑለት።

ዬምርጫ ውድድር ላይ ተወዳዳሪዎች ከዝቅተኛው ክፍልም እዬተባለ ከሚኒስተሮች ጋር እኩል አንድ የእኔ ቢጤ አቧራ ላይ ያለ እጩ ተወዳዳሪ ይሆናል። ታዲያላችሁ ከምርጫው ቀደም ብሎ አንድ ጉልበታም ተግባር ይከወናል። ያም ምስኪኑ ለህዝብ ቀርቦ እኔ ከውድድሩ እራሴን አግልያለሁ – በፍቃዴ እንዲል ይደረጋል። በተጨማሪም ከእኔ ይልቅ አቶ ወይንም ጓድ እከሌ የበለጠ ለሀገራዊ ጉዳይ ወሳኝ ናቸውና እሳቸውን ምረጡ ብሎ ለተወዳዳሪው ካድሬ ሆኖ እርፍ … በርድ – ብርድ። ወይንም እጩ ተለጣፊው ተወዳዳሪ ወይንም ማሳሳቻ አዘናጊ ተወዳዳሪው ጤናዬ ተጓድሏ፤ ወይንም ፍላጎቴ በኗል፤ ብቻ አንድ የቀደመ ጠንካራ ምክንያት ተፈጥሮ ከህዝብ የወጣው እጩ እንደራሴ እራሱን ያሰናብታል – በፈቃዱ። ፈቃዱ ግን ስውር ነው። ለውድድር እጩ የሚሆነውም በስውር ዬሚሰጠውን የቤት ሥራ ለመከወን መሆኑን – ያውቀዋል። ከአንድ የሀገር መሪ የፕሮቶኮል ሹም ጋር ተወዳድሮ እንደማያሸንፈው …. ይሄ እንግዲህ የሶሻሊዝም የተቀበረ ዬነፃነት ግበዐተ – መሬት  ንድፈ ሃሳብ ነው። አረሙ ወያኔም የሚመራውም በዚህ ነፃነት በተጎረጎረበት – በተቦረቦረበት መንፈስ ነው …. 100%

የምርጫው ውቂ ደብልቂ በድለቃ ይከወናል። በታቀደው መሰረት። ተማራጩም ቃል ኪዳኑ – ውሉ ለህዝብ ፍላጎት ተፈፃሚነት ሳይሆን በድርጅታዊ ሥራ ቦታውን ሆነ ሥልጣኑን ላስገኘለት ገዢ ፓርቲ ይሆናል። ምደባ ነው እንጂ በሶሻሊዝም ምርጫ ፈጽሞ ኑሮ አያውቅም። በምርጫና በምደባ መካከል ያለው ልዩነት በሰውና በእንሰሳት መካከል እንዳለው ያህል ነው። ቀድሞውን ነገር ተማራጮች የህዝብ ጉዳይ ቁባችውም አይደለም። ስለምን? በህዝብ ድምጽ ሳይሆን በድርጅታዊ ተግባር ነው የተመደቡትና። ስለዚህ ተቆርቋሪነታቸው ምደባውን ወይንም ሹመቱን ላፀደቀላቸው ድርጅት ያዘነበለ ይሆናል።

መቼም የጹሑፌ ታዳሚዎች እንደምታውቁትም በጣም ከጥቂቶች በስተቀር ጥቅሙን የሚፃረር ተጠቃሚ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም። እንግዲህ ከዚህ ላይ  ህዝብ የተራበው ተስፋ መክኖ ይቀራል። ራህብተኛው ከተስፋው ጋር በዚህ በሰላ ደባ ይተላለፋል። ይህን ሂደት የሚያውቁት በውስጡ ያለፉና የኖሩ ሰዎች እንጂ ሰፊው ህዝብ ይህን ድብልብል ጉድ አያውቀውም። የምርጫው ወረቀት ሲቆጠር አንድ ብቻውን የተወዳደረ ሰው ብቻ ይሆናል የሚያሸንፈው። የምርጫ ዳንኪራው ማስመሰልን ለመሞሸር ብቻ ነው። የሀገር ሃብት የሆነው ወጪውም – ጉልበትም – ሃይልም የቅስቀሳና የፕሮፖጋንዳ ሆነ ዬምርጫ ኮማንድ ፖስቱ ትርምስ – ለምንም! እርግጥ ለውጪ ሚዲያ ብርንዶ ነው።

እራሳቸውን ሳያገሉ ለቁጥር ማሟያ በሚቀጥሉትም ላይ ቢሆን፤ ገዢው ፓርቲ በፈለገው መስመር ገብቶ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ሊሰጡበት የሚገባ ቀጭን ትእዛዝ በድርጅታዊ ሥራ መስመር አስቀድሞ ይነግራቸዋል። ስለዚህ ዝንባሌው ተጣቃሎ የገዢውን ፓርቲ በርሚል ቲፍ አድርጎ ይሞላዋል። ማሟያዋች ተንሳፈው ይቀራሉ። ይህ ቁልጭ ያለው የሶሻሊዝም የለበጣ ጅዋጂዊቱ ነው። ሃሳብ ሲያቀርቡም የዝንጀሮ ቆንጆ ተስራታ አዳራሽ እንደ መጣች ያህል ይላገጥባቸዋል። ክብራቸው ያለ ይግባኝ ይጨፈላለቃል። ለስብሰባው ሆነ ለጉባኤው ባይታዋር መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ግልምጫው እስኪባቃው ድረስ ይከተክታቸዋል። ስለምን? በነሱ ባልሆነ ህዋ ውስጥ ስለሚኖሩ። የሚያሳዝነው ለዚህ ትራጀዲ ትዕይንት ደግሞ ብዙሃኑ ታስሯል፤ ተገርፏል፤ ተሰዷል – ሙቶለታል። በገበሬ መንደር በ97 ምርጫ ቅንጅትን የደገፉት እስካሁን ድረስ ያልተፈቱ እንደሚኖሩ በጣም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ከዛም በኋላ በተካሄደው ምርጫ ቢሆን አስተውሉ ለአንድ ተማላ ገበርዲን ለባሽ ተመረጭ ወይንም የህዝብ እንደራሴ መጠነ ሰፊ መስዋዕትንት ተከፍሏል። እነኝህ ብዙኃን ደመ ከልብ ናቸው። በዝርዝርም አይታወቁም። እኛ የምንጮኽላቸው ማዕከል ላይ ለሚታሰሩት ወይንም ለሚገደሉት መረጃው ለተገኘላቸው ብቻ ይሆናል። ምክንያቱም የእኛም አቅም ውስን ነው፤ በዛ ላይ በፍላጎት በነፃ በትርፍ ጊዜ እንደ ሆቢ ነው የነፃነት ትግልን ያህል አውራ የህልውና ጥያቄ፤ በኽረ የሰብዕዊ መብት ጉዳይ የሚሠራው፤ በመደበኛ እዬተከፈለው የሚሠራ የለም።  ይህ ማለት የህዝብን መብት የሚጠበቅ ሥርዓት መፍጠር አስፈላጊነቱን በሚገባ ያብራራል። የሚያስፈልገንም ሀገራዊ እንክብካቤና ጥበቃ ከገጠር እስከ ከተማ እኩል ለዜጎቹ የሚያደርግ ሥርዓትን መገንባት ነው። ምርጫ በመጣ ቁጥር ተስፋን አገኛለሁ በማለት ተስፈኛው ቀድሞ በከሸፈ ውድድር በዬጊዜው መሬት አልባ የሆነው ወገን ስፍር ቁጥር የለውም – የተፈናቀለው – በድብደባ ህይወቱ ያለፈው። ይህን ሁሉ ጥሰው ተስረክርከው የሚገቡ ቢኖሩም ፍላጎታቸው ሰምጦና ረግቦ ነው የሚቀረው። ለምን? ምክንያት

  1. አናሳ ናቸው – በፐርሰንት ሲሰሉ ከቁጥር በታች ናቸው ….
  2. በሌላ በኩል ደግሞ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች – ከስብሰባው በፊት ቀደም ብዬም እንደገለጽኩት ተለይተው የተለዬ ግዳጅ ይሰጣቸዋል። ይህ ማለት በድርጅታዊ ሥራ የፓርቲውን ተግባር እንዲከውኑ አስቀድሞ በጉዳዩ ዙሪያ ይደራጃሉ። አዳራሽ ውስጥ የሚታዬው ነገር ሁሉ ውስጡ ተለብዶ በአለቀ – በተወሰነ – ቀድሞ በጸደቀ ጉዳይ ላይ ነው የድጋፍ – የተቃውሞ እጂ ሲነሳና ሲወርድ ወይንም ጭብጫባው ሲደለቅ ዬሚታዬው …. ተግባባን ይሆን ውዶቼ ….
  3. በሶሻሊዝም ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ህብረ ብሄር ፓርቲ ብሎ ነገር አልተፈጠረም በራሱ በቲዎሪው። እንደ ወያኔ ሸንኮፍ ወይንም መሸፈኛ ልጣጭ ነገር በመስራት ካልሆነ በስተቀር። በሶሻሊዝም የምርጫ ህግ አንድ ሰው እስከ ህልፈቱ ድረስ በምርጫ አሸናፊ ተብሎ እንደ ገዘገዘ እንዲኖር ይፈቀድለታል።

ከዚህ ያፈነገጡ የተሻለ ራዕይ ያላቸው ምሰሶዎችን (pilars) ደግሞ ቀድሞ ነው ገረጭራጫማው የሶሻሊዝም አንባገነናዊ የምርጫ ሰረጋላ የሚጠቀጥቃቸው። ድብዛቸውን – ጥፍት። ንጹህ አዬርም በተዕቅቦ በሆነበት የካቴና ስንቅ ያደርጋቸዋል። ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚዲቅሳ፣ አቶ አንዱ አለም፣ አቶ ናትናኤል፤ አቶ በቀለ፣ አቶ ሃብታሞ አቶ ዳንኤል አቶ የሺዋስ … አብርሽ  ወዘተ … ናሙናዎች ናቸው / ለምስል – ለምልክት የሆነ ነገር እሲከጣፋ ድረስ … ይሄ „አሸባሪነት“ የሚለው የወያኔ ፍላጎት ተሸካሚ ባይረስ እኮ አጨዳውን የሚጀምረው ገና ከማለዳው ነው። … አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ወግ አሰኝቶኛል? ልለው ነው። ይሄው  ….

ሁለት የኩርድሽ የነፃነት ታጋዬችን አውቃለሁ። አንዷ ሁለት እግሯን ትግል ላይ አጥታለች። በጣም ጓደኛዬም ናት። ሌላዋም ሙሉ ዕድሜዋን እንደ ባከነች የኖረች ናት። ለራሷ ብጣቂ ጊዜ የላትም። ሁለቱም የራዲዮ ጋዜጠኞች ናቸው። የጣይቱ ልጆች ዓለምአቀፉን የሴቶችን ድምጽ ሲያሰተጋቡ የደረሰባቸውን ነገርኳቸው። አብረንም ቪዲዮውንም አዬን። እና ስለ ዓለምአቀፍ የሰብዕዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዝምታም ትንሽ አወጋጋን። ከዛ እኔ „እኛ ጥቁሮች ነን። ለነጻነት የሚደረግው ትግልም „በአሸባሪነት“ ተመድቧል። የነፃነት ትግሉ ቤተሰቦች የሆኑት እንኳን በነፃነት ትግል ሂደት ውስጥ ገዢው ፓርቲ „በአሸባሪነት“ የሚመድባቸውን መለዬት የሚቸግራቸው ይመስለኛል። እራሳቸውን ጨምረው በተሳሳተው ዬውንጀላ ክሱ ውስጥ የሚደረቡት ይመስለኛል አልኳቸው።“ ከነሙሉ አካሏ ያለችው የነፃነት ታጋይ ለዘመናት የሚሆን ነገር ነበር የነገረችኝ „ ለነፃነት ዬሚደረግ ትግል የቆዳ ቀለሙ ጥቁር ነው። እኛ ቆዳችን ነጭ ነው። ነገር ግን የምንታዬው በአውሮፓ ኮሚሽን ግን እንደ ጥቁር ነው። የምንገለለውም ልክ እንደ እናንተ ነው። በተጫማሪም እንደ አሸባሪነት ነው የምንታዬው። አዎን ለነፃነታችን አሸባሪዎች ነን። በዚህ እደግፍቸዋለሁ። የነጭ ጥቁርነቴንም ለነፃነቴ ስለሆነ ተቀበይዋለሁ። ቆዳዬ ነጭ መንፈሴ ግን ጥቁር ለለበሰ ነፃነት ፅድቅ የሚታገል። በዚህም እኮራለሁ“ አለችኝ። ለዛውም እሷ በተፈጥሯዋ የተረጋጋ መንፈስ የላትም። ቡና እዬሄደች ነው የምትጠጣው፤ ምግብም በመንገድ እዬሄደች ነው የምትበላው፤ ስታናግርም ሌሎች ነገሮችን እዬሰራች ነው። …. የነፃነት ራህብ እንዲህ እራስን ያሰረሳል …. ብክን ያደርጋልም።

ወያኔ ለነፃነታቸው ራሳቸውን የሰጡትን „አሸባሪ“ ቢል አይደንቀኝም። እሱም ያውቀዋል በዓለም ዐቀፉ የአሸባሪዎች ዝርዝር ማን እንዳለ። እሱ ነው ጉብ ብሎ ቀይ መብራቱ ቦግ ያለበት። ወስጤ ቁስል – እርር – ኩምትር የሚለው ግን ለእኛ ንጹህ አዬር፤ ለእኛ የተረጋጋ የቤተሰብ ምሰረታና ኑሮ፤ ለእኛ የህግ ጥበቃና ከለለ፤ ሁሉንም ለሆኑት – ለሰጡት፤ ወጣትነታቸውን ሳይሳሱለት – ለገበሩት፤ የጥበብ ፍቅራቸውን ለነፃነት ትግሉ ላበረከቱ አርበኞቻችን ፍርጃ ውስጥ የእኛው አካል በወያኔ የቅጥፈት ውንጀላ ቃል ማህጸን ውስጥ መጸነሱ ወይንም የውንጀላው እትብተኛ መሆኑ ነው። የአራዊት ፍላጎት ወዝ – ጠገብ ከመሆን ምን ይሻላል ትላላችሁ የኔዎቹ?! …. ብቻ እንዲህ ያለ የተሙረቀረቀ ያለዬለት ሰብዕና የአካሌ ጥግ ሲሆን አዝናለሁ ዬሚለው ቃል ውስጤን አይገልጸውም – ፈጽሞ። እያለሁ እሳቱ በላኝ ወይንም የቁጭቱ ነዲድ ገረፈኝ ልበል ይሆን? ወይንስ እንደ ልብ አምላኩ ነብይ „የቤትህ ቅናት በላኝ“ እንዳለው „ለጧፎቹ የተለኮሰው ቃጠሎ እኔንም በሞፈር ዘመት አነደደኝ“ ልበልን?! ምጥና – ማጥ ነው ጉዳችን።  ዓላማውን ከሳተ ከተሳሳተ የነፃነት ቁልፍ መክፈቻነት አንድነኝ ነው። ማህከነ-ተሳህለነ-ማረን ….ኧረ ማረን ፈጣሪ … አይሰማ ጉድ የለ … ህም! የትናንቱ “አሸባሪ” የዛሬ የዓለም የነፃነት አባት የተከበሩ ሟቹ ኔልሴን ማንዴላ ነፃነታቻውን ያስገኙት በእስር ላይ ሆነው ነው። እስራቸው ጉልበታም ነበርና። ዬእኛዎችም የነፃነት አርበኞቻችን የሚከፍሉት መከራ በራሱ የነፃነታችን አስገኝ ጉልበታም ኃይል አለው። አረበኞቻችን ለምትከፍሉት መስዋእትነት ከክብር ጋር እናመሰግናለን። ታሪካችንም ናችሁ!

የወያኔ ምርጫ እጅግ ብስጩ – ገረጭራጫ – ተንኳሽ እንዲሁም ቁጡ ስለሆነ፤ ነገ ከነገ ወዲያም ይቀጥላል ማናቸውም ዓይነት ጥቃቱ። ያው ጥቃቱ ማህተሙ እስኪመታለት ድረስ እኛው – እኛን እንታገላለን። የካቴና ፊርማ መፈረሙ ሲረጋገጥ በቃ ምን ሲገደን የአለም ውብ ውደሳዎች መደርደር ነው። „ጀግና – አርበኛ – ሰማዕት – በተግባር የጸደቀ ..“ አሁን ወጣት ፓለቲከኛው አቶ ይድነቃቸው የበሰለ ሃሳቡን – ግንዛቤውን – ዕይታውን በድፍረት እዬገለጸ ነው። አቅምን ዋጮው ወያኔ ደግሞ በዓይነ ቁራኛ እዬተከታተለው ነው – እሰከ ቤተሰቦቹ – ወገኖች ድረስ። ጉልበታም ትችቱን – ወያኔ አይወድለትምና። ነገ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና በህይወቱ አንድ ነገር ቢደርሰ ፎቶውን ይዘን አደባባይ … አካውንታችን ሁሉ የእሱ ፎቶ …. በቃ። አቶ ሃብታሙ አያሌው በፓናል ውይይቶች ሁሉ የሚቃርባቸው ስልጡን ሃሳቦቹ ውስጥ ነበር። ያን ጊዜ ምንም ነበር – ለእኛ። ዛሬ ደግሞ በላይ ዘለቀ። በላይ ዘለቀ ማለት የሀገር አንጡራ ታሪክ ማለት ነው። ለወጣቶቻችን ሻማነት ቢያንስ ለሚከፍሉት መስዋዕትን ቅርብነት እንኳን አቅም ያነሰዋል። ለእኔ ወጣት ይድነቃቸውና ሳልጠግበው እንደ ሳሳሁለት የካቴና እራት የሆነው ቅኑ የግንባር ሥጋው አቶ ሃብታሙ አያሌው አኩል መስመር ያሉ፤ መሳ ለመሳ የሚገኙ የነገ ፀሐዮቻችን ናቸው – ሌሎችም። ውድ የሀገሬ ልጆች አቅማችን አናሳፍፈው – ወይንም አንጋፋው – እባካችሁን። ፍላጎታችነንም አንገቱን አናስደፋው__ አራዊቱ ወያኔ ይበቃቸዋል።

ወጣቶች ግለኞች አይደሉም። ወጣቶች መንፈሳቸውን ለህዝብ ፍቅር ፈቅደው የሚለግሱ ሻማዎች ናቸው። እያሉ እንኳን እስኪ እናክብራቸው – እስኪ እንወደዳቸው – እስኪ እናበረታታቸው – ነፃነት ማለት እናት ማለት ነው። ምድር ሁሉንም የሚችል ሁሉንም የሰጠው ነው። ስለዚህ መሬት በእናት ትመሰላለች። እኛ ሊርብን የሚገባው ነፃነትም እናት ሆድ መሆን አለበት። ስለዚህ ሃሳባቸውን – ራዕያቸውን – ዕይታቸውን – ፍላጎታቸውን ያለገደብ ያለ ተዕቅቦ ይስጡ … ቢያንስ ያ ካቴና እስኪቀማን ድረስ። …. ወይንም በሆነ ነገር መንፈሳቸውን …. እህ …. እ! ቀደም ባለው ጊዜ ርትዑ አንደበት በተሰጠው በአቶ  ሃብታሙ ላይ፤ በብዕረኞች በአብርሽ ላይ ሆነ በተሜ ላይ የነበረባቸውን ነገር እናውቀዋለን። አሁን ደግሞ „አንድ ዓይን ቢኖር አሱንም በዘነዘና“ ይላል ጎንደሬ ሲተርት። አብሶ በጋለ ምጣድ ላይ እንደ አሹቅ ለሚቀቀሉት አትኩሮት – የመንፈስ ድጋፍ ጥበቃ ማድረግ ይገባል። ይመስለኛል። መሽቶ በነጋ ቁጥር – የስጋት ዝግን … ነው ዕጣ ፈንታቸውን እዬፈተለው ያለውና።

ምርጫው የወያኔ ሃርነት ትግራይን ፍላጎት ለማስቀጠል ነው። ሌላው ቀርቶ በተቃዋሚ ጎራ ተሰልፊያለሁ የሚለው ባለ – ጎራዴም ቢሆን አድፍጦ የተቀመጠው ወያኔ ቢያዳልጠው ያንኑ የተገኘውን ነባር ጥቅም ለጎጥ ፍላጎቱ ለማስጠበቅ ተብሎ ነው። ከመንጋ አስተሳብ የህዝብ ጥቅም ዕሳቤ ይመነጫል ብሎ ማለሙ ሂሳቡ – ቀመሩ – አምክንዮው ለእኔ አይገባኝም።

በተረፈ እሳት ላይ ያሉት እነሱ፤ ቋያ ላይ ያሉት እነሱ፤ ወላፈኑ የሚገርፋቸው እነሱ ስለሆነ እኛ አስተያዬታችን እንደ ዜጋ ልንሰጥ ብንችልም „ከባለቤቱ ያወቀ … “ እንዳይሆን የኖሩንበትን የወያኔ አጨዳ በአዟሪት ትዕይንት እናድሰዋለን ካሉ፤ መካራውን እንችለዋለን፤ ትክሻችን ደንዳና ነው ካሉ ምርጫውም – መብቱም የእነሱ ነው። ድካሙ ግን ለሁለት ቢበዛ ለ5 ተማራጭ ነው። ወረዳና አውራጃ ገበሬ መንደር ደግሞ ሺዎች ይህ ዕውን ይሆናል ብለው ሁሉንም ይቀባላሉ። ዛሬም፣ የዛሬ አራት ዓመትም፤ የዛሬ ስምንት ዓመትም፤ የዛሬ 16 ዓመትም ወዘተ …  ከሶሻሊዝም ለዛውም ከጎጥ ሶሻሊዝም ብናኝ የብዙሃን ነፃነት ይገኛል ብሎ መጠበቅ ቀን እንደ ሆነ ሳይጨልም ተውሎ ይታደራል ማለት ነው – ለእኔ።

በምርጫ ማሸነፍ ሲባል በነፃ መሬት፤ ዬብዙኃኑ የድምጽ የበላይነት አቅም የማግኘት ተጨባጭ ሁኔታ መኖር ሲቻል ብቻ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ለጥቂት ግለሰቦች መንፈስ ሊሆን የሚችል ፍርፋሪ ሊገኝ ይችል ይሆናል። ለዛውም ከተቻለ። አንድ ሰው አንድ ነው – በድምጽ ሥርዓት። በተለያዩ የወያኔ ምርጫዎች በወያኔ ሸንጎ ወንበር ያገኙ ወገኖች ምን አሻሻሉ? ምን አስለወጡ? ምን ፈጠሩ? ምን ተጽዕኖ የማሳደር ሆነ የመፍጠር አቅም ነበራቸው? ካለፉት ጊዜያቶች መስቀያ ገመዱን ፤ ማቃጠያ ቤንዚኑን፤ ማሳደጃ ህጉን፤ ቀነሰን? ላላን? ተሻለን? ትንፋሽን መሰብሰብ ተቻለን? ይህን ህሊና ያለው ወገን ሁሉ ቁጭ ብሎ ይመዝነው። ጥያቄዎችን ከታሰሩበት በትክክለኛ ብይን ይፍታህ ይበላቸው። አይደለም ጥቅል ማንፌስቶ መቀዬር የጎጥ ስያሜውን እንኳን ማስቀዬር አልተቻለም – እንዲያውም ህዝብ ሃብቱን አደቫቫዩን ተቀማ። አይፈቀድለትም መስቀል አደባባይ ላይ የመሰብሰብ የመናገር << አንዲት አንቀጽ እንዲሻሻል አቅም አልተገኘም …. ልዩነቱ የቀደሙት ለህዝብ ጥቅም ያደሩት ጨለማ ውስጥ፤ ሁለመናቸውን በትነው ምሰሶዎችን (pilars)  እዚያው አይሆኑ ሆኑ። ውክልና ያገኘው ደግሞ ከቀዮዋ በር ሳይደርስ …. !

እኔ እንጃ እንዴትና እንዴት ልንገናኝ እንደምንችል። ገና የመንፈስ ውህደታችን እኮ „ለአቅመ አዳም አልደረሰም“ በጥቅስ ያስገባሁት ወያኔን „ለአቅመ አዳም አልደረሰም“ የሚል ከሥነ ጥበብ አንባ ከማከብረው ወንድሜ የወሰድኩት ስለሆነ ነው። እውነት መስዋዕትነቱን ማድመጥ ብንችል ምንኛ መልካም በሆነ ነበር። የሰማዕቱ የኔሰው ገብሬ ይበቃ ነበር። አቶ ሃብታሙ ታሟል መባልን ሰምቻለሁ … ርዕዮት ውብሸት ስቃያቸው ከህመም ጋር …. የትናንትኗ ወጣት ሃና ሰቆቃ ብቻ አይበቃም?! የሚያክም ሃኪም እስክታጣ ድረስ – የነገ ቀንበጥ ተስፋ …. እንድትሞት ተፈረደባት። ማነው የዚህች ዕንቡጥ ጠበቃው?! ስለምንስ ያ የአለም ዬሥነ ጹሑፍ መብራት ሊቀ – ሊቃውንት ጧፉ ሃይሉ ጎመራው እንደ ወጣ መንፈሱ ከጣዕሙ ጋር ሳይገናኝ አፈር ሆነ?! …. እውነት እውነትን ብናምነው ወያኔ መቀጠል የሌበት ድርጅት በሆነ ነበር። ለዚያውም ደግሞ እንዲህ የእሱ የማጥቂያ ተውኔት የመድረክ ታዳሚ በመሆን … እህ!

ሁለትና ከዚያም በላይ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን፣ መርሃቸውን፣ ተስፋቸውን፣ ይዘው ከዋና ጠላታቸው ወይንም ከአጋር ፓርቲዎች ጋር መንፈስ በማደራጀት መፎካከራቸው መልካም ነው። ሃሳብን በሃሳብ ማታገል የተገባ ነው። ውጪ ሀገርም የምናዬው ይሄንኑ ነው። ከጥላቻና ከቂም በቀል በጸዳ ሁኔታ። ይህ ግን ነገን ለማራቅ ወያኔ ባሰበው አስመሳይ ቀለበት ገብቶ ሳይሆን እንዲያውም በጎን ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው እዬተደጋገፉ ጠላታቸውን እርቃኑን ለማስቀረት በጊዜያዊ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን በዘላቂ ፍላጎት ላይ፤ በግለሰቦች ክብርና ፍላጎት ላይ ሳይሆን ይልቁንም በፓርቲዎች ራዕይና በህዝቡ ፍላጎት መሃከል የጸና የመንፈስ ድልድይ – እንዲኖር ማደረግ ነው ቀዳሚ ተግባር ሊሆን የሚገባው እንጂ  ….

የጎንዮሽ መደጋጋፍ አለመኖር ለአረሙ ወያኔ የሃይሉ የቁጠባ ባንክ ነው የሚሆንለት። ላሜ ወለደች ዓይነት፤ በዬተራ መድቦ እዬነጠለ ስለሚያድክም፤ አጋጣሚዋን ሲያገኝ በአንዱ ላይ ለማዳካም የሚሰነዝረው ጥቃትን ለሌላ ስውር ተግባሩ ያውለዋል። ስለምን? የእሱ የጋራ ተቀናቃኞች አካላቸውን – አካላቸው በመንፈስ ስለሚያዳክምለት። ስለሚተችለት፤ ስለሚያገልለት፤ ስለሚያዝልልት አራት ኪሎው ሆኖ ችርስ ነው … ወያኔ ብዙ ነገር ይቆጥብለታ – ላ። ብዙ የማይታዩ ትርፎችን ይዝቅበታ- ላ። ይዝናናበታል – ጭንቀቱንም ውጥረቱን ያረግብበታል ….

ፍቅር የሚባለው ነገር ቅፅበት ነገር አይመስለኝም። ቅፅበቱ አጀንዳ ለመሆን ያለው ደወሉ ወይንም የብልጭታ ጊዜው ነው። ጠቃሚው ነገር ግን በውስጥ ያለን የወልዮሽ ዬነፃነት ፍላጎት ፍቅር ኮትኩቶ ከማሳደጉ ላይ ነው። ለፍላጎታችን ተመሳሳይ የፍቅር ሙቀት ሰጥቶ ኮትኩቶ የማሳደግ ክህሎትን በአጽህኖት ይሻል። ካለፈው ጊዜ በተሻለ መልኩ ከነጠረው ፍላጎት ጋር ያለው መተሳሳር መከራውን እንደ መንገድ ጠራጊነት አይቶ፤ ፍቅርን መጋራቱን – ሃይል አመንጪ፤ አቅም ጨማሪ ማድረግ ያስፈልግ ይመስለኛል። ያሳልፍናቸው ሶስት ዓመታት እጅግ ጎምዛዛ – ሃሞት ነበሩ። እነዚህ መራራ ጊዜያቶች ለራዕያችን እውንነት መዋለ ንዋይ የማድረግ ብልህነት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ዕንባ ነገን አጉብጦ ለማስቀጠል ሳይሆን የጎበጠውን ቀን ቀና — ቀና — ቀና እያደረገ ቁሞ እንዲሄድ የማድረግ ሥልጡን ተግባር ያስፈልገዋል። ለዚህ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ የአምልኮ ቦታዎች፤ ማህበራት ሁሉ በዚህ የፍቅር ጅረት ቢጠቃለሉ ሞገዳማ ማዕበልን ወይንም እሳተ ጎመራን ይፈጥራሉ። ለዚህ ነው ከወቅቱ ጋር በፍጹም ሁኔታ የሰመረውን የጸሐፊ አቶ ዮፍታሄን ፍላጎት እንድናዳምጥ፤ ከልብ ሆነን ጠረኑን እንድንመገበው በአጽህኖትና በተደሞ በትህትና ደጋግሜ የማሳስበው።

ክውና። መጀመሪያ እኛና እኛ እንተዋወቅ። በዚህ ቁልፍ የፍላጎታችን ስምረት ይሆናል – ታዲያ መተዋወቁን በመቁንን ሳይሆን በገፍ ካደረግነው ነው። ግን ግን በነገራችን ላይ ፍቅር ነው ወይንም ዕምነት መጣል እውር የሚያደርገው ይሆን? ጨርስኩ – የልብ አድራሼን ዘሃበሻ አመስግኜ። የኔዎቹ – መሸቢያ ሰንበት – ኑሩልኝ።

መቅደምና መቀደም ልዩነታቸው ለገባው የነፃነት አርበኛ ዬፍላጎቱን መንገድ ከማፍታታ ይጀምረዋል፤ …  ከዛ – ሩጫውን

መፍቻ

  • ጦሮ … እጅግ ኃይለኛ የነፋስ ቁጣ ነው። ጦረኛው ነፋስ ቁጣው ሲነሳ የሚቀረው የለም። ያገኘውን ሁሉ እዬጠረገ የትሜና ይሰደዋል። ቆርቆሮውን እዬነቃቀለ፤ ክብርን እዬገለበ አቧራ ባዘለ ፉጭቱ ቅጣቱን እስኪበቃው የለርህራሄ ያነደዋል። የወያኔ የምርጫ ዘመቻም ለዚህው ለጦሮ ባህሬው እርገት ነው። – እንስማማ።
  • አሳቻ ባለፈው ፁሑፌም ገልጨዋለሁ „አሳሳች“ ከሚለው መሰረታዊ ቃል የተራበ ነው። ማሳሳቻ የተሰወረ መንገድ እንደ ማለት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 

 

ታላቅ የሰላማዊ ሰልፍ 02.12.2014 BERLIN ሰአት 08:30

0
0

ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚቴ

የአለም ሰብአዊ መብት ቀን በሚጀምርበት ሳምንት የኢትዮጵያን አምባገነን ስርአት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ወደ በርሊን ጀርመን መምጣት መክንያት በማድረግ

ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተዘጋጅቶዋል

የሰላማዊ ሰልፍ አላማ

1,በኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩት የፖሊቲካ  እስረኞች በጠቅላላ ባስቸኩዋይ  እንዲፈቱ

2,ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዲቆም

3,ኢትዮጵያውያንን የሚያፈናቅሉ የሸንኮራ  አገዳ እርሻ  እና መሬት ቦንድ በዶቸ ባንክ በኩል ለዉጭ ነጋደዎች በዶላር ሽያጭን በመቃወም የጀርመን መንግስት እንዲሁም ያገሩ ነጋዴዎች እና

ዶቸ ባንክ ጸረ ሰብአዊነት ወንጀል ላይ መካፈሉን እንዲያቆሙ

4,የጀርመን መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ በስልጣን ላይ ላለው አምባገነን ስርአት የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲያቆም

እንጠይቃለን !!!

በዉጭ ጉድይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፊትለፊት ኣልፎ ወደ Kanzler Amt ጽ/ቤት ፊትለፊት ቀጥሎም ወደ

Potsdamer Platz Deutsche Bank ፊትለፊት

ቀጥሎም የእርዳታና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ጽ/ቤት ፊትለፊት

ከዛም በ SPD ዋና ጽ/ቤት ላይ ያበቃል

 

ሰልፉ የሚጀምርበት ሰአት 08:30

ሰልፉ የሚጀምርበት ቦታ Neptunbrunnen

Spandauer Straße 10178 Berlin

Nähe  Rotes Rathaus

 

Info Tel:. 0160-4357232

menschenrecht-ethiopia@hotmail.de

ETHIOPIAN HUMAN RIGHTS COMITTEE GERMANY2013-berlin

 

ታልቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በኖርዌይ ኦስሎ ተካሄደ!!!

0
0

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ የወጣቶች ክፍል አዘጋጅነት በዛሬው እለት ሀሙስ (November

27,2014) በኖርዌ ኦስሎ በእንግሊዝ ኢንባሲ ፊት በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሩቅም ከቅርብም በአንድነት

በመሰባሰብ ከቀኑ 13፡30 እስከ 15፡00 ስዓት ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።

የሰልፉ ዋና አላማ የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሃፊና የሰባዊ መብት ተቆርቋሪ የሆኑት አቶ

አንዳርጋቸው ፅጌ በአንምባ ገነኑ የወያኔ ቡድን በህገ ወጥ መንገድ ታፍነውና ፍትህ ተነፍገው በእስር ቤት መታሰራቸውን

ለመቃወም ሲሆን በሰልፉ ስፍራ የተገኙ ሰዎች ሁሉ አቶ አንዳርጋቸው ለዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት መከበር ከወጣትነት

ጀምሮ የታገለ ታላቅ የሰላም ምሳሌ፣ የፍትህ ተምሳሌት፣ የነጻነት በር ከፋች እንዲሁም አገራዊ ስሜት የተላበሰ አርበኛ እንጂ

እስር፣ ድብደባና መሰቃየት የሚገባው ሰው አልነበረም በማለት ለእንግሊዝ መንግስት በኢንባሲው አማካኝነት ዜጋዋን

ከአረመኔና ጨካኝ መዳፍ እንድትታደግና ፍትህ እንዲያገኝ በከፍተኛ ድምጽ አሳስበዋል።

ወጣቶች እጃቸውን በሰንሰለት በማሰር እኛም እንደ አርበኛው አንዳርጋቸው ጽጌና በእስር ቤት የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውን

የቁም እስረኞች ነን የሚል ጥልቅ መልእክት አስተላልፈዋል። ብዙ መስራትና መጻፍ የሚችሉ እጆች፣ መናገር የሚችል

አንደበት፣ የእውቀት ባለቤት የሆነ አእምሮ ታስረዋልና እኛም ወጣቶች እስረኞች ነን በሚል ውስጣዊ ስሜት ለስዓታት

የኖርዌ ብርድና ቁር ሳይበግራቸው እጃቸውን በሰንሰለት በማሰር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል።

እንዲሁም ሰልፈኞቹ የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ በታላቅ ድምጽና ስሜት ለኢንባሲው አሰምተዋል። ከአሰሟቸው

መፈክሮች መካከል ለአብነት “ UK, were is your citizen, Free Andrgachew Tsige, Andargachew is our

icon of democracy, where is your action , stop discrimination among citizens, Yes, we are all

Andrgachew Tsige, Brtain dont support terrirost regim in Ethiopia” የሚሉት ይገኙበታል::

ሰልፎኞችም የኢንግሊዝ መንግሥት የነጻነት ታጋዩን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ከወያኔ እጅ እስካላወጡ ድረስ ተቃውሞው

በቀጣይ እስከ መጨረሻው ድረስ ከዚህ በበለጠ ቁጣና እልህ በተሞላበት ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ ተናግረዋል።

በተመሳሳይም ለአንዳርጋቸው ያላችውን ፍቅርና ክብር በአደባባይ አስመሰክረዋል።

በመጨረሻም በድርጅቱ የተዘጋጀውን ደብዳቤ በድርጅቱ ሊቀመንበር በአቶ ዮሃንስ ዓለሙ አማካኝነት ለእንግሊዝ ኢምባሲ

ተወካይ ጉዳዩ ትኩረት የሚሻና ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን ለማሳሰብ ቢፈለጉም ተወካይ ሊመጣ ባለመቻሉ ደብዳቤው በበር

ጠባቂው አማካኝነት እንዲደርሳቸው ተደርጓል። በተጨማሪም ደብዳቤውን በኢሜይል በድጋሚ እንደሚላክ ለሰልፈኞች

አሳውቀዋል። ወደፊት በሚደረገው ተቃዉሞ ላይ ተወካይ መጥቶ እስካልተቀበለንና አቶ አንዳርጋቸው የደረሱበትን

እስካላወቅን ድረስ ከኢንባሲው በር የማንቀሳቀስ መሆኑን ሁሉም በከፍተኛ ድምጽ አሰምተው ዝግጅቱ በተሳካ ሁኔታ ከቀኑ

15፡00 ተጠናቋል።

ዛሬም ነገም ሁላችንም አንዳርጋቸው ፅጌ ነን!!!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ

 

347 344 343 346 345

Viewing all 15006 articles
Browse latest View live